Saturday, June 23, 2012

የመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ - ሃገሮች ና ከተሞች


ካሁን ቀደም ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በቅድሚያ ማወቅ የሚያስፈልጉን ጉዳዮች እምነት፡ ምግባርና መረጃ በማለት በእምነት ሥር ስለእግዚአብሔርና ስለክርስቶስ (በምሥጢረ-ሥላሴና በምሥጢረ-ሥጋዌ)፡ በምግባር ሥር ጸሎትና መታዘዝ የሚሉትን አይተናል።ቀጥለን የምናየው ስለራሱ ስለመጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ መረጃዎችን ነው። እነዚህም ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የሚረዱን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሃገሮች፡ ከተሞች፡ መልክአ ምድሮች፣ ወንዞች፣ መንግሥታት፣ ባሕሎች፡ ገንዘቦች፡ እንስሳት፣ ትውልዶች፣ የዘር ሐረጎች፣ ጸሐፊዎች ፣አጻጻፍ፣ አነጋገር፣ ዘይቤ፣ የመጻሕፍቱን ቅደም ተከተል፣ ሥርዓተ ነጥቦች፣ ጥሬ ቃላት ወዘተ… የመሳሰሉት ናቸው። በዚህ ክፍል የእነዚህን ጥቅም በአጭር በአጭሩ ከምሳሌ ጋር እያየን ጥናታችን እንቀጥላለን።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የተፈጸመው፣ ትምህርቱም ትንቢቱም የተጻፈው በአብዛኛው በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይም በእስራኤል ሃገር ነው። አዳም የተፈጠረበት፣ አብርሃም የተጠራበት፣ ኖኅ የጥፋት ውኃ መርከብ የሠራበት፣ እስራኤላውያን ከግብጽ ተመልሰው የወረሱት ምድር፣ የተለያዩ የእስራኤል ነገሥታትና ነቢያት የተነሱበት፣ በሐዲስ ኪዳንም ጌታ የተወለደበት፣ ያስተማረበት፣ የሞተበት፣ የተነሳበት፣ ሐዋርያት ወንጌልን ለማስፋፋት ሥራ የጀመሩበት…. ይህ ሁሉ ከ90% በላይ የሚሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የተፈጸመው በእስራኤል ሃገር ነው። ስለሆነም ከመካከለኛው ምሥራቅ ሃገሮች በተለይ ስለእስራኤል ማጥናት መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ዋና ጉዳይ ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ከዚህ ቦታ ወደ ዚህ ቦታ ሄዱ ሲል የለቀቁትን እና የሜሄዱበትን ሃገሮች /ቦታዎች ሁኔታ ስናውቅ ጉዳዩን ይበልጥ ትኩረት እንድንሰጠው እና መልእክቱን በደንብ እንድንረዳው ያደርጋል። ለምሳሌ አብርሃም ይኖርበት ከነበረው ከከለዳውያን ዑር ወደ ካራን ሄደ።
« ታራም ልጁን አብራምንና የልጅ ልጁን የሐራንን ልጅ ሎጥን የልጁንም የአብራምን ሚስት ምራቱን ሦራን ወሰደ ከእርሱም ጋር ወደ ከነዓን ምድር ይሄዱ ዘንድ ከከለዳውያን ዑር ወጡ ወደ ካራንም መጡ፥ ከዚያም ተቀመጡ። » ዘፍ ፲፩፣፴፩።
በኋላም እግዚአብሔር ከካራን ወጥቶ ወደ ከነዓን እንዲገባ ነገረው።
« እግዚአብሔርም አብራምን አለው፦ ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። » …..«አብራምም ከካራን በወጣ ጊዜ የሰባ አምስት ዓመት ሰው ነበረ።»…..«ወደ ከነዓን ምድር ለመሄድ ወጣ ወደ ከነዓንም ምድር ገቡ።»  ዘፍ ፲፪፣ ፩፡፬፡፭።
የከለዳውያን ዑር በዚያ ዘመን የሰለጠኑ የሚባሉ የመካከለኛው ምሥራቅ ከተማ ነበረች።
ካራን ከዑር በተሻለ የንግድ ማእከልና መተላለፍያ ስለነበረች የአብርሃም አባት ታራ ከዑር ወደ ካራን ቤተሰቡን ይዞ ሄዷል።


ከነዓን በወቅቱ ሰፊ መሬት ቢኖራትም የካራንን ያህል ሥልጣኔ ያልነበራት ትንሽ ከተማ ነበረች፤ እግዚአብሔር አብርሃምን ከሞቀችው ከካራን ከተማ ወጥቶ ወደ ገጠራማዋ ከነዓን እንዲገባ ሲያዘው አብርሃም ምን ዓይነት ስሜት ተስምቶት ይሆን? ይህ ማለት በዛሬው ሁኔታ ብናየው እግዚአብሔር አንድን አገልጋይ ከታላቋ ከተማ ከአዲስ አበባ ወጥቶ  እንደ ጃናሞራ ያለች ትንሽ የገጠር ከተማ ሂድ የማለት ያህል ነው። እኛ ብንሆን ምን ይሰማናል? መቼም አብዛኞቻችን ወደ አዲስ አበባ (እንዲይም ካለ ወደ ባሕር ማዶ) እንጂ ወደ ገጠር ለመሄድ ፈቃደኞች አይደለንም። አብርሃም ለእግዚአብሔር መታዘዙን ሲገልጽ ይህን ሁሉ ስሜቱን አሸንፎ እንደሆነ የምናስተውለው የወጣበትንና የገባበትን ሃገርና ከተማ ሁኔታ ስናውቅ ነው።
ከነዓን ስያሜዋን ያገኘችው ከኖኅ የልጅ ልጅ ነው።
« የካምም ልጆች ኩሽ፥ ምጽራይም፥ ፉጥ፥ ከነዓን ናቸው።» ዘፍ ፲፣፮።

 ከነዓን ምድር እስራኤላውያን ከግብጽ ምድር ተመልሰው የወረስዋት ሲሆን በኋላ እስራኤል ተብላ ተጠርታለች። በሰሎሞን ልጆች ጊዜም ከሁለት ተከፍላ ሰሜኑ እስራኤል ደቡቡ ይሁዳ ተብሎ ተጠርቷል። ከምርኮ በኋላ መላው ሃገር ይሁዳ ተባለ። በቱርክ ቅኝ ግዛት ወቅት ፍልስጥኤም ተባለ። በኋላም በጌታችን ዘመን በሐዲስ ኪዳን በአምስት አውራጃዎች ገሊላ፣ ሰማርያ፣ ይሁዳ፣ ዐሥር ከተማ እና የዮርዳኖስ ማዶ ተብሎ ተከፍሎአል።  ይህ አካባቢ ዛሬ አራት ሃገሮች ሆኗል። እነዚህም እስራኤል፣ ሶርያ፣ ዮርዳኖስና  ሊባኖስ ናቸው።

በሐዲስ ኪዳንም ካለ አንድ ከተማ ለምሳሌ ቆሮንቶስን ብንመለከት ከግሪክ ከተማ ዋናዋ ስትሆን በሥልጣኔዋ የታወቀች፣ የንግድ ማዕከልና የመርከቦች መተላለፊያ ወደብ የሆነች የበለጸገች ከተማ ናት። ከዚሁ ስልጣኔዋ ጋር ኃጢአትም የበዛባት ነበረች። በአጠቃላይ ከተማይቱ የዝሙት ኃጢአት፣ የጣኦት አምልኮ፣ የተስፋፋባት ነበረች። ጳውሎስ በዚህ ስር የሰደደ ክፋት በሞላባት ከተማ ሄዶ ወንጌሉን በመስበክ በትምህርት ለውጧቸዋል። እኛ ዛሬ ወንጌሉ ወንበዴ፣ ኃጢአተኛ፣ ዝሙተኛ… ለምንላቸው መሰበክ እንዳለበት አናስተውልም። ሁልጊዜ ማስተማር የምንወደው ለተከበሩ ሰዎች፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ለሚመጡ ክርስቲያኖች ብቻ እንደሆነ እናስባለን። እንደዚያም እያደረግን ነው። ጌታ ግን በወንጌሉ
« … ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ » ማቴ ፱፣፲፪። ብሏል።
ጌታ ያስተማረው ከተከበሩት የአይሁድ ምኩራብ ይልቅ በኃጢአት በተያዙት ከተሞች፣ መንደሮች እየተዘዋወረ ነበር። እርሱ የሚያስፈልጋቸው እነማን እንደሆኑ መገኘት ያለበት የት እንደሆነ ያውቃልና። በኑሮው ብቻ ሳይሆን በሞቱ ሲሰቀል እንኳ ከወንበዴዎች ጋር ነበረ፡ በዚህም ምክንያት አንዱን አዳነ።

 የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉም ሃገሮች፣ ከተሞች ያስፈልጋቸዋል። ከኛ የሚጠበቀው ቃሉን በሁሉም ቦታና መንገድ ማስተላለፍ ነው። መለወጥ ደግሞ የቃሉ ባለቤት የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው። ከላይ እንዳየነው ቅዱስ ጳውሎስ የቆሮንቶስን ከተማ ኃጢአት የሞላባት ናትና እዚያ መሄድ የለብኝም አላለም።  
እንግዲህ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለሚገኙ ሃገሮች፣ ከተሞች ሁኔታ ማወቅ መጽሐፉን እና በውስጡ የተቀመጠውንም መልእክት ይበልጥ እንድንረዳውና እኛም አገልግሎታችን ምን መምሰል፣ የት መሆን እንዳለበት እንድናስተውል ያደርገናል ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኙ ሃገሮችንና ከተሞችን በየቦታቸው ስንደርስ መረጃዎቻቸውን እያየን ከእኛ ወቅት ጋር እያገናዘብን ጥናታችንን እንቀጥላለን።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣይ ከመጽሐፍ ቅዱስ መረጃዎች ስለ መልክአምድሮችና ወንዞች እንመለከታለን።  
ይቆየን።

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment