Friday, December 16, 2011

ምሥጢረ-ሥላሴ (ክፍል ፩)


ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የሚያስፈልጉን ጉዳዮች በቅድሚያ በእግዚአብሔርና በክርስቶስ ማመን (ምሥጢረ-ሥላሴና ምሥጢረ-ሥጋዌ)፡ ቀጥሎም መጸለይና ለቃሉ መታዘዝ፡ በመጨረሻም ስለራሱ ስለመጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ልዩ መረጃዎችን ማወቅ እንደሚገባን ባለፈው ጽሑፋችን አይተናል። በዚህ የትምሀርት ክፍል እነዚህን ጉዳዮች በየተራ እንመለከታለን።
፩. ምሥጢረ-ሥላሴ
ሥላሴ የግዕዝ ቃል ሲሆን ሦስትነት ማለት ነው። ሠለሰ-ሦስት አደረገ፡ ይሤለስ፡ ሥሉስ፡ ሥላሴ እያለ ግሱ ይወጣል።
ምሥጢረ-ሥላሴ የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት የምንማርበት ክፍል ነው። እግዚአብሔር በኛ ዕውቀት ልንደርስበት የማንችል የማይመረመር ግሩም ድነቅ አምላክ ነው። ትምህርቱን ምሥጢር ያሰኘው የማይነገር ስለሆነ ሳይሆን የማይመረመር ስለሆነ ነው። ነገረ-እግዚአብሔር የማይመረመር ነው ሲባል በጭራሽ የማናገኘው እርሱም የማያገኘን- የማንገናኝ ነን ማለት አይደለም። ስለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ መረዳት የማንችለው በሁለት ምክንያት ነው።
  በአእምሮ ውስንነትና  በቋንቋ ውስንት ።
- የእኛ አእምሮ (የዕውቀት ደረጃ) እግዚአብሔርን ሊደርስበት ከቶ አይችልም። እንኳን ፈጣሪን- ፍጡራንንና ፍጥረትን መርምረን አልጨረስንም።
- በቋንቋም ብንሄድ ስለእግዚአብሔር ለመግለጽ የሚችል ቃላት የሉንም። እንኳን ስለእግዚአብሔር ለራሳችን ስሜት እንኳ ቃላት የሚያጥረን ጊዜ ብዙ ነው። ቃላት ያጥረኛል የምንልባቸው ብዙ ስሜቶችና ጉዳዮች አሉን።
ስለዚህ እግዚአብሔር እርሱ ስለራሱ የገለጠልንን ያህል፡ እኛም መረዳት የቻልነውን ያህል እንማራለን።
እግዚአብሔር በሦስት ነገሮች -በስም ፡ በአካል፡ በግብር ሦስት የሆነ፡- ። በቀሩት ነገሮች ሁሉ -በመለኮት በአገዛዝ፡ በሕልውና፡ በፈቃድ፡ በመፍጠር፡ በማዳን፡ .   አንድ የሆነ አምላክ ነው። ይህ ሲባል አንድ ሆኖ ቆይቶ ሦስት የሆነ ወይም ሦስት ሆኖ ቆይቶ አንድ የሆነ አይደለም። እግዚአብሔር በአንድ ጊዜ አንድም ሦስትም ነው። አንድነቱ ሦስትነቱን አይጠቀልለውም። ሦስትነቱ አንድነቱን አይከፋፍለውም። አንድና ሦስት ሳይሆን አንድም፡ ሦስትም ነው።



                     ወልድ ማለት ልጅ የማን ልጅ የአብ፡  የስም ሦስትነት፡- አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ። አብ ማለት አባት፡ የማን አባት የወልድ፡  
     መንፈስ ቅዱስ ማለት የሰረጸ፡ ከማን የሰረጸ ከአብ። የሰረጸ ማለት የተገኘ፡ የወጣ ማለት ነው።
የአካል ሦስተነት፡- ለአብ ፍጹም ገጽ፡ ፍጹም መልክ፡ ፍጹም አካል አለው።
                      ለወልድ ፍጹም ገጽ፡ ፍጹም መልክ፡ ፍጹም አካል አለው።
                      ለመንፈስ ቅዱስ ፍጹም ገጽ፡ ፍጹም መልክ፡ ፍጹም አካል አለው።
          ገጽ ማለት ፊት ነው። መልክ ማለት ውበት፡ኅብር፡ ቀለም ነው። አካል ማለት ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍር መላ አቋም ማለት ነው።
የግብር ሦስትነት፡- ግብር ማለት አካላዊ ግብር ነው። የአብ ግብሩ መውለድ፡ ማስረጽ ነው። የወልድ ግብሩ መወለድ ነው። የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መስረጽ (መውጣት፡ መገኘት) ነው። ግብር ሲል ሥራ ወደሚል ከወሰድነው በሌሎች ሥራዎች ዓለምን በመፍጠር፡ በመመገብ፡ በማሳለፍ ወዘተ…. ሥላሴ አንድ ናቸው። በአካላዊ ግብር ማለትም በመውለድና በማስረጽ ብቻ ነው ሦስትነታቸው።
አንድነት፡-  ከላይ ከተጠቀሱት ውጭ በቀሩት ነገሮች ሁሉ ሥላሴ አንድ ናቸው/እግዚአብሔር አንድ ነው። አንድ ከሆኑባቸው ነገሮች ለአብነት አንዱን እናያለን። ሌሎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በሂደት እያየን እንሄዳለን።
በሕልውና፡-አብ፡ ወልድ፡ መንፈስ ቅዱስ በአንድነት አብረው ካሁን ቀደም ነበሩ፡ አሁንም አሉ፡ ወደፊትም ይኖራሉ። አብ ወልድን ወለደ ሲባል ቀድሞ ነበረ፡ ወልድ በኋላ ተገኘ ማለት አይደለም።  በኛ አኗኗር ካየነው አባት ከተገኘ በኋላ ቆይቶ ቆይቶ ልጅ ይወልዳል። ስለዚህ አባት ከልጁ ይበልጣል፡ ይቀድማል፡፡ ይህም የሚሆነው ማነጻጸሪያ ጊዜ ስላለና እኛም በጊዜ ተጽእኖ ሥር ስለሆንን ነው። ለእግዚብሔር ግን እንደዚያ አይደለም። አብ ኖሮ ኖሮ ወልድን የወለደ በኋላም መንፈስ ቅዱስን ያስገኘ አይደለም። እግዚአብሔር በአንድነቱ ከጊዜና ከዘመናት በፊት የነበረ በመሆኑ በጊዜ ተጽእኖ ሥር አይደለም። ጊዜን የፈጠረ ጊዜንም የሚያሳልፍ የዘመናት ባለቤት እርሱ ነው።  
“ወለዶ አብ ለወልዱ ኢይትበሀል ዘ ጊዜ ወበከመዝ መዋዕል ወለዶ። አብ ልጁን ወለደው፡ በዚህ ጊዜ እንዲህ ባለ ዘመንም ወለደው አይባልም። የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ቁ. ፳፬፡ ገጽ ፻፺፬።
ስለዚህ አብ ከወልድ አይበልጥም፡ ከመንፈስ ቅዱስም አይበልጥም። ወልድም ከአብ አያንስም፡ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ና ከወልድ አያንስም። ቋንቋ ስለሚያጥረን ባሉን ቃላቶች እየተጠቀምን የቻልነውን ያህል እንገልጻለን።
ስለ እግዚአብሔር (ሥላሴ) አንድነትና ሦስትነት ቅዳሴ ማርያም በሰፊው የተነትናል፡-
« አኮ ዘንብል አሐዱ ከመ አዳም ቀዳሚ ኩሉ ፍጥረት አላ ሠለስቱ ውእቱ እንዘ አሐዱ ሕላዌ፡
 አኮ ዘንብል ሠለስቱ ከመ አብርሃም ይስሐቅ ወያዕቆብ አላ አሐዱ ውእቱ እንዘ ሠለስቱ ግጻዌ፡፡» ይላል፡
የፍጥረት ቀዳሚ እንደሆነው እንደ አዳም አንድ የምንል አይደለም። አንድ ሲሆን ሦስት ነው እንጂ፡
እንደ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ ሦስት የምንል አይደለም ። ሦስት ሲሆን አንድ ነው እንጂ።»
የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት ለማስረዳት አባቶች በምሳሌ ይናገራሉ። እግዚአብሔርን የሚመስለው ነገር ባይኖርም የኛን የእውቀት ውስንነት ለማገዝ ለማስተማሪያ በምሳሌ ይጠቀማሉ።

ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ለሥላሴ የሚቀርቡ ምሳሌዎችንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችን በቀጣይ እናያለን።

ይቆየን።

1 comment:

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment