Tuesday, October 25, 2011

የመጽሐፍ ቅዱስ ሁለቱ ዋና ክፍሎች ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን


መጽሐፍ ቅዱስ በአጠቃላይ ይዘቱ ስለ እግዚአብሔር ማንነትና ተግባራት እንዲሁም ከሰዎች ምን እንደሚፈልግ የሚናገር መሆኑን እና ከዓለም መፈጠር እስከ ዓለም ማለፍ ያሉ ክስተቶችን እንደሚያካትት ባለፈው ጽሑፋችን አይተናል። ይህ ታላቅ መጽሐፍ ሁለት ታላላቅ ክፍሎችን የያዘ ነው። ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን።

የኪዳናቱ ስያሜ
ብሉይ- ማለት አሮጌ/ያረጀ/የቆየ።  አዲስ - ማለት አዲስ  ነው።
ኪዳን- ማለት ውል / ስምምነት ማለት ነው።
ስለዚህ ብሉይ ኪዳን- የቆየ ውል ስምምነት/ አዲስ ኪዳን - አዲስ ውል/ስምምነት ማለት ነው። እግዚአብሔር ሁልጊዜም ከወዳጆቹ ጋር ያለው ግንኙነት በቃል ኪዳን ላይ የተመሠረተ ነው። ከኖኅ፡ ከአብርሃም… ጋር ያደረጋቸውን ቃል ኪዳኖች ያስተውሏል።
ብሉይ ኪዳን ብሉይ ኪዳን የሚለውን ስያሜ ያገኘው እግዚአብሔር ከመረጣቸው ሕዝብ ከእስራኤላውያን ጋር በሙሴ በኩል ባደረገው ቃል-ኪዳን  ነው። ቃል ኪዳኑም የተመሠረተው በእንስሳት ደም ነው።
«… የቃል ኪዳኑንም መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው። እነርሱም፡- እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን፡ እንታዘዛለንም አሉ። ሙሴም ደሙን ወስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው፡- በዚህ ቃል ሁሉ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ያደረገው የቃል ኪዳኑ ደም እነሆ አለ።» ዘጸ ፳፬፡ ፩-፰
ስለዚህ ብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር ያደረገው ስምምነት ነው።


አዲስ ኪዳን አዲስ ኪዳን የሚለውን ስያሜ ያገኘው እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ሐሙስ ማታ የማዳኑን ሥራ ለመፈጸም የሚከፍለውን የሕይወት መሥዋዕትነት በተናገረበት ክፍል  መሠረት ነው። ቃል ኪዳኑ የተመሠረተው በራሱ ደም ነው።
«…እንዲህም አለ፡- ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ። ስለብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።» ማቴ ፳፮፡፳፰
« እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንስቶ እንዲህ አለ፡- ይህ ጽዋ ስለእናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው።» ሉቃ ፳፪፡፳
ስለዚህ አዲስ ኪዳን እግዚአብሔር በልጁ በክርስቶስ ከክርስቲያኖች/ከሚያምኑት ጋር ያደረገው/የሚያደርገው ስምምነት ነው።
ብሉይ ኪዳንን ብሉይ (አሮጌ፡ ያረጀ) ያሰኘው አዲስ ኪዳን ነው። ብሉይ ኪዳን በዘመኑ  ብሉይ (ያረጀ) አልነበረም።
«ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር። እርሱም እየነቀፈ ይላቸዋልና፡- እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል።… አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል።» ዕብ ፰፡፯-፲፫ ኤር ፴፩፡፴፩-፴፬
ስለዚህ አዲስ ኪዳን በመምጣቱ የመጀመሪያው ኪዳን- ብሉይ ኪዳን (የቆየ፡ ያረጀ) ውል /ስምምነት ተባለ። አዲሱ ኪዳን ከብሉይ ኪዳን በብዙ መስፈርቶች ይበልጣል፡ ይሻላል። ሁለቱን ኪዳናት በማነጻጸር ማየት ይቻላል።
የሁለቱ ኪዳናት ንጽጽር በአጠቃላይ ይዘታቸው
በአጠቃላይና በአብዛኛው ይዘታቸው ሁለቱ ኪዳናት ሲነጻጸሩ፡-
ብሉይ ኪዳን በዓለም መፈጠር ይጀምራል።
          አዲስ ኪዳን በዓለም መዳን ይጀምራል።
ብሉይ ኪዳን  በእንስሳት ደም ተመስርቷል።
                   አዲስ ኪዳን በክርስቶስ ደም ተመስርቷል።
ብሉይ ኪዳን ይወርዳል ይወለዳል ይላል-- ወልድን
          አዲስ ኪዳን ይወርዳል ይፈርዳል ይላል-- ክርስቶስን
ብሉይ ኪዳን በክርስቶስ ልደት ተጠናቋል።
          አዲስ ኪዳን በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ይጠናቀቃል።
          /የኪዳኑ ውጤት ግን እስከ ዘላለም ይቀጥላል።/
ብሉይ ኪዳን- አንድ አምላክ እንዳለ ይናገራል
አዲስ ኪዳን- አንድ አዳኝ እንዳለ ይናገራል
ብሉይ ኪዳን ስለ አንድ ሕዝብ ይናገራል-- ስለ እስራኤላውያን
          አዲስ ኪዳን - ስለአንድ ሰው ይናገራል-- ስለ ክርስቶስ
ብሉይ ኪዳን  « እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» ይላል።
          አዲስ ኪዳን « እኔ እላችኋለሁ።» ብሎ ቀጥታ ይናገራል።
ብሉይ ኪዳን ለእስራኤላውያን የተሰጠ-ብሔራዊ ውል ነው።
          አዲስ ኪዳን ለመላው ዓለም የተሰጠ-ዓለም አቀፋዊ ውል ነው።
ብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚብሔር በፍርዱ ይታያል
/ጠላቶችን፡ ሲያጠቃ፡ ድል ሲያደርግ…/
          አዲስ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር በፍቅሩ ይታያል
/ጠላትህ ውደድ ሲል፡ ለጠላቶቹ ሲጸልይ…/
ብሉይ ኪዳን በአዳም ኃጢአት ሰዎችን ወደሞት ወስዷል።
          አዲስ ኪዳን በክርስቶስ ሞት ሰዎችን ወደ ሕይወት ይወስዳል።
ብሉይ ኪዳን ሰው ለእግዚአብሔር የሚያደርገው ነው (ሕግ)።
          አዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ለሰው ያደረገው ነው (ጸጋ)።
“ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፡ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።” ዮሐ ፩፡፲፯
·  ብሉይ ኪዳን እንደ ጥላ ነው። አካሉ አዲስ ኪዳን ነው። ጥላ እዚህ ከታየ  አካል እዚያ እንደቆመ ያሳያል።
·   ብሉይ ኪዳን የአዲስ ኪዳን መነሻ ነው። አዲስ ኪዳን የብሉይ ኪዳን መድረሻ ነው።
· ብሉይ ኪዳን ና አዲስ ኪዳን ተከታታይ ናቸው። ተቀዋዋሚ/ተተካኪ አይደሉም።
·  ብሉይ ኪዳን ያለ አዲስ ኪዳን ፍጻሜ የሌለው ጅማሬ ነው።
·   አዲስ ኪዳን ያለ ብሉይ ኪዳን ጅማሬው ያልታወቀ ፍጻሜ ነው።
ስለዚህ ሁለቱም ኪዳናት ያስፈልጋሉ። ሁለቱንም እኩል ትኩረት ሰጥተን እናነባቸዋለን። እናጠናቸዋለን። እንጠቀምባቸዋለን። አካሄዳችን  ግን ምንጊዜም ከብሉይ ኪዳን ወደ አዲስ ኪዳን ነው። ከመጀመሪያው ወደ መጨረሻው። ከጥላው ወደ አካሉ። ከትንቢቱ ወደ ፍጻሜው።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣዩ ጽሑፋችን የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳንን አከፋፈል እናያለን።
 ---------------ይቆየን----------------

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment