Friday, September 30, 2011

የመጽሐፍ ቅዱስ አጻጻፍ


« ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።» ፪ጴጥ ፩፡፳፩
መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈ፡ በ፷፮ቱ በተደረገው ጥልቅ ጥናት እንደተገለጸው 40 በሚሆኑ እርስ በርሳቸው በማይተዋወቁ፡ በተለያየ ባሕልና ቦታ ይኖሩ በነበሩ ሰዎች፡ በ1500 ዘመናት ርቀት የተጻፈ፡ ነገር ግን እርስ በርሱ የማይጋጭ እና አንድ ጭብጥ የያዘ ግሩም ድንቅ መጽሐፍ ነው።
·         መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን ወረቀት፡ እስክርፒቶ፡ የህትመት ማሽን አልነበረም። ነገር ግን በአባይ ወንዝ ዳር ከሚበቅለው ሸምበቆ መሰል ተክል ቅጠል (ፓፒረስ)፡ በድንጋይ፡ ከዚያም ሲሻሻል በብራና ይጻፍ ነበር።
“ ስትመጣ በጢሮአዳ ከአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖሱንና መጻሕፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ… ፪ጢሞ ፬፡፲፫
·         አንድ ገጽ ብራና ለማዘጋጀት በጉ/ከብቱ ታርዶ፡ ቆዳው ተገፎ፡ ጸጉሩ ተላጭቶ፡ ለስልሶ፡ ተዳምጦ….. ከዚያም በኋላ ለመጻፊያ የሚሆነው ቀለም ከተለያዩ ቅጠሎች ተጨምቆ፡ ተበጥብጦ…. ይዘጋጅ ነበር። እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለመጻፍ እንግዲህ ምን ያህል አድካሚ እንደነበር መገመት ይቻላል። ቀላል ምሳሌ ለመውሰድ የብራና ገጾችን እና ቀለሙን ለማዘጋጀት ያለውን ድካም እናቆየውና ለመጻፍ እንኳን ምን ያህል አድካሚ እንደሚሆን 50 ምዕራፎችን በ43 ገጽ የያዘውን ኦሪት ዘፍጥረትን ብቻ እስኪ በወረቀት እና በእስክርፒቶ ገልብጡ ብንባል እንዴት ነው የምንሆነው?
·         መጽሐፍ ቅዱስን የመጀመሪያውን ቅጂ ጸሐፍያኑ ከጻፉት በኋላ ያ አንዱ ቅጂ ለስንት ሰው ይደርሳል? ስለዚህ መገልበጥ ደግሞ አለበት ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ የሚገለብጡ እና የሚተረጉሙ ደግሞ ምን ያህል ድካም ይኖርባቸው?.... እኛ ግን ለመጻፍ/ለመገልበጥ አይደለም ለማንበብ ደክሞናል፡፡…
·         እንግዲህ ወረቀትና የህትመት ማሽን እስከተፈለሰፈበት እስከ 15ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ከ2500 ዓመት በላይ መጽሐፍ ቅዱስ በእጅ እየተገለበጠ ቆይቷል። እስከዚያ ዘመን ድረስ ሰዎች ሁሉ አይሁድም ሆኑ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ አይደለም ለመስማት ወደምኩራብና ወደ ቤተ መቅደስ መሄድ ነበረባቸው። …. ዛሬ ግን ለእኛ እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስን እቤታችን ድረስ አስገብቶልን አናነበውም።……
·         በ1456 ዓ/ም በጀርመን ሃገር የመጀመሪያው የህትመት ማሽን ሲፈለሰፍ መጀመሪያ የታተመው መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ከዚያ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በብዛትና በፍጥነት ለየሰው ማዳረስ ተቻለ።

ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣዩ ጽሁፋችን የመጽሐፍ ቅዱስን አመጣጥ እናያለን።
---------------ይቆየን----------------