በአዲስ ኪዳን
ዳሰሳ ባለፈው በ፫ኛው ጥናታችን የመልእክት ክፍል የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስንና ቀጣዮቹን መልእክታት ዳሰሳ አይተናል። ዛሬ በአዲስ
ኪዳን የመጨረሻ የሆነውን የትንቢት ክፍል ይሄውም የዮሐንስ ራእይን ጠቅለል አድርገን እንመለከታለን። የዮሐንስ ራእይ የመጽሐፍ ቅዱስ
የመጨረሻው ክፍል ሲሆን በአዲስ ኪዳን መጀመሪያ ክርስትና በሐዋርያት በኩል ወደ ዓለም ከተስፋፋ በኋላና የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት
(የክርስቲያኖች ኅብረት) ከተመሠረቱ በኋላ እነርሱን ለማበረታታት፣ በተለያየ ምክንያት ከክርስትና ወደ ኋላ ያሉትንም ለመገሰጽ፣
በዓለም ላይ በክርስቲያኖች የሚደርሰው መከራና ፈተና ፍጻሜ እንደሚኖረው ዲያብሎስም ለመጨረሻ ጊዜ ድል እንደሚደረግ የመሳሰሉ ሃሳቦችን
ይዟአል።
መጽሐፉ የዮሐንስ
ራእይ ቢባልም ራእዩ ከመጽሐፉ መጀመሪያ እንደምንረዳው እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የገለጠለት ሆኖ በመልአክ በኩል ለዮሐንስ
ልኮለት የጻፈው ነው።
« ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር
ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥» ራእ
፩፣፩
መጽሐፉ የአዲስ
ኪዳን ትንቢት እንደመሆኑ መጠን ከብሉይ ኪዳን እንደ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ካሉ አንዳንድ የትንበት መጽሐፍ ጋር ያሉ ጉዳዮችን እያነሳ
ይናገራል። በወቅቱ በሐዋርያት እና በተከታዮቻቸው ትምህርት ለተመሠረቱ የተለያዩ የክርስቲያኖች ኅብረት በተለይም በእስያ ለሚገኙ
፯ አብያተ ክርስቲያናት ማጽናኛ እና ተግሣጽ ሆኖ ሲጻፍ እንደ አጠቃላይ በመጨረሻው ዘመን ለሚገኙ ክርስቲያኖችም ተስፋና ማጽናኛ
ምክሮችን ይዟል። አቀራረቡ ከሌሎች በተለየ በስእላዊ መግለጫዎች የተሞላ ድራማ መሰል ሥነ-ጽሑፍ ነው። ስለመጨረሻው ዘመን ብዙ ትንቢቶችን
እንደያዘ እና ረቂቅ ምሥጢራዊ የአጻጻፍ ስልት እንዳለው ብዙ መምህራን ያስረዳሉ። በዚህም ምክንያት በመጽሐፉ አተረጓጎም ላይ ብዙ
የተለያዩ ሃሳቦች ይቀርባሉ።
ዮሐንስ ቀደም
ሲል በወንጌሉ ኢየሱስ ክርስቶስን «የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር
በግ» ብሎ ካስተዋወቀ በኋላ አሁን ደግሞ በራእዩ የታረደው በግ ይለዋል። (ዮሐ ፩፣፳፱ ፡ ራእ ፭፣፲፪)። ሞትን ድል አድርጎ
ከተነሳ በኋላም ድል የነሳው የዳዊት ስር የይሁዳ አንበሳ ተብሏል። ለዓለም ሁሉ ኃጢአት ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ የዋለው ስለ ሁላችን
የሞተው የታረደው በግ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በትንቢተ ኢሳይያስ በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ የተባለለት በዚህ መጽሐፍ የድል አድራጊነቱን
ውጤት የበጉ ደም፣ የበጉ የሕይወት መጽሐፍ፣የበጉ ሠርግ፣ የበጉ ሙሽራ፣ የበጉ ዙፋን ወዘተ… በማለት በተለያየ መልክ ይገልጻል።