በመጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር የመጀመሪያው ቃል (ንግግር)
በመጽሐፍ ቅዱሳችን በመጀመሪያው መጽሐፍ በመጀመሪያው ምዕራፍ እግዚአብሔር በመጀመሪያ የተናገረው ቃል ብርሃን ይሁን የሚል ነው። ከዚያ በፊት ባሉት ቁጥሮች በዝምታ (በአርምሞ) ሲሠራ ቆይቷል። ሰማይ፡ ምድር፡ ጨለማ፡ መላእክት…. የተፈጠሩት በዝምታው ነው። እግዚአብሔር በዝምታውም ይሠራል። በኀልዮ ይላሉ፡፡ ሲያስብ ይፈጸማል፡ ይከናወናል። የሰው ሃሳብ ምናባዊ የሆኑ ብዙ ነገሮችን ሊያወጣ ሊያወርድ ይችላል። እግዚአብሔር ግን በሃሳቡ ብቻ ተጨባጭ ነገሮችን ያስገኛል። ታላላቆቹና የፍጥረታት መሠረታውያን የተባሉት ፬ቱ ባሕርያት እሳት፡ ነፋስ፡ ውኃ፡መሬት የተፈጠሩት በኀልዮ፡ (በዝምታ) ነው።
እግዚአብሔር በምን ተናገረ?
እግዚአብሔርም፦ ብርሃን ይሁን አለ። እግዚአብሔርም… አለ። ይህ የተናገረበት ቃል ከሦስቱ አካላት አንዱ የሆነው አካላዊ ቃል ወልድ በኋላም ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ቃል ነው። እግዚአብሔር በሦስትነቱ ሥላሴ ሲባል አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው። ሥላሴ በአብ ልብነት ያስባሉ፡ በወልድ ቃልነት ይናገራሉ፡ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት ሕያው ሆነው ይኖራሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር የተናገረበት ቃል ወልድ ነበረ።
በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ዮሐ ፩፡ ፩።
ያ ቃል ወልድ በሐዲስ ኪዳን ሥጋን ለብሶ ሰው የሆነው፡ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው፡ ዓለምን ሁሉ ያዳነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ….. ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ዮሐ ፩፡ ፲፬።
ዛሬ እግዚአብሔር በምን ይናገራል?
- በብሉይ ኪዳን በዝምታ፡ በሕልም፡ በራእይ፡ በነቢያት፡…. በወልድ ቃልነት ይናገር ነበር።
ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ዕብ ፩፡፩
-በሐዲስ ኪዳን የሚያናግርበት መንገድ አንድ ብቻ ነው።
ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን። ዕብ ፩፡፪
እንግዲህ እግዚአብሔር ዛሬ እኛን የሚያናግረን በዚያው ቃል - በወልድ - በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንም የምናውቀው በተጻፈው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ እና በመምህራን አማካይነት ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር የሚያናግረንን ለማወቅ፡ ብሎም ለመታዘዝ ቃሉን - ይሄውም ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እና መጽሐፍ ቅዱስን - ማወቅ አለብን ማለት ነው። ይህ ቃሉ ዓለምን የፈጠረ - ፈጣሪ፡ ዓለምንም ያዳነ - አዳኝ ዛሬም የእኛን ሐይወት ያዳነ- የሚሠራ አካላዊ ቃል ነው። እግዚአብሔር ሲያናግረን ልናዳምጥና ልንጠቀምበት ይገባል።