ባለፈው ክፍል የዓለምን ፍጻሜ አመላካች የሆኑ ከአሁን ቀደም እኔ ክርስቶስ ነኝ ብለው የተነሱ ሃሰተኞችን እንዲሁም በየቦታው
እስከዛሬ የተካሄዱ ጦርነቶችን መረጃዎች ማየታችን ይታወሳል። ዛሬም ይህንኑ መረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል እየተፈጸመ እንደሆነ
እናያለን።
ማቴ ፳፬፣፯… ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ
ልዩ ስፍራ ይሆናል፤
ራብም፡
ከየትኛውም ዘመን ይልቅ በያዝነው ክፍለ ዘመን ሕዝቦች በተለይ በታዳጊ ሃገሮች የሚገኙ ወገኖች በከፍተኛ ደረጃ በረሃብ
እየተጠቁ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም። የዓለማችን የሃብት ክፍፍል እና የሕዝቦች ስብጥር ሲነጻጸር ምን ያህል ፍትሐዊ እንዳልሆንን
ያሳያል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት 80% የሚሆነው የምድራችን ሃብት
20% በሆነው የዓለም ሕዝብ እጅ ይገኛል። የሚከተሉት እውነታዎች የዓለም የምግብ ፕሮግራም /World Food Program/ በተለያዩ ጊዜያት ካወጣቸው መረጃዎች የተወሰዱ ናቸው።
- እ.ኤ.አ በ2009 ዓ/ም ከአንድ ቢሊየን በላይ የሚሆን ሕዝብ በቂ ምግብ ማግኘት አልቻለም። ይህም ማለት የአሜሪካ፡ የአውሮፓ
እና የካናዳ ሕዝብ ቢደመር እንኳ ይህን ያህል አይሆንም። በወቅቱ ከዓለማችን ከ6 ሰው አንዱ ለረሃብ የተጋለጠ ነበር ማለት ነው፡፡
ከእነዚህም 90 በመቶ በላይ የሚገኘው በታዳጊ ሃገራት ውስጥ ነው።
- ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ምክንያት በየቀኑ 25 ሺ ሕጻናት እና ወጣቶች ለህልፈት ይዳረጋሉ።
- ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ የሚኖርባቸው እስያ እና የፓሲፊክ አካባቢዎች በዓለም ከሚገኙት በረሃብ ከተጠቁት
2/3 ኛው ይገኝባቸዋል።
- በአሁኑ ሰዓት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት /malnutrition/ ከኤች አይ ቪ/ኤድስ፡ ከቲቢ እና ከወባ ከሶስቱም ድምር
በላይ ሕጻናትን እየቀጠፈ ያለ የዓለማችን ችግር ነው። ከአራት ሕጻናት አንዱ የተመጣጠነ ምግብ አያገኝም። በታዳጊ ሃገራት ከ10
ሚሊየን በላይ ለሚሆነው የሕጻናት ሞት 60 በመቶ ምክንያቱ ይሄው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነው። ከ9 ሚሊየን በላይ ለሆነው ከአምስት
ዓመት በታች ባሉ ሕጻናት ለደረሰው የሞት አደጋ ምክንያቱ ይሄው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነው። ይህ ማለት በየ6 ሴኮንድ አንድ
ሕጻን ይሞታል ማለት ነው።
- ከዓለማችን ሕዝብ ከ7 ሰው አንዱ ራቱን ሳይበላ ይተኛል።…….