Melkam endehone aye, sebket, READ IN PDF
በመጽሐፍ ቅዱሳችን የመጀመሪያ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ (ዘፍ ፩) እግዚአብሔር ፍጥረታትን በየቀኑ እየፈጠረ በመጨረሻ የሚናገረው ቃል «መልካም እንደሆነ አየ።» የሚል ነው። ይህም ሰባት ጊዜ ተጽፎአል። (ቁጥር ፬፡፲፩፡፲፫፡፲፱፡፳፪፡፳፭፡፴፩)።
ከርሱ በላይ ጥበበኛ የሌለ፡ ለሰዎች ጥበብን የሚሰጥ አምላክ የሠራውን ነገር ሁሉ መልካምነት የሚያረጋግጥለት ሌላ አካል ስለማይኖር ራሱ በዚህ ድንቅ ቃል እያረጋገጠ ፍጥረታትን ፈጥሯል። ሰዎች የሚሠሩትን ነገር ሰዎች ያጸድቃሉ፡ ይተቻሉ፡ ያሻሽላሉ ወይም ውድቅ ያደርጋሉ። እግዚአብሔር ግን በሥራው ፍጹም ስለሆነ አንዳች እንከን ሊኖርበት ከቶ አይችልም። ሰዎች ሆነን ስንፈጠር ምንም እንኳ አዋቂነት ቢኖረንም ባለን የመረዳት አቅም ውስንነት ምክንያት ሁሉንም የርሱን ሥራዎች ለማየትም ሆነ ለመተቸት አንችልም።
አንድ የሚነገር ታሪክ አለ። ሰውየው ፈላስፋ ቢጤ ነውና በሚያያቸው ነገሮች ሁሉ አስተያየት መስጠት ይወዳል። ታዲያ አንድ ቀን መንገድ ሲሄድ ደከመውና በአንድ ሾላ ዛፍ ስር አረፍ አለ። ቀና ብሎ ሲመለከት ሾላው ዛፉ ትልቅ ነው፡ ፍሬው ግን ትንሽ ነው። አጠገቡ ደግሞ የዱባ ተክል ነበረና ሲመለከተው ዱባው ግንዱ ትንሽ ነው፡ ፍሬው ግን ትልቅ ነው መሬት ለመሬት ይጎተታል። ታዲያ ሰውየው ሁለቱን አነጻጸረና አንዲህ ሲል ተናገረ፡-
« እግዚአብሔር አነዚህን ሁለት ዕጽዋት የፈጠረ ቀን ተሳስቷል። ለትልቁ የሾላ ዛፍ ትንሽ ፍሬ፡ ለትንሹ የዱባ ተክል ትልቅ ፍሬ በመስጠት አዘዋውሮታል። ከዚያ ይልቅ ለትልቁ ትልቅ ፍሬ፡ ለትንሹ ትንሽ ፍሬ ሰጥቶ በየመጠናቸው ቢያደርጋቸው መልካም ነበረ።» አለ።
ይህን እያሰላሰለ ደክሞት ነበረና መሬት ላይ ጋደም ብሎ እንቅልፍ ያሸልበዋል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሆነ ነገር አፍንጫውን ይመታውና ይነቃል። ሲያይ አፍንጫው ደምቷል። ከዚያ ከደረቱ ላይ የሾላውን ፍሬ ያገኛል። ነፋስ የጣላት የሾላ ፍሬ አድምታዋለች። የርሱን አባባል አስታወሰ። እኔ ያልኩት ቢፈጸምና ያ ዱባ ከላይ ወድቆ ቢመታኝ…? …ወዲያው እንደተሳሳተ ተረዳና-- እግዚአብሔር ሆይ ያንተ ሥራ ትክክል ነው። እኔ ተሳስቻለሁ፡ ብሎ መሸነፉን አውቆ ንስሐ ገባ። አዎ እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉም አንዳች እንከን የሌለበት መልካም ነው።