Saturday, November 9, 2013

አዲስ ኪዳን - የመልእክት ክፍል

ባለፈው ጥናታችን በአዲስ ኪዳን የታሪክ ክፍል የተባለውን የሐዋርያት ሥራን አጠቃላይ ዳሰሳ አይተናል። ዛሬ በመቀጠል የአዲስ ኪዳን ፫ኛ ክፍል የሆነውን የመልእክታት አጠቃላይ ዳሰሳ እናያለን። የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የተቀመጡት በታሪካዊ ፍሰታቸው ቅደም ተከተል እንደመሆኑ መጠን በቅድሚያ በወንጌል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ከልደት እስከ ሞትና ትንሣኤ የፈጸመውን የቤዛነት ሥራ፡ በመቀጠል ተከታዮቹ የነበሩት ሐዋርያት ይህን ወንጌል ወደ ዓለም ለማዳረስ ቤተ ክርስቲያንን በመመሥረት የፈጸሙት ሥራ በተለይ የጴጥሮስና የጳውሎስ ተልዕኮና ስብከቶች በሐዋርያት ሥራ ተዘግቧል። በማስከተል እነዚሁ ሐዋርያት የመሰረቷቸውን አብያተ ክርስቲያናት /የክርስቲያኖች ኅብረት/ ለማጠናከር በሩቅ ሆነው ደብዳቤ /መልእክት/ በመጻፍ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ያሳድጓቸው ነበር።
የመልእክት ክፍል ልዩ መልእክታትና አጠቃላይ መልእክታት ተብለው በሁለት ሊከፈሉ ይችላል።  ልዩ መልእክታት የሚባሉት ሰፊውን ክፍል የሚይዙት የጳውሎስ መልእክታት ሲሆኑ ከሮሜ እስከ ዕብራውያን ያሉት ፲፬ መልእክታት ናቸው፤ ልዩ ያሰኛቸውም በወቅቱ ለታወቁ አብያተ ክርስቲያናት (ኅብረቶች) እና ግለሰቦች በተወሰኑ ርዕሰ ጉዳዮች ስለጻፈላቸው ነው። /የዕብራውያን መልእክት የጳውሎስ ይሁን አይሁን በመጽሐፍ ቅዱስ መምህራን አከራካሪ ጉዳይ ነው። አጻጻፉ ከሌሎች መልእክታት ይለያል።/ አጠቃላይ መልእክታት የሚባሉት ጌታ በተለያዩ ጉዳዮች ከሌሎች ለይቶ ሲያቀርባቸው የነበሩት የ፫ቱ የጴጥሮስ፣ የዮሐንስ፣ የያዕቆብ እና የይሁዳ በጠቅላላ ፮ መልእክታት ሲሆኑ እነዚህ መልእክታት ጠቅለል ያለ ጉዳይ የያዙ እና በወቅቱ ለሁሉም አማኞች የተጻፉ ነበሩ። ይሁንና ሁሉም መልእከታት ዛሬ እግዚአብሔር ለኛ የሚያስተላልፋቸውን ጉዳዮች የያዙ መሆናቸውን ወደፊት በጥናታችን በየተራና በሰፊው  የምናየው ይሆናል።


 እኛ ደብዳቤ በምንጽፍበት ጊዜ ቅርጹ በመጀመሪያ የተቀባዩን ሰው ስም እንጠቅሳለን።… ይድረስ ለውድ ወንድሜ….. በማለት፤ ከዚያም ሰላምታችን በማስከተል ወደ ዝርዝር ጉዳዩ ገብተን በመጨረሻ ለእገሌ ሰላምታ አቅርብልኝ፣ እገሌ ሰላም ብሎሃል ብለን የላኪውን /የራሳችንን/ ስም አስፍረን እንዘጋለን።…. ያንተው/ውድ ወንድምህ ….በማለት። በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኙ የጥንት ደብዳቤዎች ሲጻፉ ቅርጻቸው ከእኛ ከአሁኑ ትንሽ ለየት ይላል። እነዚህ በቅድሚያ የጸሐፊውን ስም ቀጥሎ የተቀባዮችን ስም ይጠቅሳሉ።በኋላ ሰላምታቸውን ያስከትሉና ወደ ርእሰ ጉዳዩ ይገባሉ። ለምሳሌ፡-
-         ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ጳውሎስ….በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ በሮሜ ላላችሁት ሁሉ፥ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ሮሜ ፩፣፩ና ፯።
-         የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፥….በጳንጦስና በገላትያ በቀጰዶቅያም በእስያም በቢታንያም ለተበተኑ መጻተኞች፤ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። ፩ጴጥ ፩፣ ፩ና፪
-         የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን። ያዕ ፩፣፩
ደብዳቤያቸውን ሲቋጩ ሰላምታ የሚያቀርቡላቸውንና ያቀረቡላቸውን ወገኖች በመጥቀስ በመዝጊያ ሰላምታና በቡራኬ ይጨርሳሉ። ለምሳሌ
-         ለቅዱሳን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰላምታ አቅርቡ። ከእኔ ጋር ያሉቱ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ቅዱሳን ሁሉ ይልቁንም ከቄሣር ቤት የሆኑቱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። ፊልጵ ፬፣፳፩-፳፫
-         ሰላም ለአንተ ይሁን። ወዳጆች ሰላምታ ያቀርቡልሃል። ወዳጆችን በየስማቸው እየጠራህ ሰላምታ አቅርብልኝ።  ፫ዮሐ ፩፣፲፭።
በመልእክቶች በሙሉ ማለት ይቻላል በመግቢያና በመዝጊያ በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ ሁለት ቃላት አሉ። ጸጋና ሰላም። እነዚህ በመደጋገማቸው ወሳኝ ጉዳዮችን እንደያዙ እንረዳለን። ጸጋ የምንለው ነጻ የሆነው የእግዚአብሔር ስጦታ ወይም ቸርነቱ ነው። ይሄውም ከመፈጠራችን ጀምሮ፡ መዳናችን፣ የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን፣ በኑሮአችንም የዝናብ መምጣት፣ የፀሐይ መውጣት… ወዘተ የሚከናወንበት ከእኛ ሳይሆን ከራሱ የሆነ የእግዚአብሔርን ቸርነት የሚያሳይ ነው። «በከመ ምሕረትከ አምላክን ወአኮ በከመ አበሳነ፤ እንደቸርነትህ እንጂ እንደበደላችን አይሁን» እንዲል በቅዳሴ። ሰላም ደግሞ ጸጋን ተከትሎ የምናገኘው መረጋጋት እና እረፍት ነው። ይሄውም ዙርያው ቢታወክ የማይታወክ፣ ከውጭ ሳይሆን ከውስጥ የሚመነጭ ከሰላም አለቃ፣ ከሰላም ባለቤት ከኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ የሚገኝ ነው። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ኤፌ ፪፣፲፬። ስለዚህ መልእክቶቻችን ሁሉ ጸጋውንና ሰላምን የሚሰብኩ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ከመልእክታቶች መግቢያና መዝጊያ እንማራለን። የመልእከታቱም ዋና ዓላማ እነዚህ ናቸውና።
መልእክቶች በአብዛኛው የሚያተኩሩት በክርስቶስ ያመኑ ክርስቲያኖች ከዳኑ በኋላ ሊከተሏቸው ስለሚገቡ የሥነ ምግባር ትምህርቶች፣ የኑሮ መመሪያዎች፣ ስለሐሰት ትምህርቶች ጥንቃቄ፣ በጾም በጸሎት ስለመትጋት፣ በፍቅር ስለመኖር፣ ስለአንድነት፣ ስለክርስቶስ ማንነት የጠለቁ ትምህርቶች (ስለመለኮቱ፣ ስለትንሣኤ ሙታን፣ ስለዳግም ምጽአት… ) ስለመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችና ፎሬዎች….የመሳሰሉ ጉዳዮችን ያነሳሉ። በተለይ የጳውሎስ መልእክት ስለመዳንና ካስተማራቸው ወገኖች በሚቀርቡለት ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን መልስ ለመስጠት የጻፋቸው ናቸው፤ ለምሳሌ ስለኃጢአት፣ ስለጽድቅ፣ ስለሕግ፣ ስለጋብቻ፣ ስለመንፈሳዊ ስጦታ፣ ስለመንፈሳዊ ውጊያ፣ ስለወንዶችና ሴቶች ሚና፣ ስለክርስቶስ ምጽአት፣ ስለቤተክርስቲያን (የክርስቲያኖች ኅብረት) ወዘተ የመሳሰሉ በርካታ የሥነ መለኮትና የሥነ ምግባር አስተምህሮዎችን በሰፊው ጽፎአል።
መልእክታቱ ስነጽሑፋዊ ይዘታቸው ትረካ ወይም ቅኔያዊ ስላልሆነ ሃሳባቸው ቀጥተኛና ድብቅ የሆነ ምሥጢር የሌለው ነው። ስለሆነም እንዲህ አድርጉ፣ እንዲህ አታድርጉ የሚሉ በቀጥታ አንብበን የምንፈጽማቸው ዝርዝር ምክሮች ናቸው እንጂ ሰምና ወርቅ የያዙ ስውር ነገር የላቸውም። ለዚያ ነው ብዙ አንባቢያንና መምህራን ከመልእክታት በመጥቀስ ማመርና ማስተማር የሚቀላቸው። ከእነዚህ የተወሱነትን በመጥቀስ የዚህን ክፍል ጥናታችን እንጨርሳለን።
-      የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፥ መርቁ እንጂ አትርገሙ።…ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።…ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።  ሮሜ ፲፪፣ ፲፬፡፲፰፡፳፩
-      ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።   ፩ተሰ ፭፣ ፲፮-፲፰
-      የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።  ፩ጴጥ ፪፣፳፩
-      ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል። እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። ፩ዮሐ ፬፣፲፭-፲፯።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣይ የአዲስ ኪዳን የመጨረሻ ክፍል የሆነውን የትንቢት ክፍል /የዮሐንስ ራእይ/ አጠቃላይ ዳሰሳ እናያለን።

ይቆየን።

1 comment:

  1. kala hiwot yasamlin rageme edemana tena yestilen

    ReplyDelete

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment