Saturday, April 12, 2014

የክርስቶስ መከራና ሞት - የመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት

መጽሐፍ ቅዱስ ስለተለያዩ ርእሰ-ጉዳዮች በውስጡ ባሉት መጻሕፍቱ በተለያየ መንገድ ይናራል። አንዳንድ ጉዳዮች ደግሞ ሲደጋገሙ እናያለን። አንድ ታሪክ ወይም ክስተት ከተደጋገመ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ማለት ነው። ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጠቃሚዎች እንደሆኑ ቢታወቅም የሚደጋገም ጉዳይ ከሆነ ልዩ ትኩረት የተሰጠው እና እጅግ ጠቃሚ ነው ማለት ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት ተሰጥቶአቸው ከተደጋገሙት ታሪኮች የጳውሎስ መለወጥ አንዱ ነው፤ ጳውሎስ አሕዛብን ያስተማረ ታላቅ ሐዋርያ ነው። ክርስቲያኖችን እያሳደደ ሳለ ጌታ ተገልጦ እንደለወጠው የሚናገረው ታሪክ በዚያው በሐዋርያት ሥራ ውስጥ  ሦስት ጊዜ ተጽፎ እናገኘዋለን። የእርሱ መለወጥ ለብዙዎች መለወጥ ምክንያት ስለሆነ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።
የሐዋ ፱፥ ፩-፱፣            ፳፪፥፩-፲፩፣       ፳፮፥፲፪-፲፰።
አብርሃም ከታወቁት የብሉይ ኪዳን አባቶች ይበልጥ ሰፊ ሽፋን ያገኘ በብዙ መጻሕፍት የተጠቀሰ ታላቅ የእምነት አባት ነው። በኦሪት፡ በታሪክ፡ በመዝሙር፡ በትንቢት፡ በወንጌል፡ በመልእክታት መጻሕፍት ስሙ ተጠቅሶአል።  ምንም እንኳ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን የመጀመሪያው ቃል ኪዳኑ በሥጋ አባታቸው በሆነው በአብርሃም በኩል ከእስራኤላውያን ጋር ቢሆንም በሐዲስ ኪዳን በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ ልጆቹ እንደሚሆኑ አስቀድሞ በማየት አብርሃምን መርጦታል።
« እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ። በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። » ገላ ፫፥፯-፰
ስለዚህ አብርሃም በእምነት ጉዳይ ላይ ትልቅ መታዘዝ ያሳየ፡ አስቀድሞ ወንጌል የተሰበከለት፡ ለሌሎችም አርአያ የሆነ የብዙዎች አባት በመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት ተሰጥቶታል።
በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ሶፍትዌር (አዮታ) ቆጠራ መሠረት በመላው መጽሐፍ ቅዱስ፡
ዳዊት 957 ጊዜ፡     ሙሴ 783 ጊዜ፡     አብርሃም 229 ጊዜ      ስማቸው ተጠቅሶአል። (የአብርሃም ስም ግን ከሌሎቹ ይልቅ በብዙ ጸሐፊዎች/ መጻሕፍት የተጻፈ ከሌሎች የበለጠ ሽፋን ተሰጥቶታል።)  
እግዚአብሔር  የሚለው ቃል  7361   ጊዜ        ፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ 1185  ጊዜ ተጽፎአል።  መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ትልቅ ትኩረት የሰጠው ሰው ለሆነው እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
 
አሁን የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ትኩረት ወደ ሆነው ጉዳይ ስናልፍ የክርስቶስ የሕማማቱን ሳምንት ወይም መከራና ሞቱን እናገኛለን።
አራቱ ወንጌላውያን ስለ ክርስቶስ የጻፉትን ብንመረመር የተለየ ውጤት እናገኛለን። ለምሳሌ የጌታን ልደቱን በተመለከተ ፬ቱ ወንጌላውያን በተለያየ አቅጣጫ ይጀምራሉ።
ማቴዎስ በዘር ሃረግ ቆጠራ                  ማርቆስ በመንገድ ከፋቹ በመጥምቁ ዮሐንስ፡
ሉቃስ በብሥራቱና በበረት እንዴት እንደተወለደ፡     ዮሐንስ በመለኮታዊ ማንነቱ ቀዳማዊ መሆኑን  በመጥቀስ በተለያየ ሁኔታ ልደቱን ዘግበዋል።
ስለጥምቀቱ፡ ስለጾሙ የጻፉ አሉ፤ ያልጻፉም አሉ። ከትምህረቶቹ፡ ከተአምራቶቹ የዘገቡ አሉ። ያልዘገቡም አሉ። መከራና ሞቱን ግን አራቱም ዘግበዋል። ከተያዘበት ከሐሙስ ማታ ጀምሮ እስከ ዓርብ ማታ እንዲሁም እስከ ተነሳበት ቅዳሜ ለእሑድ ሌለት ድረስ ያሉት 3 ቀናት የተለየ ትኩረት ተሰጥቶባቸዋል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚች ምድር ላይ 33 ዓመት ከ3ወር እንደቆየ ይታወቃል። 30 ዓመት እናቱን ድንግል ማርያምን እያገለገለ፡ ለዋናው አገልግሎቱ ሲዘጋጅ ከቆየ በኋላ፡ 3 ዓመት ሰማያዊ አባቱን በማገልገል በመጨረሻ በመስቀል ተሰቅሎ ሞቶ በመነሳት ወደ ሰማይ ዐርጓል።
አራቱ ወንጌላት በጠቅላላ 89 ምዕራፎች አሉአቸው። ከዚህ ውስጥ፡-
ስለ30 ዓመት ቆይታው የሚናገሩት 4 ምዕራፎች ብቻ ሲሆኑ፡  የ3 ዓመት አገልግሎቱ በቀሩት 85 ምዕራፎች ተጽፎአል፤  ስለዚህ 95 % የሚሆነው የወንጌል ክፍል ስለ 3 ዓመት አገልግሎቱ ይናገራል። አሁንም ከዚህ ውስጥ፡ 18 ምዕራፎች ስለመጨረሻዎቹ 3 ቀናት ይናገራሉ። እንግዲህ በ4 ቱም ወንጌሎች  20%  የሚሆነው ክፍል ስለ 3 ቀናቱ መከራና ሞት ይናገራሉ።
ማቴዎስ ከምዕራፍ 26- 28 በመጨረሻዎቹ 3  ምዕራፎች
ማርቆስ ከምዕራፍ 14 - 16 በመጨረሻዎቹ 3 ምዕራፎች
ሉቃስ ከምዕራፍ 22 - 24  በመጨረሻዎቹ 3 ምዕራፎች
ዮሐንስ ከምዕራፍ 13 - 21            በመጨረሻዎቹ 9 ምዕራፎች
በአጠቃላይ 18 ምዕራፎች የመጨረሻዎቹን 3 ቀናት መከራና ሞቱን (ትንሣኤውንም) ይዘግባሉ። ዮሐንስ የመጨረሻውን ቀን (የሐሙስ ማታ) ትምህርቱን በሰፊው ጽፎአል።
አራቱም ወንጌላውያን በተለያየ መልክ ይጀምራሉ፡ ተመሳሳይ / የተለያዩ ጉዳዮችን ይዳስሳሉ፡ አራቱም መከራና ሞቱን በመናገር በተመሳሳይ ርእስ ይጨርሳሉ።
እዚህ ላይ የአራቱን ወንጌላት ትኩረት አየን እንጂ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ በኦሪት፡ በታሪክ፡ በመዝሙራት፡ በነቢያት መጻሕፍት በምሳሌ እና በትንቢት መልክ፡ በመልእክታትና በራእይ መጻሕፍት ሁሉ ስለክርስቶስ መከራና ሞት የተዘገበ የመጽሐፍ ቅዱስ አንኳር መልእክት ነው።
(ስለዚህ ጉዳይ ከዚህ ጽሑፍ በፊት የወጣውን ስለ ክርስቶስ መከራና መስቀል በመጽሐፍ ቅዱስ  የሚለውን ንባብ ይመልከቱ።)
አብዛኛው ማለት ይቻላል መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ እንደሚናገር ራሱ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ መስክሮአል።
« ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው። ….. እርሱም፦ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው።» ሉቃ ፳፬፥፳፯፡፵፬
መላው መጽሐፍ ቅዱስ በአቀራረቡ ከፍጥረተ-ዓለም እስከ ኅልፈተ-ዓለም የብዙ ሺ ዓመታት ነገሮችን በአብዛኛው ጠቅለል አድርጎ ሲናገር የክርስቶስን ሕይወት ግን ከልደቱ እስከ ሞቱና ትንሣኤው በዝርዝር ዘግቧል። ከሚናገርለት የብዙ ሺ ዓመታት ጉዳይ እና ብዙ ሰዎች አንጻር ስናየው ስለ ክርስቶስ ከሁሉም የበለጠ ሰፊ ሽፋን ሰጥቷል።  በተለይም መከራና ሞቱን፡ የሦስቱን ቀናት ክስተት (ከትንሣኤው ጋር) በተለየ ሁኔታ በየሰዓቱ ማለት ይቻላል የነበረውን ዝርዝር ሁኔታ በመናገር ከሌላው የሕይወት ክፍሉ የላቀ ትኩረት እንደሰጠው እናስተውላለን።  
የክርስቶስ መከራና ሞት በመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው፡ በሕይወታችንም ትልቅ ስፍራ የያዘ ታላቅ ጉዳይ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ትኩረት የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ መከራና ሞት ፡ የእግዚአብሔር  እቅድ፡ ፍቅሩ የተገለጸበት፡ ሕይወትን ያገኘንበት፣ የመዳናችንና የሕልውናችን መሠረት የሆነ ታላቅ ርእስ በመሆኑ እንዲሁ በቀላሉ የምናልፈው ነገር አይደለም።
የዘላለም ሕይወትን ያገኘነው በክርስቶስ ሞት ነው ፡ሞቱ በሕይወታችን የሕልውናችን ጉዳይ ነው።  የኢየሱስ ክርስቶስን መከራና ሞት ሊተካ፡ ሊተካከል፡ ወይም ሊወዳደር የሚችል አንዳች ነገር የለም አይኖርምም። ስለሆነም የአንድ ሰሞን አጀንዳ ብቻ ሳይሆን የዘወትር ርእሳችን ሊሆን ይገባል። በመጽሐፈ ቅዳሴ «ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ፡ ወትንሣኤከ ቅድስተ» ይላል። « አቤቱ ሞትህን እንናገራለን፡ ቅድስት የምትሆን ትንሣኤህንም።»  በየዕለቱ ዘወትር የክርስቶስን መከራና ሞት ልናስብ፡ ልንናገር ይገባል።
« ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና።»   ፩ቆሮ ፲፩፥፳፮።
አንዳንዶች ዛሬ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በተነገረ ጊዜ ቅር ይላቸዋል፡ ሌላ ጉዳይ ያስባሉ። ነገር ግን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መቼ ተነግሮ ያልቅና። መቼስ ተጽፎ ያልቅና። የሚወደው ሐዋርያም ይህን መስክሮአል።
« ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል።»  ዮሐ ፳፩፥ ፳፭።
ቢጻፍ ዓለም የማይበቃው የክርስቶስ ነገር የመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት፡ የእግዚአብሔር መልእክት እንደሆነ ሁሉ የኛም የስብከታችን ትኩረት፡ የዘወትር ርእሳችን፡ የሁልጊዜ መልእክታችን ሊሆን ይገባዋል።   
« በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤
ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው» ፊልጵ ፪፥ ፰-፲፩።
« እንግዲህ እንደ ወንጌሌ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ተሰበከ፥ ከዘላለም ዘመንም የተሰወረው አሁን ግን የታየው በነቢያትም መጻሕፍት የዘላለም እግዚአብሔር እንደ አዘዘ ለእምነት መታዘዝ ይሆን ዘንድ ለአሕዛብ ሁሉ የታወቀው ምሥጢር እንደ ተገለጠ መጠን ሊያበረታችሁ ለሚችለው፥
ብቻውን ጥበብ ላለው ለእግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።» ሮሜ ፲፮፥፳፭-፳፯።

2 comments:

  1. I pray for you all the timeJune 1, 2012 at 10:06 AM

    life giving teaching!

    ReplyDelete
  2. ketint geta lelijochu bateleyaya manged yinager neber ;zarre degmo baliju bakul sila rasu maninet yetenagernin yahiwoptin kal enante degmo gilts behona menged silastelelefachulin be ewunet ahunim geta yibarikachu

    ReplyDelete

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment