Monday, February 17, 2014

ድንቅ ምርጫ

Denk mercha, sebket, READ IN PDF
እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፦ ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው። ፩ሳሙ ፲፮፡ ፯
መጽሐፍ ቅዱሳችን ስናጠና ከምንመለከታቸው አስደናቂ የእግዚአብሔር እውነቶች መካከል አንዱ የእግዚአብሔር ምርጫ ከሰው ምርጫ ፈጽሞ የተለየና የማይገናኝ መሆኑን ነው። ሰዎች በተለያየ መስፈርት አንደኛ ብለው የመረጡትን እግዚአብሔር አያጸድቅም። በድምጽ ብልጫም ስለማይሠራ የራሱ የሆነ ምርጫ ያለው ግሩም ድንቅ አምላክ ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው መጽሐፍ እንኳ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ (በኩር) ይልቅ በሁለተኛ (መጨረሻ) ልጅ ላይ ትኩረት ሲያደርግ እንመለከታለን።
·         በአዳም የመጀመሪያ ልጅ በቃየን ሳይሆን በሦስተኛው ልጅ በሴት
·         በአብርሃም የመጀመሪያ ልጅ በእስማኤል ሳይሆን በይስሐቅ
·         በይስሐቅ የመጀመሪያ ልጅ በዔሳው ሳይሆን በያዕቆብ
·         በያዕቆብ የመጀመሪያዎች ልጆች ሳይሆን በመጨረሻው በዮሴፍ
·         በዮሴፍ በመጀመሪያው ልጅ በምናሴ ሳይሆን በሁለተኛው ልጅ በኤፍሬም…. በረከቱን ሲያፈስ፡ ቃልኪዳኑን ሲያጸና እንመለከታለን።





ሰዎች በልደት፡ በዕድገት፡ በቁመት፡ በጉልበት…. አንደኛ ያደረጉትን እግዚአብሔር አይጠቀምም። እግዚአብሔር አስደናቂ ሥራውን የሚሠራው ሰዎች በናቋቸው፡ በጠሏቸውና በረሷቸው ሰዎች እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ የምንገነዘበው የእግዚአብሔር ድንቅ ምርጫ ነው።
ለእስራኤል ንግሥ ሆኖ የተቀባው፡ ታላቁን ጎልያድን ድል ያደረገው ፡ እግዚአብሔር እንደልቤ ያለው የእሴይ ልጅ የተረሳው እረኛ፡ የመጨረሻው ልጅ ዳዊት እንደሆነ ማስታወስ አለብን። ፩ሳሙ ፲፮፡፲፩
እግዚአብሔር ላሰበው ጉዳይ ማንን እንደሚመርጥ በምንና እንዴት እንደሚሠራ ለማወቅ አይደለም ለመገመት አንኳ አንችልም። አሠራሩ ብዙ ነው። በጠበቅነው ቀርቶ ባልጠበቅነው ሊመጣ ይችላል። ከምናያቸው ነገሮች ከጥናቶቻችን፡ወይም ከመረጃዎቻችን ተነስተን አንደን ሰው ይህ እግዚአብሔር የመረጠው የእርሱ አገልጋይ ነው/አይደለም ብለን መደምደም አንችልም።
በሐዲስ ኪዳን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን ለአገልግሎት ሲመርጥ ከምኩራብ (የአይሁድ መድረክ)፡ ወይም ከቤተ መቅደስ ሲያገለግሉ ከኖሩት ሰዎች አልነበረም። ሐዋርያት እዚህ ግባ የሚባል የእግዚአብሔር ዕውቀት የነበራቸው ሰዎች አልነበሩም። ከዓሳ-አጥማጅነት፡ ከቀራጭነት፡ …. ከመሳሰሉት የተናቁ ሥራዎች ላይ ተመርጠዋል።
እኛ  በተለያየ መስፈርት የምንንቃቸው፡ ሽፍታ፡ ሌባ፡ ወዘተ… ብለን የፈረጅናቸው ነገ ምን እንደሚሆኑ አናውቅም። እግዚአብሔር ቸርነቱን ካበዛለት የማይለወጥ የለም። ዛሬና አሁን ያለበትን ሁኔታ ብቻ በማየት ሰውን እንዲህ ነው ብለን መደምደም አንችልም። የነገውንና የመጨረሻውን አናውቅምና።
አዳምን ቀድሞት ወደ ገነት የገባው ዘመኑን ሁሉ ሽፍታ ሆኖ የኖረ ወንበዴ መሆኑን ማስታወስ አለብን። ሉቃ፳፫፡ ፴፱ - ፵፫፡  
በሰዎች ዓለም ሰው ለአንድ ሥራ የሚታጨው ብዙ ነገሮቹ ታይተው ነው። እግዚአብሔር ሰዎችን ለአገልግሎት ሲመርጥ ከመልካምነታቸው ተነስቶ፡ ፈተና አውጥቶ፡ መስፈርት አስቀምጦ፡ … አይደለም።
አንባቢው ያስተውል። የተጻፈው እውነት- የእግዚአብሔር ቃል- አንብበን እንድናደንቀው ሳይሀን አንድንጠቀምበት ነው።  ዛሬም በዘመናችን ይህ አስደናቂ የእግዚአብሔር ድንቅ ምርጫ አለ።  በማንጠብቃቸውና በማንገምታቸው ሰዎች  እግዚአብሔር  ስራውን ይሰራል:;
-       አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና ይላል እግዚአብሔር፦ ኢሳ ፶፭:፰

1 comment:

  1. Tebareku yebelete yemititegubetin Tsegawun yabzalachu

    ReplyDelete

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment