Friday, February 10, 2012

ጸሎት

Prayer, Education, READ IN PDF
ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በቀዳሚነት የሚያስፈልጉንን እግዚአብሔርንና ክርስቶስን ማወቅ በምሥጢረ-ሥላሴና በምሥጢረ-ሥጋዌ ትምህርታችን ባለፈው ጊዜያት አይተናል። ጸሎትና ለቃሉ መታዘዝ ቀጣይ ጉዳዮች ይሆናሉ። ለዛሬ ጸሎት የሚለውን እናያለን።
ጸሎት ምንድን ነው? ቢባል በአጭሩ ልመና ማለት ነው። እግዚአብሔር ስላደረገልን ነገር ምስጋና፡ እንዲያደርግልን ስለምንፈልገው ነገር ልመና ወደ እርሱ ይቀርባል። ለእስከአሁኑ ጉዳይ ምስጋና ለወደፊቱ ደግሞ ልመና እናቀርባለን። ምነው እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን ያውቀው የለም? ለምን መለመን ያስፈልጋል ቢባል ልመና ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረትን ያመጣል። ለልመና ስንቆም በእግዚአብሔር ፊት ነውና የምንሆነው እርሱ ከእኛ ጋር  እኛም ከርሱ ጋር፡ እንዳለን ይበልጥ ይሰማናል። በእርግጥ እርሱ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ነው። እኛ ግን ከእርሱ ጋር የምንሆነው እርሱን ስናስብ ነው። እርሱን ከምናስብባቸው መንገዶች አንዱ ጸሎት ነው።
ጸሎት የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት እግዚአብሔር አባታችንን በልጅነት መንፈስ የምንጠይቅበት መንገድ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት የአባትና የልጅ ስለሆነ ስንጸልይ አባት ብለን እንድንጠራው ታዘናል።

መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ  ጸልይ፤ ይላል። ማቴ ፮፡፮
እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ። በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ .. ማቴ ፮፡፱
አባት ቅርበትን፡ ነጻነትን፡ ፍቅርን ያሳያል። ስለዚህ እኛም በቀጥታ፡ በነጻነት፡ በፍቅር በልጅ ወግ ስንጠይቀው እርሱም በአባትነት ወግ የምንፈልገውን ሁሉ ሳይሆን የሚያስፈልገንን ይሰጠናል። አባት ለልጁ እሳት ቢለምነው ስለለመነ ብቻ አይሰጠውም። እንደሚጎዳው ከልጁ ይልቅ አባቱ ያውቃል። እግዚአብሔርም ከእኛ ይልቅ ለእኛ ያስባልና የሚያምረንን ሳይሆን የሚያምርብንን፡ በእኛ ሳይሆን በርሱ ጊዜ ይሰጠናል።

ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት መሰላል ነው። መሰላል ወደላይ መውጫ ብቻ ሳይሆን ወደታች መውረጃም ነው። እግዚአብሔር በቃሉ ያናግረናል፡፡ እኛም ለሚያናግረን ጉዳይ መልሰን እርሱን ከምንመልስለት መንገዶች አንዱ ጸሎት ነው። ወይም ደግሞ እኛ እግዚአብሔርን በጸሎት እናናግረዋለን። እርሱም ለምናናግረው ጉዳይ መልስ ከሚሰጥበት መንገዶች አንዱ ቃሉ ነው። ቃሉንም የምናገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው። መናገር አንድ ወገን ብቻ ነው። መነጋገር ግን የሁለቱንም ተሳትፎ ይፈልጋል። እኛ ለእግዚአብሔር የምንናገር እርሱ የማይናገር፡ ወይም እርሱ የሚናገር እኛ የማንናገር አይደለንም። ሁለታችንም የምንነጋገር ነን። እኛ የምንናገረው በጸሎት ነው፡ እርሱ ደግሞ የሚናገረው በቃሉ ነው። መነጋገራችን የተሟላ እንዲሆን ደግሞ መደማመጥ ያስፈልጋል። እርሱ ጆሮን የፈጠረ አምላክ ይሰማል።
«ጆሮን የተከለው አይሰማምን?» መዝ ፺፫ (፺፬)፡፱።
እኛስ ጆሮ የተፈጠረልን እንሰማለን?  የሰውን እንሰማለን፡ የአምላክንስ?። የምንሰማው የሚናገረውን ቃሉን በማንበብ ነው። እርሱም መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እግዚአብሔር የተጻፈው ቃሉ እንደተናገረው ቃሉ እኩል ኃይል አለው። ሰው ደብዳቤ ከሚጽፍልን በቃሉ በቀጥታ ቢያናግረን የላቀ ትኩረት እንሰጣለን። አንድ ሰው አንድን ጉዳይ ጽፎልን ከምናነበው በቃሉ በቀጥታ ቢያናግረን ይበልጥ ኃይል አለው። ለእግዚአብሔር ግን እንደዚያ አይባልም። እግዚአብሔር ሙሴን፡ ክርስቶስ ሐዋርያትን ባናገረበት ኃይል ዛሬም በተጻፈው ቃሉ ያናግረናል። ኃይሉ ፍ          ጹም ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እግዚአብሔርን ማዳመጥ ማለት ነው።
እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ የተናገረውና የሚናገረው ለሁሉም ዘመን ለሁሉም ሰዎች ነው። ለእኛ በዚህ ዘመን ያለውን ትርጉም እንድናገኝ (ለማስተዋል) መጸለይ ይጠበቅብናል። ቃሉን ያስጻፈው መንፈስ ቅዱስ እንዲገልጥልንና ልባችንን እንዲከፍትልን በጸሎት መጠየቅ ዋና ጉዳይ ነው። የእግዚአብሔር ቃል ከጠቢባን የተሰወረ ለየዋሃን የተብራራ ነው። ለማንበብ ከመነሳታችን በፊት የራሳችንን ዕውቀት፡ ማስተዋልና ጥበብ ወደጎን መተው፡ በየዋህነት በንጹሕ ልብ ከጸሎት ጋር መቅረብ አለብን። አንድ ሃሳብ ይዘን ለዚያ ድጋፍ የሚሆን ጥቅስ ፍለጋ መሄድ የእግዚአብሔርን ሃሳብ ለራሳችን ሃሰብ ማብራሪያ ማድረግ በቃሉ መሰናከል እና ማሰናከል ይሆናል።
ቃሉን ለማንበብ ከመነሳታችን በፊት ከእኛ የሚጠበቀው ቀዳሚ ነገር መጸለይ ነው። ይህንም የምናደርገው ራሱ ባዘዘን አምላካዊ ቃል በመተማመን ነው።    
«ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል።» ማቴ ፯፡፯
ከምንለምነውና ከሚሰጠን ነገሮች አንዱ የቃሉን ሙላትና ማስተዋል ነው። እኛ ለመጸለይ ከታመንን እርሱ ለመስጠት የታመነ ነው።
ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለምን አታነቡም? ሲሉ የሚሰጡት መልስ አይገባኝም የሚል ነው። እንዲገባን ማድረግ የሚገባን ግን መጸለይ ነው።
«ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል።» ያዕ ፩፡፭።
የጸሎትን ጥቅም አንባቢው (ምእመኑ) ራሱ ተጠቅሞበት ያየዋል እንጂ ይህን ይመስላል ብሎ መግለጽ አይቻልም። መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት መጸለይ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በዚህ ጽሑፍ መግለጽ ያስቸግራል። አንባቢው ራሱ ጸሎት አድርጎ እንዲያነብና ከዚያም የሚያገኘውን አምላካዊ ምላሽ እንዲያስተውል ከማሳሰብ በቀር እንዲህ ነው ለማለት አንችልም።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣይ የምናየው መታዘዝ የሚለውን ይሆናል።
ይቆየን።

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment