Friday, November 15, 2013

አዲስ ኪዳን - የትንቢት ክፍል (የዮሐንስ ራእይ)

በአዲስ ኪዳን ዳሰሳ ባለፈው በ፫ኛው ጥናታችን የመልእክት ክፍል የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስንና ቀጣዮቹን መልእክታት ዳሰሳ አይተናል። ዛሬ በአዲስ ኪዳን የመጨረሻ የሆነውን የትንቢት ክፍል ይሄውም የዮሐንስ ራእይን ጠቅለል አድርገን እንመለከታለን። የዮሐንስ ራእይ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ክፍል ሲሆን በአዲስ ኪዳን መጀመሪያ ክርስትና በሐዋርያት በኩል ወደ ዓለም ከተስፋፋ በኋላና የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት (የክርስቲያኖች ኅብረት) ከተመሠረቱ በኋላ እነርሱን ለማበረታታት፣ በተለያየ ምክንያት ከክርስትና ወደ ኋላ ያሉትንም ለመገሰጽ፣ በዓለም ላይ በክርስቲያኖች የሚደርሰው መከራና ፈተና ፍጻሜ እንደሚኖረው ዲያብሎስም ለመጨረሻ ጊዜ ድል እንደሚደረግ የመሳሰሉ ሃሳቦችን ይዟአል።
መጽሐፉ የዮሐንስ ራእይ ቢባልም ራእዩ ከመጽሐፉ መጀመሪያ እንደምንረዳው እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የገለጠለት ሆኖ በመልአክ በኩል ለዮሐንስ ልኮለት የጻፈው ነው።   
« ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥» ራእ ፩፣፩
መጽሐፉ የአዲስ ኪዳን ትንቢት እንደመሆኑ መጠን ከብሉይ ኪዳን እንደ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ካሉ አንዳንድ የትንበት መጽሐፍ ጋር ያሉ ጉዳዮችን እያነሳ ይናገራል። በወቅቱ በሐዋርያት እና በተከታዮቻቸው ትምህርት ለተመሠረቱ የተለያዩ የክርስቲያኖች ኅብረት በተለይም በእስያ ለሚገኙ ፯ አብያተ ክርስቲያናት ማጽናኛ እና ተግሣጽ ሆኖ ሲጻፍ እንደ አጠቃላይ በመጨረሻው ዘመን ለሚገኙ ክርስቲያኖችም ተስፋና ማጽናኛ ምክሮችን ይዟል። አቀራረቡ ከሌሎች በተለየ በስእላዊ መግለጫዎች የተሞላ ድራማ መሰል ሥነ-ጽሑፍ ነው። ስለመጨረሻው ዘመን ብዙ ትንቢቶችን እንደያዘ እና ረቂቅ ምሥጢራዊ የአጻጻፍ ስልት እንዳለው ብዙ መምህራን ያስረዳሉ። በዚህም ምክንያት በመጽሐፉ አተረጓጎም ላይ ብዙ የተለያዩ ሃሳቦች ይቀርባሉ።
ዮሐንስ ቀደም ሲል በወንጌሉ ኢየሱስ ክርስቶስን «የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ» ብሎ ካስተዋወቀ በኋላ አሁን ደግሞ በራእዩ የታረደው በግ ይለዋል። (ዮሐ ፩፣፳፱ ፡ ራእ ፭፣፲፪)። ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላም ድል የነሳው የዳዊት ስር የይሁዳ አንበሳ ተብሏል። ለዓለም ሁሉ ኃጢአት ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ የዋለው ስለ ሁላችን የሞተው የታረደው በግ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በትንቢተ ኢሳይያስ በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ የተባለለት በዚህ መጽሐፍ የድል አድራጊነቱን ውጤት የበጉ ደም፣ የበጉ የሕይወት መጽሐፍ፣የበጉ ሠርግ፣ የበጉ ሙሽራ፣ የበጉ ዙፋን ወዘተ… በማለት በተለያየ መልክ ይገልጻል።

Saturday, November 9, 2013

አዲስ ኪዳን - የመልእክት ክፍል

ባለፈው ጥናታችን በአዲስ ኪዳን የታሪክ ክፍል የተባለውን የሐዋርያት ሥራን አጠቃላይ ዳሰሳ አይተናል። ዛሬ በመቀጠል የአዲስ ኪዳን ፫ኛ ክፍል የሆነውን የመልእክታት አጠቃላይ ዳሰሳ እናያለን። የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የተቀመጡት በታሪካዊ ፍሰታቸው ቅደም ተከተል እንደመሆኑ መጠን በቅድሚያ በወንጌል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ከልደት እስከ ሞትና ትንሣኤ የፈጸመውን የቤዛነት ሥራ፡ በመቀጠል ተከታዮቹ የነበሩት ሐዋርያት ይህን ወንጌል ወደ ዓለም ለማዳረስ ቤተ ክርስቲያንን በመመሥረት የፈጸሙት ሥራ በተለይ የጴጥሮስና የጳውሎስ ተልዕኮና ስብከቶች በሐዋርያት ሥራ ተዘግቧል። በማስከተል እነዚሁ ሐዋርያት የመሰረቷቸውን አብያተ ክርስቲያናት /የክርስቲያኖች ኅብረት/ ለማጠናከር በሩቅ ሆነው ደብዳቤ /መልእክት/ በመጻፍ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ያሳድጓቸው ነበር።
የመልእክት ክፍል ልዩ መልእክታትና አጠቃላይ መልእክታት ተብለው በሁለት ሊከፈሉ ይችላል።  ልዩ መልእክታት የሚባሉት ሰፊውን ክፍል የሚይዙት የጳውሎስ መልእክታት ሲሆኑ ከሮሜ እስከ ዕብራውያን ያሉት ፲፬ መልእክታት ናቸው፤ ልዩ ያሰኛቸውም በወቅቱ ለታወቁ አብያተ ክርስቲያናት (ኅብረቶች) እና ግለሰቦች በተወሰኑ ርዕሰ ጉዳዮች ስለጻፈላቸው ነው። /የዕብራውያን መልእክት የጳውሎስ ይሁን አይሁን በመጽሐፍ ቅዱስ መምህራን አከራካሪ ጉዳይ ነው። አጻጻፉ ከሌሎች መልእክታት ይለያል።/ አጠቃላይ መልእክታት የሚባሉት ጌታ በተለያዩ ጉዳዮች ከሌሎች ለይቶ ሲያቀርባቸው የነበሩት የ፫ቱ የጴጥሮስ፣ የዮሐንስ፣ የያዕቆብ እና የይሁዳ በጠቅላላ ፮ መልእክታት ሲሆኑ እነዚህ መልእክታት ጠቅለል ያለ ጉዳይ የያዙ እና በወቅቱ ለሁሉም አማኞች የተጻፉ ነበሩ። ይሁንና ሁሉም መልእከታት ዛሬ እግዚአብሔር ለኛ የሚያስተላልፋቸውን ጉዳዮች የያዙ መሆናቸውን ወደፊት በጥናታችን በየተራና በሰፊው  የምናየው ይሆናል።