Friday, June 30, 2017

እግዚአብሔርን ማወቅ - ክፍል ፮


እግዚአብሔርን ፍለጋ - ቀጣይ
፫. የት ነው የምንፈልገው?

፫.፩ በተፈጥሮ፡-  ለእግዚአብሔር ሕልውና የመጀመሪያው ማስረጃ ሥነ ፍጥረት ነው።

የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤   ሮሜ ፩፣ ፳

እየመረመሩ ከተባለ - ለመመርመር ስሜት ህዋሳቶቻችንን እንጠቀማለን። ከእነዚህም አንዱ እና ዋናው ማየት ነው። ምን እናያለን? የምናየው ምንድን ነው?

ሀ. ፍጥረታት ከምን ተገኙ? ከየት መጡ?  የሚታየው ነገር ሁሉ አስገኚ አለው። በራሱ የተገኘ ነገር የለም።

o   አንዳንድ ወገኖች ዓለሙ የተገኘው እንዲሁ ነው የሚሉ አሉ፤ - ተመራማሪዎች።

§  በእግዚአብሔር መኖር የማያምን ጓደኛ የነበረው አንድ የእግዚአብሔር  ሰው  ያን ኢአማኒ ጓደኛውን «ዓለማት ከየት ተገኙ?» ሲለው

የማያምነው ጓደኛም፡- «እንዲሁ ተገኙ» ይለው ነበር።

አንድ ቀን አማኙ በካርቶን እና በወረቀት ቆንጆ ቤት ከሠራ በኋላ  ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠው። በኋላ ከሃዲ ጓደኛው ሲመጣ የቤቱን ሞዴል አይቶ በጣም ተደነቀና ፡- « ከየት አገኘህው?» ሲለው - አማኙ  «እንዲሁ ተገኘ» አለው.. ይሄማ ሊሆን አይችልም  ሲል ያ አማኙ ጓደኛም፡- «አየህ እኔም ፍጥረታት ከየት ተገኙ? » ስልህ እንዲሁ ስትለኝ የነበረውም ሊሆን አይችልም ማለት ነው።

§  የምናየው ነገር ሁሉ ሠሪ ወይም አስገኝ አለው። በራሱ የተገኘ ነገር የለም። ወንበሩ- አናጺ፣ ቤቱ-ግምበኛ… ሁሉም የየራሱ አስገኚ የሆነ ባለሙያ አለው። በአጠቃላይ የዚህ ውብ ተፈጥሮ አስገኝውስ ማን ነው?  ስንል -ፈጣሪ- እንዳለ /እንዳለው እንረዳለን።

. ፍጥረታት እንዴት ተገኙ?

o   አሁንም ተመራማሪዎች የመጀመሪያው ታላቅ ፍንዳታ (Big Bang) ከተከሰተ በኋላ- በሂደት ነገሮች ሁሉ ተገኙ፤ ይላሉ። ግን የመጀመሪያው የታላቅ ፍንዳታ ቁስ ከየት መጣ? ሲባል መልስ የለም።

ከዚያም በኋላ በአዝጋሚ ለውጥ- አንዱ ከአንዱ እየተወጣ.. ተገኙ ይላል።

o   አንድ ጸሐፊ እንዲህ ብሏል፡-  ነገሮች አንዱ ከአንዱ ተገኘ ከተባለ ይህ ማለት እንግዲህ በከተማችን የምናያቸው ታላላቅ ፎቆች፣መንገዶች፣ ድልድዮች የተገኙት፡-  ጥሬ ዕቃዎቹ - ብረቱ፣ ሲሚንቶው ራሳቸውን አዘጋጅተው፣ እንጨቶች ራሳቸውን ጠርበው አስተካክልው፣ ጡቦች በራሳቸው እየተደረደሩ፣ ቆርቆሮው በራሱ እየተመታ፣ እየተጋጠመ ቤቱ ተሠራ የማለት ያህል ነው። ይህ ግን ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው።

o   ይህ ዓለም የተፈጠረ ብቻ ሳይሆን በሥርዓት የተዋቀረ ዓለም ነው። Intelligent design - ግሩም ንድፍ ያረፈበት ድንቅ ተፈጥሮ ማለት ነው።

Thursday, June 8, 2017

እግዚአብሔርን ማወቅ - ክፍል ፭


እግዚአብሔርን ፍለጋ


ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።

ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ። እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን።   የሐዋ ፲፯፣ ፳፮ - ፳፰

፩. እግዚአብሔርን መፈለግ ለምን አስፈለገ?

ü ተፈጠርንበት ዋና ዓላማ በመሆኑ-  እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ፡-

·        የሰውን ወገኖች ከአንድ ፈጠረ - ከአዳምና ከሔዋን። አንድ ጊዜ ፈጠረ፣ በኋላ ብዙ ተባዙ ባለው አምላካዊ ቃል  በመዋለድ የሰው ዘር ይቀጥላል።  

o   …..እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥  ዘፍ ፩፡ ፳፯ - ፳፰

o   አዳምም ለሚስቱ ሔዋን ብሎ ስም አወጣ፥ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና። ዘፍ ፫፣ ፳

·        የምንኖርበትን ዘመን - እና - ስፍራ /ቦታ/ መደበልን።  በየት ዘመን እስከ ስንት ጊዜ፣ በየት ሃገር ከየትኛው ቤተሰብ እንደምንወለድ እድሜና ሥፍራ የመደበልን እግዚአብሔር ነው።

ስለዚህ «አፄ /አቶ እገሌ ያለዘመናቸው የተወለዱ… »  የምንለው ፈጽሞ ስህተት ነው ማለት ነው። 

·        እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረበት ዓላማ እንዲፈልገው  ነው። በሰጠው ነጻነት ተጠቅሞ ፈልጎ፣ አግኝቶ ፣ ወዶ እንዲከተለው እና አብሮት እንዲኖር።

·        እግዚአብሔርን ስለመፈለግ ዳዊት እንዲህ ብሏል፡-

·        …. በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው።

እግዚአብሔርን ፈልጉት ትጸናላችሁም ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ።  መዝ ፻፬/፻፭፣ ፩ - ፬
እግዚአብሔርን የምንፈልገው ለምንድን ነው? ከላይ በጥቅሱ እንዳየነው፡-