Wednesday, October 16, 2013

አዲስ ኪዳን - የታሪክ ክፍል (የሐዋርያት ሥራ)

ባለፈው ክፍል በጀመርነው የአዲስ ኪዳን ዳሰሳ የወንጌል ክፍልን ማየታችን ይታወሳል። በዚህም ወንጌል ማለት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ ሕይወት ከልደት እስከ ሞትና ትንሣኤ በአራቱ ወንጌላውያን የተዘገበው የመጽሐፍ ቅዱስ የምሥራች ቃል መሆኑን ተመልከተናል። በመቀጠል ይህ ወንጌል በሐዋርያት በኩል እንዴት ወደ ዓለም መሰራጨት እንደጀመረ በአዲስ ኪዳን የታሪክ ክፍል በሚባለው በሐዋርያት ሥራ ተዘግቦ የምናገኘው ሲሆን ለዛሬ ይህን እናያለን።
የሐዋርያት ሥራ ስሙ እንደሚነግረን ሐዋርያት የሠሩት ወንጌል የማስፋፋት ሥራ ነው። ሐዋርያት በአንድነት መንፈስ ለአንድ የተቀደሰ ዓላማ በጽናት እንደሠሩ እናያለን። ይህ ኅብረታቸው ቤተ ክርስቲያን ይባላል። የቤተክርስቲያን ቀዳሚ ትርጉም የክርስቲያኖች ኅብረት /አንድነት/ ነው። መጽሐፉ በሐዋርያት የተመሠረተችው የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን (ኅብረት) የነበራትን የአገልግሎት ትጋት ያሳየናል። የወንጌል ስብከትና መስፋፋት፣ ጸሎት፣ የጋራ የፍቅር ማዕድ (አጋፔ)፣ ሃብትና ንብረታቸውን በጋራ መጠቀም፣ የተቸገሩትን መርዳት፣ ድውያንን መፈወስ፣ የሥራ ክፍፍል /አስተዳደራዊ መዋቅር፣ በመሳሰሉት መንፈሳዊ አገልግሎቶች  እናያለን።
ከዚህም ጋር ከነበራቸው ጠንካራ አገልገሎት ጎን ለጎን ይደርስባቸው የነበሩ ፈተናዎች ነበሩ። ከአይሁድ የሚደርስባቸው ስደት፣ እንደ ሐናንያና ሰጲራ ካሉ ራስ ወዳዶች የሚመጣው ስስት፣ ከአይሁድ ጋር ስለነበራቸው የእምነት ግጭት፣ በውስጥ አስተዳደራዊና ቀኖናዊ ልዩነቶች ወዘተ የመሳሰሉ… ተግዳሮቶችን እንዳስተናገዱ ይታያል። ሐዋርያቱ ከፍተኛ የሆነ የወንጌል አገልግሎት ሥራ የሠሩት በከፍተኛ ተግዳሮት ውስጥ እያለፉ ስለነበር ምንጊዜም ዛሬም ከተሳካ አገልግሎት ጋር የከረረ ተቃውሞ የማይቀር መሆኑን እንገነዘባለን።


ወንጌላቱ የክርስቶስን ምድራዊ ሕይወትና አገልግሎት ከልደቱ - ሞቱና ትንሣኤው መዘገባቸውን በመዝገቦቻቸው በአጭሩ እንዳየነው የሐዋርያት ሥራ ከክርስቶስ ዕርገት ጀምሮ የሐዋርያቱን የቅዱስ ጴጥሮስንና የቅዱስ ጳውሎስን አገልግሎቶች ከተረከልን በኋላ ጳውሎስ በሮም እስከታሰረበት ከዚያም በቤቱ እስከሚሰብክበት ጊዜ ድረስ ያለውን ታሪካዊ ሂደት ይናገራል። በዚህም ምክንያት በቀጣይ ለሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል -ለመልዕክቶች- ዋና ታሪካዊ ዳራ ሆኖ ይገኛል።
የሐዋርያት ሥራን የጻፈው የሉቃስ ወንጌልን የጻፈው ወንጌላዊው ሉቃስ እንደሆነ ይታመናል። ሁለቱም መጻሕፍት ለአንድ ግለሰብ - ለቴዎፍሎስ- መጻፋቸውን በመግቢያቸው ማየት ይቻላል። በሉቃስ ወንጌል   ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉት፥ በዚያ ስለ ተፈጸመው ስለኢየሱስ ክርስቶስ ነገር በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትሎ በየተራው እንደጻፈው፡ በሐዋርያት ሥራ ደግሞ ያው ኢየሱስ የመረጣቸውን ሐዋርያትን በመንፈስ ቅዱስ ካዘዛቸው በኋላ ስለተከናወነው ነገር ይተርካል። (ሉቃ ፩፣፩ የሐዋ ፩፣፩)። ስለዚህ ወንጌል ሥጋን የለበሰው ወልድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ሲሆን የሐዋርያት ሥራ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው ማለት ይቻላል።
«እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።» ሉቃ ፳፬፣፵፱። «ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥…. ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ። » የሐዋ ፩፣፰ ባላቸው መሠረት ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የክርቶስን ወንጌል ማስፋፋት ሥራ /ምስክርነት/ ቀጥለዋል።
የመጽሐፉ መሪ ቃል በምዕራፍ ፩ ቁጥር ፰ ላይ ክርስቶስ የተናገረው ኃይለ ቃል እንደሆነ ብዙ መምህራን ያስረዳሉ። «ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።»
በዚህ መነሻነት ክርስትናው፡-
- መጀመሪያ በእስራኤል ዋና ከተማ በኢየሩሳሌም
- ቀጥሎም በሃገሩ በይሁዳ
- በመቀጠል በጎረቤት ሃገር በሰማርያ
-በመጨረሻ እስከ ምድር ዳር ድረስ እየተስፋፋ እንደሚሄድ
ክርስቶስ ባዘዘው መሠረት ሲፈጸም፡ ዛሬም እየተፈጸመ (መፈጸም እንዳለበት) እናያለን። ስለዚህ አንድ የክርስቶስ ተከታይ ነኝ የሚል ክርስቲያን መጀመሪያ ለራሱ፣ ቀጥሎ ለቤተሰቡ፣ ከዚያም ለጎረቤቱ እያለ ወደ ውጭ እስከ ምድር ዳር (ሌላ ሃገር) ድረስ ወንጌሉን የመመስከር ኃላፊነት እንዳለበት ያሳየናል። ምክንያቱም «መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ» ሮሜ ፲፣፲፭ በሌላም ቦታ ቅዱስ ጳውሎስ «ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ።» ይላል፤ ፩ቆሮ ፱፣፲፮። የሐዋርያትን ፈለግ ተከትለን ወንጌልን ባንሰብክ ወዮታ አለብን።
የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን በአገልጋዮቹ መሠረት ብናየው ከምዕራፍ ፩ - ፲፪ የጴጥሮስ፣ ከምዕራፍ ፲፫-፳፰  የጳውሎስ አገልግሎቶች ተብሎ ከሁለት መክፈል ይቻላል። በዚሁ አንጻር አብዛኛውን የያዘው የአሕዛብ ሐዋርያ በመባል የታወቀው ጳውሎስ ከኢየሩሳሌም ውጭ የተለያዩ ሐዋርያዊ ጉዞዎችን በማድረግ ቤተ ክርስቲያንን ያስፋፋ ሲሆን የሰበከላቸውን አብያተ ክርስቲያናት ለማጽናት ደግሞ በርቀት ሆኖ ደብዳቤ (መልዕክት) ይልክላቸው ነበር። በዚህም ምክንያት ፲፬ መልዕክቶችን በመጻፍ የአዲስ ኪዳንን የመልእክት ክፍል ሰፊውን ድርሻ ይይዛል።
በቀጣይ በአዲስ ኪዳን በሥነ ጽሑፋዊ አከፋፈል ፫ኛ የሆነውን የመልዕክት ክፍል አጠቃላይ ዳሰሳ እናያለን።

ይቆየን።

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment