Tuesday, July 31, 2012

የእግዚአብሔር ቃል

ሰማያትን ያለምሰሶ ያጸና ነው፡
«በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ» መዝ ፴፫፣፮

ዓለማትን የፈጠረ ነው፡
«ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን።» ዕብ ፲፩፣፫

ሰማይና ምድር ሲያልፉም ይቀጥላል፡
«ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።» ማቴ ፳፬፣፴፭።

ለዘላለም ይኖራል
«የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል። በወንጌልም የተሰበከላችሁ ቃል ይህ ነው።» ፩ጴጥ ፩፣፳፭።

ብርቅ የሆነበት ዘመን ነበረ፡
«በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ ራእይም አይገለጥም ነበር።» ፩ሳሙ ፫፣፩።

የረሃብ ዘመን ይመጣል፡
«እነሆ፥ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም።» አሞ ፰፣፲፩።

የበረከት ምንጭ ነው፡
«በኤልያስም እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዱቄቱ ከማድጋው አልተጨረሰም፥ ዘይቱም ከማሰሮው አልጎደለም። » ፩ነገ ፲፯፣፲፮።

የተፈተና ለሚታመኑት ጋሻ ነው፡
«የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ተፈትናለች እርሱ ለሚታመኑት ጋሻ ነው።» ምሳ ፴፣፭።

የሰው ሕልውና በቃሉም እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም
«ኢየሱስም፦ ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል ብሎ መለሰለት።» ማቴ፬፣፬

አይሻርም፡
«ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል የተሻረ አይደለም።» ሮሜ ፱፣፮።

አይታሰርም
«ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም።»
፪ ጢሞ ፪፣፱።

Tuesday, July 24, 2012

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ዳሰሳ-ብሉይ ኪዳን



መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ የዓለምና የሰው ዘሮችን ታሪክ ለመተረክ የተጻፈ / የታሪክ መጽሐፍ አይደለም። ይሁን እንጂ በታሪክ ውስጥ በዘመናት እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ያደረጋቸውን ግንኙነቶች በቅደም ተከተል  እናገኝበታለን። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው አከፋፈሉ በሁለት ዐበይት ክፍሎች ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ተብሎ የተከፈለ ሲሆን እያንዳንዳቸው ወጥ የሆኑ የራሳቸው ታሪካዊ አወቃቀር ያላቸው በመሆኑ ለአጠቃላይ ግንዛቤና ስለምን እንደሚያወሩ ለመረዳት በውስጣቸው ያለውን ታሪካዊ ይዘት ፍሰት በጥቅል መመልከቱ አስፈላጊ ነው።  በዚህም መሠረት ለዛሬ የብሉይ ኪዳንን ታሪካዊ ዳሰሳ እናያለን።
ብሉይ ኪዳን ከዓለም መፈጠር እስከ ክርስቶስ ልደት ያለውን ዘመን የሚሸፍን ነው። በዚህም ክፍል የኦሪት፣የታሪክ፣ የመዝሙራትና የነቢያት መጻሕፍት ይገኙበታል። በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ በሆነው መጽሐፍ በኦሪት ዘፍጥረት በመጀመሪያዎቹ ፲፩ ምዕራፎች መላውን ዓለም የሚወክል የነገሮችን ጅማሬ ያሳየናል። የዓለምን አፈጣጠር፣ የኃጢአት መጀመር፣ የቋንቋ መብዛት፣ የሰው ዘር መባዛት፣ ወዘተ… ይናገራል። ከምዕራፍ ፲፪ በኋላ ግን የአንድን ወገን ማለትም የእስራኤላውያንን ታሪክ ብቻ ይዞ ይሄዳል። ከክርስቶስ ልደት በፊት ባለው የዘመን ስፍር ፭ሺ ፭፻ መሠረት ከዘፍጥረት ፩ - ፲፩ (ከአዳም - አብርሃም) ያለው ክፍል የ፫ሺ ፭፻ ዓመት ታሪክ ሲሆን የቀረው ከዘፍጥረት ፲፪ - ክርስቶስ ልደት (ከአብርሃም - ክርስቶስ) ያለው የ፪ሺ ዓመት ታሪክ እንደሆነ ይነገራል። ብሉይ ኪዳን የተፈጸመው በ፭ሺ ፭፻ ዘመን ውስጥ ቢሆንም የተጻፈው ግን ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ፩ሺ ፬፻ ዓመት  እስከ ፬፻ ዓመት- በ፩ሺ ዓመት ውስጥ ነው።
እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረ በኋላ ከሰዎች ጋር በውል /ኪዳን/ ለመሥራት ለሚያዘጋጀው ለመጀመሪያው ቃል ኪዳን (ለብሉይ ኪዳን) አንድን ሕዝብ እስራኤላውያንን በመምረጥ ለዚህም አብርሃምን በመጥራት ይጀምርና  ከዚያ በኋላ መላው ብሉይ ኪዳን እነዚህ የአብርሃም ዘር የሆኑት እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው የቃል ኪዳን ግንኙነት አንጻር የደረሰባቸውንና ያደረሱትን ጉዳዮች፣ (ታሪካቸውን) ይናገራል።
የመጀመሪያው የብሉይ ኪዳን ክፍል አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት እግዚአብሔር በቀደምት እስራኤላውያን  አበው፡- አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ አማካይነት እስራኤል የተባለ ሕዝብ ለራሱ እንዴት እንደመረጠ፣ ወደ ግብጽ ከወረዱ በኋላ በመሴ እንዴት እንዳወጣቸውና በጉዞአቸው ሕግና ሥርዓቶችን በመስጠት እርሱን ብቻ እንዲያመልኩ በማዘዝ ቃል የገባላቸውን ምድረ-ርስት ለማውረስ እንዴት እንዳዘጋጃቸው ይናገራል።

Friday, July 13, 2012

የመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ - ወንዞችና መልክአ-ምድሮች


ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ከእምነትና ከምግባር ቀጥሎ መረጃዎች አስፈላጊ መሆናቸውን በመጥቀስ ባለፈው ሃገሮችና ከተሞች በሚል ጠቅለል አድርገን አይተን ነበር። ለዛሬ የወንዞችና መልክአ-ምድሮችን አስፈላጊነት በምሳሌ እናያለየን፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው ክፍል በኦሪት ዘፍጥረት ገነትን አጠጥቶ የሚወጣው ወንዝ ከአራት እንደሚከፈል ተጽፎአል።
« ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፣ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር።» ዘፍ ፪፣፲
ለመሆኑ ገነት የሚባለው የዚያን ጊዜ የት ነበር? አሁንስ የትኛው ነው? አራቱ ወንዞች ዛሬ የትኞቹ ናቸው? መረጃ ያስፈልገናል ማለት ነው።
ቃኤል አቤልን  በሜዳ ገደለው፣ ሎጥ ወደ ተራራ ሸሽቶ አመለጠ፣ ለምን ወደ ሜዳ ወሰደው?  በሜዳ ያለ ሰው እና የሚያደርገው ነገር ለሁሉም የሚታይ ስለሆነ መሸሸግም ሆነ ማምለጥ አይችልም። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የመጀመሪያው ነፍሰ-ገዳይ ቃኤል የፈጸመው በደል እንኳን ከእግዚአብሔር ከሰው የተሰወረ አልነበረም። ተራራ ግን ራስን ደብቆ ሌላውን ማየት የሚቻልበት ስትራቴጂያዊ ቦታ ነው። ሎጥ እና ሌሎችም ወደ ተራራ ሸሽተው ሲያመልጡ በመጽሐፍ ቅዱስ እናያለን።
 እስራኤላውያን ቀይ ባሕር ተከፍሎ በደረቅ እንደተሻገሩ በመጽሐፍ ቅዱሰ የተገለጸ ታላቅ ተአምር ነው። እዚህ ላይ አንድ ወንድሜ የነገረኝ ቀልድ አዘል ቁም ነገር ትዝ አለኝ። ሁለቱ ጓደኛሞች አንዱ በእግዚአብሔር የሚታመን፣ ሁልጊዜ በሁሉ ነገር የሚያመሰግን፤ አንደኛው ግን ሁልጊዜ በቀልድና በፌዝ ጊዜውን የሚያባክን ነበሩ። ታዲያ የመጀመሪያው አምላኩን ሲያመሰግን እስራኤላውያንን ቀይ ባሕርን ከፍለህ ያሻገርህ አምላኬ ተመስገን፡ ተመስገን እያለ ይዘምራል። ያመስግናል።  ፈዘኛ ጓደኛው፡- አንተ ቀይ-ባሕር፡ ቀይ ባሕር ትላለህ የዚያን ጊዜ የነበረው ቀይ ባሐር በአሁኑ አንድ ኩሬ የምታክል ውሃ ነው የነበር አለው። በዚህ ጊዜ መንፈሳዊው ይህን ሲሰማ ይበልጥ እያመሰገነ ይፈነጥዝ ጀመር። እንዴ ምነው? እንደዚህ ስላልኩህ ይበልጥ ፈነጠዝክ ቢለው አምላኬ ፈርኦንንና ሠራዊቱን ኩሬ በምታህል ውኃ ማስጠሙ አስገርሞኝ ነው አለው ይባላል። የፈለገ ነገር ቢሰማ ሳይበገር ሁሉንም ነገር ለአምላኩ ክብር አዋለው።
በዚያን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጹት ቀይ-ባሕር፡ ዮርዳኖስ ወንዝ ዛሬ የትኞቹ ናቸው? ምን ይመስላሉ? የሚለውን ማወቃችን መጽሐፍ ቅዱስንና የአምላክን ተአምራት በይበልጥ እንድንረዳ እርሱንም እንድናመሰግን ይረዳናል።