Wednesday, May 7, 2014

ስለመጽሐፍ ቅዱስ መረጃዎች-



መጽሐፍ ቅዱስ ከስሙ ስንነሳ ልዩ መጽሐፍ ማለት ነው። ቀደሰ- ለየ ብሎ ቅዱስ - ልዩ ይላልና።
- በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት በሰዎች ቋንቋ የተጻፈው ይህ ታላቅ መጽሐፍ በመንፈሳዊያን ብቻ ሳይሆን በዓለማውያን ዘንድም አድናቆትን ያገኘ ዘመን የማይሽረውየሕይወት መመሪያ ነው።
 ለምሳሌ፡ ሳይንቲስ ሚካኤል ፋራዳይ ስለመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሏል።
       ለምን ይሆን ሰዎች በተሳሳተ አቅጣጫ ሕይወታቸውን የሚመሩት? የተባረከው ቅዱስ መጽሐፍ በቀና 
       ጎዳና ሊመራቸው መቻሉን አልተረዱት ይሆን?
             ፲፮ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳነት አብርሃም ሊንከንም፡-
       መጽሐፍ ቅዱስን በማንበቤ ብዙ ተጠቅሜአለሁ። እስኪ አንተም በመንፈስና በዕምነት ተሞልተህ
        አንብበው። ያለጥርጥር በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የተሻለ ሰው ሆነህ ትኖራለህ።
- የሚገርመው የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት በተመጠነ እና ግልጽ በሆነ ቋንቋ መጻፉ ሲሆን በየትኛውም ዘመን፡ በየትኛውም ቦታ፡ በየትኛውም የዕውቀት ደረጃ ላለ ሁሉም ሰውሊረዳ የሚችል ነው።
- መጽሐፍ ቅዱስ ከሰዎች የኑሮ ልማድ ጋር በየጊዜው መሻሻል የማያስፈልገው፡ አንድ ጊዜ የተጻፈና ሁልጊዜ የሚነበብ ዕለታዊ የነፍስ ማዕድ ነው።
-መጽሐፍ ቅዱስ ከየትኛውም ጥንታዊ መጽሐፍ ይልቅ እስካሁን የተጠበቀ፡ እንዲሁም በኅትመት ደረጃ አንደኛ የሆነ፡ በብዛትና በፍጥነት እየታተመ ያለ ብቸኛ መጽሐፍ ነው።
- በዓለም የራሳቸው ፊደል ባላቸው ቋንቋዎች ሁሉ የተተረጎመ ብቸኛው መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ፡-
- ለክርክር ሳይሆን ለፍቅር የተጻፈ፡ ለምርምር የሚሰወር ለእምነት የሚገለጽ
- ለተማረውም ላልተማረውም እኩል የሚናገር፡ ለሁሉም ዘመን ለሁሉም ሰው የሚሆን
- ከየት እንደመጣን፡ ለምን እንደምንኖር፡ ወዴት እንደምንሄድ የሚናገር
- እግዚአብሔርን የምናይበት መነጽር፣ ራሳችን የምናይበት መስታውት ነው።
    + ስለሕይወት አጀማመር በተለያዩ ወገኖች የተለያየ መላምት በሚነገርበት ዓለም ላይ ስለሕይወት ጅማሬ በመላምት ሳይሆን በእርግጠኝነት የሚናገር
    + ሳይንስ እንዴት እንኖራለን? የሚለውን በመመለስ አኗኗራችን ባሻሻለበት ዓለም ላይ ለምን እንኖራለን የሚለውን ባይመልስም የመኖርን ትርጉም የሚሰጠን
    + ስለአንድ ሰው የነገ ዕጣ ፈንታ መናገር በማይቻልበት ዓለም ላይ ስለአንድ ሰው አይደለም ስለመላው ዓለም (የሰው ልጅ)  የነገ ዕጣ ፈንታ እና ከሞት በኋላ ስላለውሕይወት የሚገልጽ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው።
- ሕይወት ጉዞ ናት። እኛም መንገደኞች ነን። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ወዴት እና እንዴት መሄድ እንዳለብን የሚነግረን የጉዞ ካርታችን ነው። መጽሐፍ ቅዱስንየማያነቡ ካርታቸውን የጣሉ መንገደኞች ናቸው። ተንከራታቾች ናቸው።
- በዓለም ላይ የነበሩ ታላላቅ ሰዎች፡ ርእዮተ-ዓለሞች፡ አስተሳሰቦች ሁሉ አልፈዋል። የማለፍን ሥርዓት ተቋቁሞ አሁን ድረስ የቆየ ወደፊትም ሰማይና ምድር ሲያልፉጸንቶ የሚኖረው የእግዚአብሔር ቃል ነው።
- እግዚአብሔር የተጻፈውም፡ የተናገረውም ቃሉ እኩል ኃይል አላቸው። ለሰው ደብዳቤ ከሚጽፍልን በግምባር በቃሉ ቢያናግረን ይበልጥ ትኩረት እንሰጠዋለን።ለእግዚአብሔር ግን እንደዚያ አይደለም። የተጻፈው ቃሉ እንደተናገረው ቃሉ እኩል ኃይል አለው።
እግዚአብሔር ሙሴን ባናገረበት፡ ክርስቶስም ሐዋርያትን ባናገረበት መጠን እና ኃይል ዛሬም እኛን በቃሉ ያናግረናል።
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን አናነብም ማለት እግዚብሔር እያናገረን አልሰማነውም/ዘጋነው ማለት ነው።
- ስለዚህ እናንብ።
                                         ምንጭ፡- ከተለያዩ ስብከቶችና መጻሕፍት
---------------- ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣይ ስለመጽሐፍ ቅዱስ አጻጻፍ  እንቀጥላለን-------
------------------------------ይቆየን-------------------------