Saturday, December 3, 2011

-የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መመሪያዎች



መጽሐፍ ቅዱስ ከላይ ወደ ውስጥ በሚዘልቅ አካሄድ  በ፯ ደረጃዎች እንደሚከፋፈልና ሁሉም በየደረጃው ጥቅምና ዋጋ እንዳለው ባለፈው ጽሑፋችን አይተናል።
ወደዝርዝር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ከማለፋችን በፊት ግን ስለመጽሐፉ ጠባያት አስቀድመን ልናውቃቸው የሚገቡ ፫ ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ የጥናት መመሪያዎች ይባላሉ።  
እምነት፡ ምግባር፡ እና መረጃ ።
፩. እምነት
መጽሐፍ ቅዱስ የታሪክ፡ የፍልስፍና የሳይንስ… መጽሐፍ እንዳልሆነ ከዚህ ቀደም አይተናል። መጽሐፉ ዓለማዊ ሳይሆን መንፈሳዊ የእምነት መጽሐፍ እንደመሆኑ መጠን ልንረዳው የምንችለውም በመንፈሳዊ መንገድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት እና በተግባር ለመተርጎም/ለመኖር የሚፈልግ ማንኛውም ሰው አስቀድሞ በሁለት ነገሮች ማመን አለበት።
በእግዚአብሔርና በኢየሱስ ክርስቶስ፡፡
·         የመጀመሪያው በእግዚአብሔር ማመን - ምሥጢረ-ሥላሴ  ይባላል።  ሁሉን ያስገኘ፡ ለራሱ መገኘት ምክንያት የሌለው፡ ዓለምን የፈጠረና የሚመግብ፡ በሦስት ነገሮች ሦስትነት ያለው፡ (በስም፡ በአካል፡ በግብር) በቀሩት ነገሮች ሁሉ (በመለኮት፡ በአገዛዝ፡ በሕልውና…) አንድ የሆነ ስሙ እግዚአብሔር የሆነ ዘላለማዊ አምላክ አለ ብሎ ማመን።
·         ሁለተኛው በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን-  ምሥጢረ-ሥጋዌ/ነገረ-ድኅነት ይባላል።  ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ በኋለኛው ዘመን (በአዲስ ኪዳን) ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለወንድ ዘር በመወለድ፡ በአጭር ቁመት፡በጠባብ ደረት ተወስኖ ሰው ሆኖ የአዳምንና የሰውን ኃጢአት ዕዳ ለመክፈል በመስቀል ላይ ውሎ ሞቶ የተነሳ፡ ዳግመኛም ለፍርድ የሚመጣ ፍጹም ሰው፡ ፍጹም አምላክ  የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝ መሆኑን መቀበል።  



«ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ አምናችሁም በስሙ ሕይወት  ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።» ዮሐ ፳፡፴፩
አንድ ሰው በነዚህ ካመነ በኋላ  ክርስቲያን ይሆንና፡
- ምሥጢረ-ጥምቀትን ይፈጽማል። «ያመነ የተጠመቀ ይድናል።» ማር ፲፮፡፲፮ 
- ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል ምሥጢረ-ቁርባንን ይፈጽማል። «ሥጋየንም የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው።» ዮሐ ፮፡፭፬።
- በመጨረሻ ሞቶ በመነሳት ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳል። ምሥጢረ-ትንሣኤ ሙታን።  « እነሆ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፡ ሁላቸን አናንቀላፋም፡ ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፡ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።» ፩ቆሮ ፲፭፡ ፶፩-፶፪፡፡
በቤተክርስሪያናችን ትምህርት ከላይ የተጠቀሱት አምስቱ አዕማደ-ምሥጢራት ይባላሉ። ራሱን የቻለ ሰፊ ትንታኔ አላቸው።
እንግዲህ ማንኛውም ሰው እነዚህን መሠረታዊ እምነቶች ተረድቶ  ካልፈጸመ  መጽሐፍ ቅዱስን ሊረዳው ስለማይችል እንደማንኛውም ተራ መጽሐፍ ሊቆጥረው ይችላል።
፪. ምግባር
 እምነት በምግባር (በሥራ) መገለጽ አለበት። ካለበለዚያ፡
«ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።» ያዕ ፪፡፳፮።
መጸሐፍ ቅዱስ ጥናትን በተመለከተ ከአማኙ የሚጠበቁት ምግባራት መጸለይና መታዘዝ ናቸው።
ሀ. ጸሎት
ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት መሰላል እንደሆነ አባቶች ይናገራሉ። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ እግዚአብሔር በዚያ ውስጥ ለኛ ያለውን መልዕክት ለመረዳት በጸሎት መጠየቅ አስፈላጊ ነው።
እግዚአብሔር በቃሉ /በመጽሐፍ ቅዱስ / ያናግረናል። እኛም ተመልሰን ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኘው/የምንነጋገረው በጸሎት ነው።
ለ. መታዘዝ፡- መጽሐፍ ቅዱስን የምናነበው ለግንዛቤ ወይም ለዕውቀት አይደለም። ለሕይወት ነው። ስለዚህ የተረዳነውን ቃል  ወዲያው በተግባር ማዋል- መታዘዝ ይጠበቅብናል።
 «ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።» ያዕ ፩፡፳፪
፫. መረጃ (ዕውቀት)
በመጨረሻ መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ለመረዳት ስለራሱ ስለመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ማወቅ የሚገባን ነገሮች አሉ፡፡
·         መጽሐፉ የተጻፈው  በእስራኤል ሃገር እንደመሆኑ መጠን ሃሳቡን ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ስለእስራኤል ባሕል፡ መልክአ-ምድር፡ ገንዘቦች፡ ወንዞች፡ አባባሎች… ማወቅ አለብን።
·         በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መጻሕፍት ስምና ቅደም-ተከተል፡ የጥሬ ቃላት መፍቻ፡ የጥቅስ አወጣጥ፡ የግርጌ ማስታወሻዎችን፡ ማወቅ አለብን። እነዚህንም የምናገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ማውጫ፡ እንዲሁም ከብሉይ ኪዳን መጨረሻ፡/ ከአዲስ ኪዳን መጀመሪያ ነው።
·         የመጽሐፍ ቅዱስን ዋና ሃሳብ (መልእክት) ማወቅ አለብን። በመጽሐፉ የሚገኙት ታሪኮች፡ ትንቢቶች፡ ትምህርቶች ሁሉ ምንግዜም ከዋናው ሃሳብ ጋር በመነሳት/በመያያዝ ይተረጎማሉ።
·         እያንዳንዱ መጽሐፍት የተጻፉላቸውን ሰዎች ሁኔታ፡ ችግሮች፡ የጸሐፊዎቹን ምክንያት፡ ዓላማ… አስቀድመን መረዳት።
·         የመጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ልዩ የአተረጓጎም ዓይነቶችን/ ትርጉሞችን ማወቅ። እነዚህ ነጠላ ትርጉሞች- ለምሳሌ ከቋንቋ ወደቋንቋ የሚደረጉ እና አንድምታ ትርጉሞች ከማብራሪያና ከምሳሌ ጋር የሚተነተኑ ትርጉሞች ናቸው።
ከለይ የተጠቀሱት የጥናት መመሪያዎች ምን ያህል ተግባራዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው  የምንረዳው ስንጠቀምባቸው ነው። ይሁንና እያንዳንዳቸው  ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ያላቸውን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ በምሳሌ በየተራ በአጭር በአጭሩ እያየን እንሄዳለን።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣዩ ጽሑፋችን ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መመሪያዎች ምሳሌዎችን እናያለን።
 ---------------ይቆየን----------------


No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment