Bible Translation Septuagent, READ IN PDF
የትርጉም ሥራ በመጽሐፍ ቅዱስ
መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጽሐፍት ይልቅ በመጀመሪያ ፡ በብዛትና በሁሉም ቋንቋዎች የተተረጎመ አሁንም በፍጥነት እየተተረጎመ ያለ ብቸኛ መጽሐፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ከተጻፈበት ቋንቋ በኋላ በተለያየ ዘመን ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። ከመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራዎች ውስጥ የሰባ ሊቃናት ትርጉም (ሴፕትዋጅንት) የሚባለው በጣም የታወቀ፡ ቀደምት ትርጉም ሲሆን ለሌሎች የዓለም ቋንቋዎች ትርጉም ዋና መነሻ ነው ። ስለዚህ የትርጉም ሥራ ሰፊ ጥናት ካደረገ ከአንድ መጽሐፍ የሚከተለው ቀርቧል።
«በዚያን ጊዜም ኒሳን በተባለው በመጀመሪያው ወር ከወሩም በሀያ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠሩ መርዶክዮስም ስለ አይሁድ እንዳዘዘው ሁሉ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሀያ ሰባቱ አገሮች ላሉ ሹማምትና አለቆች አዛውንትም ለእያንዳንዱም አገር እንደ ጽሕፈቱ ለእያንዳንዱም ሕዝብ እንደ ቋንቋው ለአይሁድም እንደ ጽሕፈታቸውና እንደ ቋንቋቸው ተጻፈ።» አስ ፰፣፱
ከክርስቶስ ልደት 2100 ዓመት በፊት በባቢሎን የነበረው ንጉሥ ሐሙራቢ ብዙ ጸሐፊዎች ስለነበሩት የንጉሦን አዋጆች በግዛቱ ውስጥ ባሉ በርካታ ቋንቋዎች እየተረጎሙ ሕዝቡ በሚገባ እንዲገዛለት ያደርግ ነበር። በነህምያ ጌዚም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በአምስተኛው መቶ በኋለኛው ክፍል በአይሁድ ዘንድ ልዩ የትርጉም ቅጽ ተዘጋጅቶ ነበር። በመጀመሪያ ይህ ዓይነት ትርጉም የቃል (የስማ በለው ዓይነት) ትርጉም ነበር፤ ሆኖም ቀስ በቀስ አደገና በጽሑፍ ላይ ዋለ። ከዚህም ሥራ ትርጉም የተባለው ቃል ቀስ በቀስ ተገኘ። በባቢሎን ምርኮ ጊዜ በሀገራቸውና በባቢሎን ይኖሩ የነበሩ አይሁድ የሚናገሩት አራማይክ ነበር። ሕገ ኦሪት (አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት) በምኩራቦች ውስጥ ለምእመናን የሚነበበው በዕብራይስጥ ነበር። ንባቡ በመጀመሪያ በዕብራይስጥ ቋንቋ በኋላም ሕዝቡ በዕብራይስጥ የተነበበውን መገንዘብ እንዲችሉ በአራማይክ ይተረጎም ነበር። (ዛሬም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያ በግዕዝ ተነቦ በኋላ በአማርኛ እንደሚተረጎመው ማለት ነው።)
ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ሕዝቡ የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብ ለመስማት «የውሃ በር» ከሚባለው ቦታ ፊት ለፊት ባለው አደባባይ ይሰበሰቡ እንደነበር ከነህምያ ም 8 ከቁጥር 1-8 እንረዳለን። የሕግ ምሁሩ ዕዝራ ቅዱሳት መጻሕፍትን በዕብራይስጥ ሲያነቡ ሌዋውያኑ (ዕብራይስጥና አራማይክ ስለማያውቁ) ሕዝቡ በዕብራይስጥ የተነበበውን እንዲረዱት የተነበበውን በአራማይክ ቃል በቃል ይተረጉምላቸው ነበር።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ
ከመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራዎች ውስጥ ሰብዓ ሊቃናት (ሴፕቱዋጅንት) የዕብራይስጥ ብሉይ ኪዳን ወደ ግሪክኛ የተመለሰበት የመጀመሪያና በጣም ጥንታዊ ትርጉም ሲሆን ቅ.ል.ክ. ከ285-246 በዳግማዊ በጥሊሞስ ፊላደልፉስ ዘመነ መንግሥት በግብጽ አገር በእስክርድርያ የተተረጎመ ነው። ሰብዓ ሊቃናት /ሴፕቱዋጅንት የሚባለውም 70 የሚል ትርጉም ከነበረው ከላቲን ቃል የተገኘ ነው። ይህም ቁጥር መጽሐፍ ቅዱስን (ብሉይ ኪዳንን) ወደ ግሪክኛ ተርጉመዋል ተብለው የሚታመንባቸውን ሰባ ሁለት የአይሁድ ምሁራንን ያመለክታል።