Tuesday, February 28, 2017

እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? (ክፍል ፪)

Chosen Fasting by God p 2 , READ IN PDF
ባለፈው ጽሑፋችን በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ፶፰ ስለጾም በሚናገረው ክፍል ጾማችን ምን መምሰል እንዳለበትና ምን መምሰል እንደሌለበት በማየት ከጥልና ከክርክር በመራቅ፡ በመልካም ምግባር መታጀብ እንዳለበት የሚገልጸውን የመጀመሪያውን ክፍል አይተናል። በዚህ ክፍል በጾማችን የምናገኘውን በረከት እናያለን።
ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ፶፰፡-
ቁ. ፰. የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል
የዚያን ጊዜ የሚለው ቃል ከላይ ከነበረው ጉዳይ ጋር አያያዥ ነው። በክፍል ፩ ካየነው ሃሳብ የሚቀጥል ነው። ጾማችን ምን መምሰል እንዳለበት ተረድተን በተግባር የፈጸምነው እንደሆነ፡ ለሌሎች የነፍስ መዳን ንስሐን በማሰብ ከጠብና ክርክር በመራቅ፡ ፣ በፍቅር፡ በመልካም ምግባር፡ የተራበን በማብላት፡ የተጠማን በማጠጣት የታረዘን በማብላት…. የታጀበ ከሆነ የዚያን ጊዜ  የምናገኛቸውን በረከቶች ይዘረዝራል። ብርሃን፡ ፈውስ፡ ጽድቅ፡ ጥበቃ።
-  ብርሃን፡- ጨለማን የሚያስወግድ ክስተት ነው፡፡ በዓለም ለተፈጥሮው ጨለማ የፀሐይ ብርሃን ይወጣል። የሕይወት ጨለማ ለሆነው ጭንቀት፡ ተስፋ መቁረጥ ብርሃን ያስፈልጋል። ይህም ብርሃን በጌታ በደስታ በእረፍት ያለጭንቀት መኖር፡ነው። ጨለማ አያሳይም፡ ምንም የሕይወት ተስፋ በሌለበት፡ ምን እበላለሁ? ምን እጠጣለሁ?... ብለን ከምንጨነቅበት ሁኔታ ያስወጣናል፡ ሕይወታችን ይመራል። ምድራዊ በረከትን ያመለክታል።
- ፈውስ፡-  የሥጋም የነፍስም ሊሆን ይችላል። ለሥጋ በሽታ ሃኪም መድኃትን ቢያዝም ፈውስ ግን ከእግዚአብሔር ነው። ጾም ለበሽታ ፈውስ አንዱ መሣሪያ እንደሆነ ጌታ ተናግሮአል።«ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጦም በቀር አይወጣም አላቸው።» ማቴ ፲፯፡፳፩።  የነፍስ በሽታ ኃጢአት ነው። በክርስቶስ በማመን የምናገኘውን የነፍሳችን ድኅነት (መዳን) ጠብቀን የምናቆየው በጾምና ጸሎት (በአምልኮ) እና በቅድስና በመኖር ነው። ስለዚህ ጾም የነፍሳችንን መዳን (ፈውስ) ለማቆየት አንዱ መሣሪያ ነው። ፈውስ ወይም መዳናችን እስከመጨረሻው ከጸና ለፍሬ ይደርሳል። እስከዚያ መብቀል (ማደግ) አለበት። ለዚህም ጾም ያስፈልጋል ማለት ነው። ፈውስህ ፈጥኖ ይበቅላል።.. ለፍሬም ይደርሳል። ማለት ነው። ለመንፈስ ቅዱስ ፍሬ። (ገላ ፭፡፳፪)
 

Monday, February 20, 2017

እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? (ክፍል ፩)

God chosen fasting part 1, read in pdf
የያዝነው አርባ ጾም ዐቢይ (ታላቅ) ጾም እንደመሆኑ መጠን በመጽሐፍ ቅዱሳችን በምዕራፉ ሙሉ ስለጾም የሚናገረውን ትንቢተ ኢሳይያስ ም. ፶፰ ከሕይወታችን ጋር በማያያዝ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረንን እናያለን።
ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ፶፰፡-
ቁ .፩  በኃይልህ ጩኽ፥ አትቈጥብ፥ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፥ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር።
ኃጢአት ሰዎችን ከእግዚአብሔርን የሚለይ ሲሆን ንስሐ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ የሚያደርግ ተግባር ነው። ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ኃጢአታቸው ሊነገራቸው፡ እነርሱም ኃጢአታቸውን በመናገር ንስሐ ሊገቡ ይገባል። በዚህ ክፍል እግዚአብሔር ነቢዩ ኢሳይያስን ለአይሁድ ኃጢአታቸውን እንዲነግራቸው ያዘዋል። አይሁድ እግዚአብሔርን የሚያውቁና የሚያምኑ ሕዝቦች ቢሆኑም ጥፋታቸው ሊነገራቸው ይገባ ነበርና ነቢዩን ላከላቸው።
ዛሬ እግዚአብሔርን የሚያውቁና፡ በቤቱ ስለሚኖሩ ክርስቲያኖች ጥፋት ምን እያደረግን ነው? ጥፋታቸው ለራሳቸው ተነግሮአቸው ንስሐ እንዲገቡ ወይስ ለሌላው ተነግሮባቸው እንዲበረግጉ?  ወንድሞቻችን ምንም ዓይነት ጥፋት ያጥፉ ቁም ነገሩ ለምን አጠፉ? ሳይሆን እንዴት ይመለሱ? መሆን አለበት። አንድ ወንድም «ከጥፋቴ በፊት መጥፋቴ ያሳስባችሁ» ብሎአል። ብዙ ጊዜ ስለ ጥፋታቸው እንጂ ስለመጥፋታቸው አናስብም። እግዚአብሔር ግን ሁሉም በጥፋታቸው ተጸጽተው በንስሐ ይመለሱ ዘንድ ጥሪ እንድናደርግ በኃይልህ ጩኽ፥  ዝም እንዳንልም አትቈጥብ  ይለናል። በአንድምታውም ጩኽህ አስተምር፡ ማስተማሩን ቸል አትበል ይላል።
ከዚህ ሌላ ብዙዎቻችን በዓለም ያሉ ሰዎችን ኃጢአት በግልጽ መቃወም እንወዳለን። በቤቱ ላሉት ግን ጥፋታቸውን መናገር እንፈራለን። ሰባኪም ይሁን ተማሪ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚታየው (ምናልባት ለራሳቸው የማይታያቸው) ጥፋታቸው ሊነገራቸው ይገባል። ለሕዝቤ  መተላለፋቸውን ንገር ይላል። ለሌላው ተናገር ሳይሆን ለራሳቸው ንገር።
ቁ.፪ . ነገር ግን ዕለት ዕለት ይሹኛል መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውንም ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝብ እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ።
አይሁድ የእግዚአብሔርን ሥርዓቱንና ሕጉን በመጠበቅ እግዚአብሔርን ማምለክ ይወዳሉ። እርሱን ለማስደሰት ሁሉንም ውጫዊ ሥርዓት ለመፈጸም አጥብቀው ይጠነቀቃሉ፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ፍትህን እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።  በአንድምታው በጎ ሥራ እንደሚሠራ ሰው ሁሉ ሕጌን ልታውቁ ትወዳላችሁ፡ ይላል፤ በጎ ሥራ የላቸውም ማለት ነው።
ዛሬም ብዙዎቻችን በምንፈጽማቸው ዕለታዊ የሃይማኖት ሥራዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን በመመላለስ፡ እንደ ጸሎት፡ ጾም፡ ስግደት…ያሉ የአምልኮ ሥርዓቶችን በመፈጸም እግዚአብሔርን ለመቅረብና ደስ ለማሰኘት እንጥራለን። ይህ ጥሩ መነሻ ሊሆን ይችላል። ያለ በጎ ሥራ ይህ ትጋታችን ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ይህ ክፍል ያስተምረናል።

Tuesday, February 7, 2017

እግዚአብሔርን ማወቅ ክፍል ፪


    ማወቅ ማለት ምን ማለት ነው? 
       o   የእገሌን ቤት አውቀዋለሁ ማለት ውስጡን ክፍሎቹን፣ ዕቃዎቹን ወዘተ.. ማለት ነው።

ቤቱን ማወቅ ግን ባለቤቱን ማወቅ ላይሆን ይችላል።

ግዑዝ ነገሮችን በማየት፣ በመጎብኘት ማወቅ ይቻላል።

o   ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ግን አውቃለሁ ለማለት ቀርበን የጠባይ ልውውጥ ማድረግን ይጠይቃል። ለምሳሌ አንድ ሰው« ይህን ውሻ አውቀዋለሁ፣» ቢል እንስሳው ውሻ መሆኑን እያለ አይደለም። ግን ካሁን ቀደም ከውሻው ጋር የተለየ ልምምድ አለው፡- ጠባዩን ስላየ - ኃይለኛ ስለሆነ/ ስለነከሰው ወዘተ ሊሆን ይችላል።

o   እንስሳን ለማወቅ ለማላመድ ጥቂት ቀናት/ ሳምንታት ሊጠይቅ ይችላል። ከዚህ በላይ ደግሞ ሰውን ማወቅ ቀላል አይደለም። ምክንያቱም ስለሰዎች የምናውቀው እኛ ባየናቸው፣ በሰማናቸው.. መጠን ብቻ አይደለም፤ ሰዎቹ ስለራሳቸው ማንነት በለቀቁት መጠን ጭምር ነው። -- ዋናው ይህ ነው። ስላየናቸው አብረናቸው ስለኖርን ብቻ ላናውቃቸው እንችላለን። --- ሰዎችን ለማወቅ ወሳኙ ነገር ሰዎቹ ራሳቸውን የሚገልጡበት ሁኔታ ነው።

 ስለእግዚአብሔር ማወቅ ሰዎች ሁሉ ከእነዚህ ከ፫ቱ አይወጡም፡

፩. ጭራሽ አለማወቅ- ሰምተው የማያውቁ….. ጥቂት ሰዎች

፪. የተሳሳተ ማወቅ- ያወቁት መስሏቸው፣ ግን በደንብ አለማወቅ፡- አለመገናኘት።….. አብዛኛው ሰው

፫. ትክክለኛ እውቀት፡- ማወቅ፣ ማናገር፣ እርሱም- መስማት፣ መመለስ። … የተወሰነ ሰው

እኛ የትኛው ውስጥ ነን? በትክክል እናውቀዋለን ወይ? ያ ከሆነ ስናናግረው የሚሰማ እና የሚመልስ እንደሆነ ሊገባን ይገባል።

እግዚአብሔርን ማወቅ ማለት በትክክል ካየነው በእግዚአብሔር ዘንድ መታወቅ ማለት ነው።

ከእርሱ ጋር መስማማት ፣ በግል ሕይወት መለማመድ እና መቀራረብ፣ መገናኘትን.. ያካትታል።

፪. እግዚአብሔርን እንዴት እናውቀዋለን?

-      እግዚአብሔርን ለማወቅ እኛ ምን ማድረግ አለብን ወይም  ምን ማድረግ እንችላለን?

-      እግዚአብሔርስ እንዲታወቅ እርሱ ምን ማድረግ አለበት/ ነበረበት? ወይም ምን አድርጓል?

-      እኛ ተምረን፣ ተመራምረን እንደርስበታለን? - አንችልም። እንኳን እርሱን የፈጠረውንም ተምረን አልጨረስነውም።

-      እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ አውቅን መረዳት/ መጨረስ እንችላለን? -- አይቻልም፡- ምክንያቱም፡-

o   ፩. የቋንቋ ውስንነት

o   ፪. የአእምሮ ውስንነት

-      ስለእግዚአብሔር ልናውቅ የምንችለው

o   ፩. እርሱ የገለጠልንን ያህል

o   ፪. እኛም መረዳት የቻልነውን ያህል

እግዚአብሔር የመገለጥ አምላክ - እርሱ ራሱን ገልጧል / እየገለጠም ነው። እነዚህ መገለጥ ሁለት ዓይነት ናቸው።

፩. አጠቃላይ መገለጥ፡-  በተፈጥሮ እና  በኅሊና

፪. ልዩ መገለጥ፡-  በመጽሐፍ ቅዱስ እና በኢየሱስ ክርስቶስ

o   ተፈጥሮ እና በመጽሐፍ ቅዱስ - ስለእግዚአብሔር እናውቃለን።

o   ኅሊና እና በኢየሱስ ክርስቶስ - እግዚአብሔርን እናውቃለን።

-      ስለእግዚአብሔር ማወቅ - እግዚአብሔርን ከማወቅ ፈጽሞ የራቀ እና የማይወዳደር ነው።

አንዲት ዓሳ እናቷን - « ሁልጊዜ ሲወራለት የምንሰማው ውኃ ምን ዓይነት ነው? የት ነው ያለው?»  ብላ ስትጠይቅ፣ እናቲቱ ዓሳ ከውቅያኖሱ ሥር ልጇን አስቀምጣ፣ በፕሮጄክተር  ፎቶ፣ ፊልም እያሳየች - «ውኃ ይህን ይመስላል» ብላ ካስተማረቻት በኋላ -- «እንግዲህ ትንሽ ፍንጭ ካገኘሽ ራስሽ ሂጂና በዙርያሽ እንዲሄድ በውስጡ ሆነሽ ተለማመጂ»  ብላ ለቀቃቻት።

o   መጽሐፍ ቅዱስ መምህራን ተፈጥሮ፣-  ስለ እግዚአብሔር እንድናውቅ ያደርጉናል። ስለውኃ በሰሌዳ፣ በስዕል፣ በቤተሙከራ /በትንሽ ብርጭቆ/ መማር ማለት ነው።

o   በልባችን ክርስቶስን አምነን ወደ ሕይወታችን ስናስገባው  - ወደ ውቅያኖሱ ገባን - እግዚአብሔርን ማወቅ እንጀምራለን። ሕይወታችን እንዲመራ፣ እንዲገዛ እንዲቆጣጠር እንፈቅድለታን - በእርሱ ሙላት ውስጥ እንሆናለን። ያን ጊዜ የሕይወት የመኖር ትርጉም እየገባን ይሄዳል።
/ይቀጥላል..../