Friday, November 15, 2013

አዲስ ኪዳን - የትንቢት ክፍል (የዮሐንስ ራእይ)

በአዲስ ኪዳን ዳሰሳ ባለፈው በ፫ኛው ጥናታችን የመልእክት ክፍል የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስንና ቀጣዮቹን መልእክታት ዳሰሳ አይተናል። ዛሬ በአዲስ ኪዳን የመጨረሻ የሆነውን የትንቢት ክፍል ይሄውም የዮሐንስ ራእይን ጠቅለል አድርገን እንመለከታለን። የዮሐንስ ራእይ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ክፍል ሲሆን በአዲስ ኪዳን መጀመሪያ ክርስትና በሐዋርያት በኩል ወደ ዓለም ከተስፋፋ በኋላና የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት (የክርስቲያኖች ኅብረት) ከተመሠረቱ በኋላ እነርሱን ለማበረታታት፣ በተለያየ ምክንያት ከክርስትና ወደ ኋላ ያሉትንም ለመገሰጽ፣ በዓለም ላይ በክርስቲያኖች የሚደርሰው መከራና ፈተና ፍጻሜ እንደሚኖረው ዲያብሎስም ለመጨረሻ ጊዜ ድል እንደሚደረግ የመሳሰሉ ሃሳቦችን ይዟአል።
መጽሐፉ የዮሐንስ ራእይ ቢባልም ራእዩ ከመጽሐፉ መጀመሪያ እንደምንረዳው እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የገለጠለት ሆኖ በመልአክ በኩል ለዮሐንስ ልኮለት የጻፈው ነው።   
« ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥» ራእ ፩፣፩
መጽሐፉ የአዲስ ኪዳን ትንቢት እንደመሆኑ መጠን ከብሉይ ኪዳን እንደ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ካሉ አንዳንድ የትንበት መጽሐፍ ጋር ያሉ ጉዳዮችን እያነሳ ይናገራል። በወቅቱ በሐዋርያት እና በተከታዮቻቸው ትምህርት ለተመሠረቱ የተለያዩ የክርስቲያኖች ኅብረት በተለይም በእስያ ለሚገኙ ፯ አብያተ ክርስቲያናት ማጽናኛ እና ተግሣጽ ሆኖ ሲጻፍ እንደ አጠቃላይ በመጨረሻው ዘመን ለሚገኙ ክርስቲያኖችም ተስፋና ማጽናኛ ምክሮችን ይዟል። አቀራረቡ ከሌሎች በተለየ በስእላዊ መግለጫዎች የተሞላ ድራማ መሰል ሥነ-ጽሑፍ ነው። ስለመጨረሻው ዘመን ብዙ ትንቢቶችን እንደያዘ እና ረቂቅ ምሥጢራዊ የአጻጻፍ ስልት እንዳለው ብዙ መምህራን ያስረዳሉ። በዚህም ምክንያት በመጽሐፉ አተረጓጎም ላይ ብዙ የተለያዩ ሃሳቦች ይቀርባሉ።
ዮሐንስ ቀደም ሲል በወንጌሉ ኢየሱስ ክርስቶስን «የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ» ብሎ ካስተዋወቀ በኋላ አሁን ደግሞ በራእዩ የታረደው በግ ይለዋል። (ዮሐ ፩፣፳፱ ፡ ራእ ፭፣፲፪)። ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላም ድል የነሳው የዳዊት ስር የይሁዳ አንበሳ ተብሏል። ለዓለም ሁሉ ኃጢአት ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ የዋለው ስለ ሁላችን የሞተው የታረደው በግ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በትንቢተ ኢሳይያስ በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ የተባለለት በዚህ መጽሐፍ የድል አድራጊነቱን ውጤት የበጉ ደም፣ የበጉ የሕይወት መጽሐፍ፣የበጉ ሠርግ፣ የበጉ ሙሽራ፣ የበጉ ዙፋን ወዘተ… በማለት በተለያየ መልክ ይገልጻል።


በዚህ መጽሐፍ ብዙ ነገሮችን በሰባት ተገልጸው እናገኛለን። ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፣ ሰባቱ ማኅተሞች ሰባቱ መለከቶች፣ ሰባቱ መቅሰፍቶች፣ ወዘተ። በዕብራውያን ባሕል ሰባት በቀጥታ ብዛትን ሳይሆን ሃሳብን ያመለክታል። ፍጹምነትን ያሳያል። ቁጥሮች ያለውሳኔ ሲነገሩ ከብዛት ይልቅ ሃሳብን ያሳያሉ። ለምሳሌ በእኛ ባሕል አሥር እና ሺ ሃሳብን እንደሚያሳዩ፣ አሥር ጊዜ እንዲህ አትበል፣ ሺ ጊዜ ብትለፋ አይሆንም የሚለው አነጋገራችንን ማየት እንችላለን። በመጽሐፉ ሰባት ቁጥር ሃምሳ ሁለት ጊዜ እንደተጻፈ ይጠቀሳል።
የዮሐንስ ራእይ አጽንኦት የሚሰጣቸው ሃሳቦች በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በተጻፈው መሠረት፡ ስለእግዚአብሔር ልእልና፣ የሰይጣን ኃይል ጥላቻና የሚፈረድበት መሆኑ፣ የዓለም ኃይል ከንቱነትና ኃላፊ መሆኑ፣ ቤተ ክርሰቲያን የምትቀበለው መከራ፣ የመጨረሻው ፍርድ መቃረብ፣ የክርስቶስ ድልና የመገለጡ ክብር፣ ምዕመናን እስከ መጨረሻው መታገሳቸው ጥበቃቸውና ብጽእናቸው… ወዘተ ይገልጻል።  
መጽሐፉ በተጻፈበት ዘመን በሐዋርያት እና በተከታዮቻቸው ስብከት ወደ ክርስትና የገቡ ብዙ አማኞች ስለነበሩ በወቅቱም ትምህርቱ አዲስ በመሆኑ ክርስቲያኖች ከአሕዛብም ሆነ ከአይሁድ የተለያዩ ስደት ይደርስባቸው ነበር። እስከ መታመም፣ እስራትና ሞት ድረስ የደረሱም ነበሩ። ስለዚህ እነዚህን በመከራ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖችን ለማበረታታት፣ ተስፋ ለመስጠት መልእክቱ ተጽፎአል። በልዩ ልዩ መንገድ መከራ የሚያደርስባቸው ዘንዶው ዲያብሎስ ፍጹም ድል እንደሚደረግ፣ አዳኙና ድል አድራጊው የታረደው በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመከራቸውም፣ ከዲያብሎስም በላይ እንደሆነ፣ የሚደርስባቸው ችግር ሁሉ ከዓለም ጋር ጊዜያዊ እንደሆነና እንደሚያልፍ በመጨረሻ ፍጹም በሆነ እረፍት ለዘላለም የሚኖሩበት ጊዜ እንደሚመጣ በመገንዘብ እንዲጽናኑ ይመክራል።
ይህ መልእክት ለእኛም ዛሬ ወቅታዊ የሆነ አስፈላጊያችን ነው። ክርስቶስን በማመናችን የሚደርስብን ነቀፌታ፣ ስደት ሁሉ ጊዜያዊ እና ሃላፊ መሆኑን አውቀን፣ በዓለም ላይ የሚደርስብን ፈተናና ችግር ሁሉ ከዓለሙ ጋር እንደሚያልፍ በማስታወስ ከችግሮቻችን ሁሉ በላይ የሆነውን  ክርስቶስን ተስፋ አድርገን በትዕግሥትና በጽናት እንድንኖር ያሳስበናል።
በአጠቃላይ የዮሐንስ ራእይ ከሌሎች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ረቀቅ ያለ ላለንበት ወቅት እና እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የማጽናኛ ቃል የሆነ ትንቢታዊ መልእክትን ያዘለ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ዘመን የመጨረሻው መልእክት ነው። መጽሐፉ እንደ ዓለሙ በክርስቶስ መምጣት ፍጻሜውን ያደርጋል። ከአሁን ቀደም እንዳየነው መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም መፈጠር ይጀምራል፣ የዓለምን መዳን ማዕከል ያደርጋል በዓለም ማለፍ ይደመድማል።
የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው መጽሐፍ የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር፡
«በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። » ይላል። ዘፍ ፩፣፩
የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው መጽሐፍ የመጨረሻው ዓረፍተ ነገር፡
« ይህን የሚመሰክር። አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና።» ራእ ፳፪፣ ፳     
በመጨረሻም በጸሎትና ቡራኬ ይደመድማል።
« የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።» ራእ ፳፪፣፳፩።
እኛም በሥነ ጽሑፋዊው አከፋፈሉ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ ዳሰሳ በዚህ እየፈጸምን በቀጣይ መጽሐፍ ቅዱስ ለመረዳት እንድንችል የሚያደርጉ ቁልፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትን (ሃሳቦችን) እናያለን።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣይ- የመጽሐፍ ቅዱስ ቁልፍ ሃሳቦችን ፲፪ ክፍል ተከታታይ ጥናት በየተራ እናያለን።
ይቆየን። 

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment