Sunday, May 13, 2012

ለቃሉ መታዘዝ

Lekalu Metazez, read in pdf here
ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በዋናነት የሚያስፈልጉንን እግዚአብሔርንና ክርስቶስን ማወቅ በምሥጢረ-ሥላሴና በምሥጢረ-ሥጋዌ ፣ እንዲሁም ጸሎት የሚሉትን ርእሶች ባለፉት ተከታታይ ትምህርታችን ማየታችን ይታወሳል።  ቀጣዩ ዋና አስፈላጊ ጉዳይ ለቃሉ መታዘዝ የሚለው ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው፡ ለታሪክ፡ለምርምር፡ ለጠቅላላ ዕውቀት፡ ለግንዛቤ፡ ወይም ለመረጃ አይደለም። የተጻፈበት ቀዳሚ ዓላማ ለሕይወት ነው። ቃሉ በሁለት ወገን እንደተሳለ ሰይፍ ላመኑበት መዳንን ላላመኑት ደግሞ ፍርድን የሚያስከትል  እንዲሁም ተናጋሪውንም አድማጩንም የሚነካ ኃይል ያለው፡ እና የሚሰራ ነው። የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። ኤፌ ፮፡፲፯
የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም  ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ ዕብ ፬፡፲፪
መጽሐፍ ቅዱስን መታዘዝ አለብን ስንል መጽሐፉ ከዳር እስከ ዳር ይህን አድርግ ይህን አታድርግ በሚሉ ትእዛዛት የተሞላ መጽሐፍ ነው ማለታችን አይደለም። እግዚአብሔር እንድንታዘዘው የሚፈልገውን ሃሳብ በቃሉ ውስጥ በተለያየ መንገድ አስቀምጧል። ይህንንም ማስተዋል የኛ ድርሻ ይሆናል።
« እግዚአብሔር በአንድ መንገድ በሌላም ይናገራል ሰው ግን አያስተውለውም።» ኢዮ ፴፫፥፲፬፤
እግዚአብሔር ከሚያስተምርባቸው መንገዶች የሚከተሉት ዋናዎቹ ናቸው።




፩. በቀጥተኛ ትዕዛዝ
መጽሐፍ ቅዱስ አድርግ/አታድርግ የሚሉ ቀጥተኛ ትእዛዛት አሉት፤ ለምሳሌ እንደ አሠርቱ ቃላት እና ትእዛዛተ-ወንጌል፤ እነዚህንም በቀጥታ መፈጸም ይጠበቅብናል።
«አትግደል፤ አትስረቅ፤ አታመንዝር…. በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ አትጨነቁ፤ ጽድቁን ፈልጉ።…» ዘጸ ፳፤ ማቴ ፮።
፪. በምክር መልክ
በቅኔ እና በጥበብ መጻሕፍት ውስጥ በምሳሌ፡ በምስጋና፡ በግጥም፡ በጸሎት መልክ በተጻፉት በምክር ያስተምራል። እነዚህም በመከራ ጊዜ ድጋፍ፡ መጽናኛ የሚሆኑ ኃይል ያላቸው ቃላት ናቸው።
            «እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው የሚያስፈራኝ ማን ነው? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው የሚያስደነግጠኝ ማን ነው?» መዝ ፳፯፥፩
፫. በሰዎች ታሪክ
ደካማም ይሁኑ ብርቱ፡ ከድካማቸው እንድንማር፡ ብርታታቸውን እንድንከተል በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ታሪካቸው የተጻፈላቸው ሰዎች ሁሉ ምንጊዜም ለኛ የሚያስተምሩት ነገር  አለ። ለምሳሌ አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅ ለመባል የበቃው በእምነት ባሳየው መታዘዝ በመሆኑ እኛም እንደ አብርሃም በእምነት እግዚአብሔርን ብንታዘዝ የበረከቱ ተካፋዮች እንደምንሆን እግዚአብሔር ተናግሯል።
« መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ። በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ። » ገላ ፫፣፰
፬. በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዚች ምድር የመጣው አንደኛ ለቤዛነት (ዓለምን ሁሉ ለማዳን) ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ለአርአያነት / በኑሮአችን እንድንመስለው በተግባር ለማስተማር ነው። ከልደቱ እስከ ሞቱ መላው የክርስቶስ ሕይወቱ ለእኛ አስተማሪ ነው።
« የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። » ፩ ጴጥ ፪፣፳፩።
ኢየሱስ ክርስቶስ በምድራዊ ሕይወት ዘመኑ ሁሉ በመታዘዝ ኖሮአል። እስከ ፴ ዓመቱ ድረስ ለወላጅ እናቱ ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም እና ለአሳዳጊ አባቱ ለዮሴፍ ሲታዘዝ እንደኖረ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክርልናል።
« ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር። » ሉቃ ፪፣፶፩።
ልጆች ለወላጆቻቸው እንዲታዘዙ መጀመሪያ በቃል በ፲ቱ ትዕዛዛት በኋላም ሰው ሆኖ በተግባር እየታዘዘ  አስተማረን - የሕይወት መምህር ኢየሱስ ክርሰቶስ። ይህን በማስታወስ ቅዱስ ጳውሎስ ልጆች ለወላጆች እንዲታዘዙ ይመክራል።
« ልጆች ሆይ፥ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፥ ይህ የሚገባ ነውና። መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት።» ኤፌ ፮፣፩
ለወላጅ መታዘዝ ለጌታ መታዘዝ ማለት ነው። አስቀድመን ለሥጋ አባት እና እናት ቀጥሎም ለሰማያዊው አባት በሕይወት መታዘዝ ይኖርብናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ከ፴ ዓመት በኋላ ለሰማያዊው አባቱ እየታዘዘ ኖረ፡ እስከ መስቀል ሞት ድረስ።
«…በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። » ፊልጵ ፪፣፰።
የአዳም አለመታዘዝ ለሰዎች ሁሉ ሞትን እንዳመጣ የክርስቶስ መታዘዝ ደግሞ ሕይወትን አስገኝቷል።
በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።» ሮሜ ፭፣ ፲፱።
መታዘዝ የበረከት ብቻ ሳይሆን የሕይወትም ጉዳይ ነው። ክርስቶስ እንደታዘዘ የሕይወትንም መንገድ እንዳመጣ እኛም በእርሱ በማመን፡ እምነታችንንም በመልካም ሥራ በመግለጽ ስንታዘዝ የዘላላም ሕይወትን እናገኛለን።
ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስን መጀመሪያ በእግር ቀጥሎም በግብር ተከተሉት ሲባል ሕይወታቸው በሙሉ እርሱን የሚመስል ሆኖ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ኖሩ ማለት ነው። እኛም በክርስቶስ በስሙ ተጠርተን ክርስቲያኖች (የክርስቶስ) ስንባል ሕይወታችንም እርሱን የሚመስል ሊሆን ይገባዋል ማለት ነው።
ለእግዚአብሔር ከምናቀርብለት ከየትኛውም መሥዋዕታችን ይልቅ ለእግዚአብሔር እንደመታዘዝ ያለ ነገር የለም።  
በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል።  ፩ሳሙ ፲፭፣፳፪።
በብሉይ ኪዳን ለእግዚአብሔር ይቀርብ የነበረው መሥዋዕት የአውራ በግ፡ ዋኖስ፡…. ነበር። በሐዲስ ኪዳን እነዚህን አናቀርብም፤ የቀረበ አንድ መሥዋዕት አለ። እርሱም የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንግዲህ እኛ የምናቀርበው መሥዋዕት ምስጋና ነው። ጸሎትም ወደ እግዚአብሔር እናደርሳለን። ምጽዋት በእግዚአብሔር ስም ለተቸገሩት እንሰጣለን። ወደ እግዚአብሔር ከሚደርሱት ምስጋና፡ ጸሎት፡ ጾም፡ ምጽዋት….ከእነዚህ ሁሉ በላይ/በፊት ለእግዚአብሔር መታዘዝ እንደሚቀድም ቃሉ ያስተምረናል።
እንግዲህ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘው የእግዚአብሔር ቃል እያንዳንዳችን አድራሻ ያደረገ የሰማያዊ አባታችን መልእክት ስለሆነ በእምነት ስንቀበለው፡ በተግባርም ስንታዘዘው ያን ጊዜ የበረከቱ ተካፋዮች እንሆናለን። የእግዚአብሔር ቃል ከወተት እስከ አጥንት በተለያየ ደረጃ የሚገኝ በመሆኑ እኛም በመጀመሪያ በመንፈስ ሕጻናት ሆነን የቃሉን ወተት እየተመገብን በእርሱ ስናድግ እየተገለጠልን፡ እየተረዳነው እንመጣለን።
« ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። » ዕብ ፭፣፲፪
ቃሉ እንዲሠራብን ከኛ ግንዛቤን ሳይሆን ተግባራዊ ምላሽን  ይፈልጋል። ስለዚህ ለቃሉ እንታዘዝ።
«ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።» ያዕ ፩፣፳፪
ቃሉን ሰምተን እንድንታዘዝ ጸጋውን ያብዛልን።
ይቆየን። 

1 comment:

  1. አሜን አሜን!!!!!! ቃሉን ሰምንተን እንድንታዘዝ ይርዳን አንተን እና ቤተሰቦችህን እግዚአብሔር አምላክ አብዝቶ ይባርክ!!!

    ReplyDelete

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment