Chosen Fasting by God p 2 , READ IN PDF
ባለፈው ጽሑፋችን በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ፶፰ ስለጾም በሚናገረው ክፍል ጾማችን ምን መምሰል እንዳለበትና ምን መምሰል እንደሌለበት በማየት ከጥልና ከክርክር በመራቅ፡ በመልካም ምግባር መታጀብ እንዳለበት የሚገልጸውን የመጀመሪያውን ክፍል አይተናል። በዚህ ክፍል በጾማችን የምናገኘውን በረከት እናያለን።
ባለፈው ጽሑፋችን በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ፶፰ ስለጾም በሚናገረው ክፍል ጾማችን ምን መምሰል እንዳለበትና ምን መምሰል እንደሌለበት በማየት ከጥልና ከክርክር በመራቅ፡ በመልካም ምግባር መታጀብ እንዳለበት የሚገልጸውን የመጀመሪያውን ክፍል አይተናል። በዚህ ክፍል በጾማችን የምናገኘውን በረከት እናያለን።
ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ፶፰፡-
ቁ. ፰. የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል።
የዚያን ጊዜ የሚለው ቃል ከላይ ከነበረው ጉዳይ ጋር አያያዥ ነው። በክፍል ፩ ካየነው ሃሳብ የሚቀጥል ነው። ጾማችን ምን መምሰል እንዳለበት ተረድተን በተግባር የፈጸምነው እንደሆነ፡ ለሌሎች የነፍስ መዳን ንስሐን በማሰብ ከጠብና ክርክር በመራቅ፡ ፣ በፍቅር፡ በመልካም ምግባር፡ የተራበን በማብላት፡ የተጠማን በማጠጣት የታረዘን በማብላት…. የታጀበ ከሆነ የዚያን ጊዜ የምናገኛቸውን በረከቶች ይዘረዝራል። ብርሃን፡ ፈውስ፡ ጽድቅ፡ ጥበቃ።
- ብርሃን፡- ጨለማን የሚያስወግድ ክስተት ነው፡፡ በዓለም ለተፈጥሮው ጨለማ የፀሐይ ብርሃን ይወጣል። የሕይወት ጨለማ ለሆነው ጭንቀት፡ ተስፋ መቁረጥ ብርሃን ያስፈልጋል። ይህም ብርሃን በጌታ በደስታ በእረፍት ያለጭንቀት መኖር፡ነው። ጨለማ አያሳይም፡ ምንም የሕይወት ተስፋ በሌለበት፡ ምን እበላለሁ? ምን እጠጣለሁ?... ብለን ከምንጨነቅበት ሁኔታ ያስወጣናል፡ ሕይወታችን ይመራል። ምድራዊ በረከትን ያመለክታል።
- ፈውስ፡- የሥጋም የነፍስም ሊሆን ይችላል። ለሥጋ በሽታ ሃኪም መድኃትን ቢያዝም ፈውስ ግን ከእግዚአብሔር ነው። ጾም ለበሽታ ፈውስ አንዱ መሣሪያ እንደሆነ ጌታ ተናግሮአል።«ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጦም በቀር አይወጣም አላቸው።» ማቴ ፲፯፡፳፩። የነፍስ በሽታ ኃጢአት ነው። በክርስቶስ በማመን የምናገኘውን የነፍሳችን ድኅነት (መዳን) ጠብቀን የምናቆየው በጾምና ጸሎት (በአምልኮ) እና በቅድስና በመኖር ነው። ስለዚህ ጾም የነፍሳችንን መዳን (ፈውስ) ለማቆየት አንዱ መሣሪያ ነው። ፈውስ ወይም መዳናችን እስከመጨረሻው ከጸና ለፍሬ ይደርሳል። እስከዚያ መብቀል (ማደግ) አለበት። ለዚህም ጾም ያስፈልጋል ማለት ነው። ፈውስህ ፈጥኖ ይበቅላል።.. ለፍሬም ይደርሳል። ማለት ነው። ለመንፈስ ቅዱስ ፍሬ። (ገላ ፭፡፳፪)