Thursday, April 17, 2014

ስለ ክርስቶስ መከራና መስቀል (ማዳን) በመጽሐፍ ቅዱስ


ዲያብሎስ ድል እንደሚሆን ለአዳም ተስፋ የተሰጠው
« በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ። » ዘፍ ፫፣፲፭።
ትንቢት የተነገረለት
«አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ?...  ብዙ ውሾች ከብበውኛልና የክፋተኞች ጉባኤም ያዘኝ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ።…..ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፥ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ።» መዝ፳፩ (፳፪)፥፩፣፲፮፣፲፰።
«በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል….. እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፡ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።……ተጨነቀ ተሣቀየም፡ አፉንም አልከፈተም፡ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።….. ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።» ኢሳ ፶፫፥ ፬፣፭፣፯፣፲፪
የማይቆጠር መከራ
«ከእሾህም አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ፥ በቀኝ እጁም መቃ አኖሩ፥ በፊቱም ተንበርክከው። የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ ዘበቱበት፤…. ከሰቀሉትም በኋላ ልብሱን ዕጣ ጥለው ተካፈሉ፥….» ማቴ ፳፯፥ ፳፱፣፴፭።
« ራሱንም በመቃ መቱት ተፉበትም፥ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ከተዘባበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት፥ ሊሰቅሉትም ወሰዱት።….. ሰቀሉትም፥ ልብሱንም ማን ማን እንዲወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ።..»  ማር ፲፭፥ ፲፱፣፳፣፳፬፣፳፭።

Saturday, April 12, 2014

የክርስቶስ መከራና ሞት - የመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት

መጽሐፍ ቅዱስ ስለተለያዩ ርእሰ-ጉዳዮች በውስጡ ባሉት መጻሕፍቱ በተለያየ መንገድ ይናራል። አንዳንድ ጉዳዮች ደግሞ ሲደጋገሙ እናያለን። አንድ ታሪክ ወይም ክስተት ከተደጋገመ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ማለት ነው። ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጠቃሚዎች እንደሆኑ ቢታወቅም የሚደጋገም ጉዳይ ከሆነ ልዩ ትኩረት የተሰጠው እና እጅግ ጠቃሚ ነው ማለት ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት ተሰጥቶአቸው ከተደጋገሙት ታሪኮች የጳውሎስ መለወጥ አንዱ ነው፤ ጳውሎስ አሕዛብን ያስተማረ ታላቅ ሐዋርያ ነው። ክርስቲያኖችን እያሳደደ ሳለ ጌታ ተገልጦ እንደለወጠው የሚናገረው ታሪክ በዚያው በሐዋርያት ሥራ ውስጥ  ሦስት ጊዜ ተጽፎ እናገኘዋለን። የእርሱ መለወጥ ለብዙዎች መለወጥ ምክንያት ስለሆነ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።
የሐዋ ፱፥ ፩-፱፣            ፳፪፥፩-፲፩፣       ፳፮፥፲፪-፲፰።
አብርሃም ከታወቁት የብሉይ ኪዳን አባቶች ይበልጥ ሰፊ ሽፋን ያገኘ በብዙ መጻሕፍት የተጠቀሰ ታላቅ የእምነት አባት ነው። በኦሪት፡ በታሪክ፡ በመዝሙር፡ በትንቢት፡ በወንጌል፡ በመልእክታት መጻሕፍት ስሙ ተጠቅሶአል።  ምንም እንኳ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን የመጀመሪያው ቃል ኪዳኑ በሥጋ አባታቸው በሆነው በአብርሃም በኩል ከእስራኤላውያን ጋር ቢሆንም በሐዲስ ኪዳን በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ ልጆቹ እንደሚሆኑ አስቀድሞ በማየት አብርሃምን መርጦታል።
« እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ። በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። » ገላ ፫፥፯-፰
ስለዚህ አብርሃም በእምነት ጉዳይ ላይ ትልቅ መታዘዝ ያሳየ፡ አስቀድሞ ወንጌል የተሰበከለት፡ ለሌሎችም አርአያ የሆነ የብዙዎች አባት በመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት ተሰጥቶታል።
በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ሶፍትዌር (አዮታ) ቆጠራ መሠረት በመላው መጽሐፍ ቅዱስ፡
ዳዊት 957 ጊዜ፡     ሙሴ 783 ጊዜ፡     አብርሃም 229 ጊዜ      ስማቸው ተጠቅሶአል። (የአብርሃም ስም ግን ከሌሎቹ ይልቅ በብዙ ጸሐፊዎች/ መጻሕፍት የተጻፈ ከሌሎች የበለጠ ሽፋን ተሰጥቶታል።)  
እግዚአብሔር  የሚለው ቃል  7361   ጊዜ        ፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ 1185  ጊዜ ተጽፎአል።  መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ትልቅ ትኩረት የሰጠው ሰው ለሆነው እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ ነው።