Friday, February 3, 2012

ምሥጢረ-ሥጋዌ (ነገረ-ድኅነት) (ክፍል ፪)

Mistere-Segawe part 2, READ IN PDF
ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ከሚያስፈልጉን ጉዳዮች ቀዳሚዎቹ በእግዚአብሔርና በክርስቶስ ማመን (ምሥጢረ-ሥላሴና ምሥጢረ-ሥጋዌ)፡ መሆኑን በመጥቀስ ምሥጢረ-ሥጋዌን ባለፈው ጽሑፋችን ጀምረናል። በዚህ ክፍል ቀሪውን የክርስቶስን ነገር በአጭሩ እናያለን።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ሰው ሆነ? የሚለውን መሠረታዊ ነጥብ ለማየት ወደ ብሉይ ኪዳን እንሄዳለን። የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አምሳል ከተፈጠረ በኋላ ትእዛዙን ጥሶ በኃጢአት ወደቀ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰው የኃጠአት፡ የሰይጣን፡ የሲኦል ባርያ ሆነ፡፡ ሰው ሁሉ በደለኛ ስለሆነ ሲሞት ሁሉም ወደ ሰኦል መውረድ ጀመረ። ሰው ሁሉ ይድን ዘንድ የሚያስችለው ፍጹም የሆነ ጽድቅ እና መልካም ሥራ  አልተገኘበትም።
«ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥» ሮሜ ፫፡፲፩
 በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር የፈጠረውን፡ ሰው ያበላሸውን ዓለም ለማዳን ልጁን ይልክ ዘንድ ዓለምን ማዘጋጀት ጀመረ። ለዚህም አብርሃምን በመጥራት ከርሱ አንድን ሕዝብ እስራኤልን አዘጋጀ። ከእስራኤልም ከይሁዳ ነገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ። እስራኤል በመካከለኛው ምሥራቅ የምትገኝ የዓለም ማዕከላዊ ሃገር ናት። ኢየሱስ ክርስቶስም የዓለሙ ሁሉ መድኃኒት መድኃኔዓለም ይሆን ዘንድ በዚች በዓለም መካከል በሆነችው ሃገር ተወለደ፡ ተሰቀለ። ሞቶ ተነሳ።

«እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ።» መዝ ፸፬፣፲፪።
ይህ በምድር መካከል ተወልዶ የተሰቀለው የሁላችን መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
«እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።» ማቴ ፩፣፳፩።
ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት ነው።

 እርሱ የሞተው ለእኛ ሕይወትን ለመስጠት ነው። እኛ በኃጢአት ሞትን አመጣን። ሕይወታችን (የዘላለም ሕይወት) ተወሰደችብን። ስለዚህ በውዳሴ ማርያም ዘዓርብ እንደተጻፈው፡
ዘዚኣነ ሞተ ነሥዓ ወእንቲአሁ ሕይወተ ወሀበነ፡ የእኛን ሞት ተቀብሎ የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጠን።
እርሱ ሲሞት ሕይወቱ ትወጣለች። ለእኛ ስናምን ትሰጠናለች። እርሱ ግን ሞቶ አልቀረም። በአምላክነቱ ደግሞ ተነሳ። እኛም እርሱን አርኣያ አድርገን ለዘላለም ሕይወት እንነሳለን።
ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ ቢቀር ኖሮ መዳናችን አይረጋገጥም ነበር። እኛም እንደምንነሳ እርግጠኞች አንሆንም ነበር። እርሱ በሰውነቱ ሞተ በአምላክነቱ ደግሞ  ተነሳ።ስለዚህ እኛ የዳንነው በሰውነቱ ሞት ብቻ ሳይሆን በአምላክነቱ ትንሣኤም ነው። በእምነት የምናገኘው  መዳናችን የሰውነቱ (የሞቱ)  ብቻ ሳይሆን የአምላክነቱም (የትንሣኤውም) ውጤት ነው። መዳናችን የተፈጸመው በክርስቶስ ሰውነትና አምላክነት በተዋሕዶ ነው። ስለዚህ ክርስቶስ አምላክም ሰውም መሆኑን ማወቅ (ምሥጢረ-ሥጋዌ) የመዳናችን መሠረት ነው። ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ፡-
«መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።» የሐዋ ፬፡፲፪ ብሎ የተናገረው። ምክንያቱም አምላክም ሰውም ሆኖ ሁለቱን ያሟላ፡ ሞቶ የተነሳ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ስለሌለ ሊያድነን የሚቻለው እርሱ ብቻ ነው።  
ምሥጢረ-ሥጋዌ ከነገረ-ድኅነት ጋር የተያያዘ ነው። ምሥጢረ-ሥጋዌ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክም ሰውም እንደሆነ የምንማርበት ሲሆን ነገረ-ድኅነት ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና መላውን የሰው ዘር ለማዳን ሞቶ መነሳቱን የምናይበት ነው። መዳናችን የተገኘው በኛ ጥረት ወይም መልካም ሥራ ውጤት ሳይሆን በክርስቶስ ሞት ነው።
ደኅንነትን (መዳንን) በተመለከተ፡
-       መዳናችን የተገኘው በክርስቶስ ሞት ነው፡
-       መዳናችን የምንቀበለው በእምነት ነው፡
-       መዳናችን (እምነታችን) የምንገልጸው ደግሞ በሥራ ነው፡
 የመዳናችንን ጉዳይ ወደፊት በዝርዝር የምናየው ይሆናል።
ቀደም ብለን እንዳየነው በዓለም መካከል የተሰቀለው መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ማዕከል ነው። የሕይወታችንም ማዕከል ነው። ስለዚህ ዋናውን ማዕከል ካልያዝን ዙርያው ሊገባን አይችልም። አንድ መምህር የመጽሐፍ ቅዱስ አስኳል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብሏል። የመጽሐፍ ቅዱስነ ሃሳብ በአንድ ዓረፍተ ነገር አስቀምጡ ቢባልም፡ በወልድ የተፈጠረው ዓለም በወልድ ዳነ። ብሎ መደምደም ይቻላል። የመጽሐፍ ቅዱስን ማዕከላዊ ሃሳብ የሚለግጸው እጅግ ተወዳጅ የሆነው ጥቅስ፡
«በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።»   ዮሐ ፫፡፲፮
እግዚአብሔር ፍቅር እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ፩ዮሐ ፬፡፰። እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑ በተግባር የተገለጸው በሁለት መንገድ  ነው፡-
፩. እግዚአብሔር ወልድ ከታላቅ ክብሩ ወርዶ ሰው በመሆኑ፡ ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ፡ እንደተባለው
፪. ሰው ከሆነ በኋላም እስከሞት በመድረሱ፡ ወአብጽሖ እስከ ለሞት እንደተባለው
እነዚህ ሁለቱ የተገለጹት በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔርንና ፍቅሩን ለማወቅ ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አስፈላጊ ነው ማለት ነው። በሌላም ቦታ እንዲህ ይላል።
«መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።» ዮሐ ፩፡፲፰።
እግዚአብሔርን በብሉይ ኪዳን ሰማነው በሐዲስ ኪዳን ግን አየነው። እንዲያውም ዳሰስንው፡፡ ማየት ከመስማት ይበልጣል። መዳሰስ ደግሞ ከሀሉም ይበልጣል። ተጨባጭነትን ማረጋገጫን ያመልከታል። እግዚአብሔርን  ያየነው የዳሰስነው (ይበልጥ ያወቅነው) በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለምን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነው እግዚአብሔር ነውና፡፡
እንግዲህ በአጠቃላይ እግዚአብሔርን፡ ፍቅሩን፡ ሥራዎቹን፡ ቃሉን፡ መጽሐፍ ቅዱስን በአግባቡ ለመረዳትና በሕይወት ለመጠቀም ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ የመጀመሪያው ተቀዳሚ ጉዳይ ነው።  
የኢየሱስ ክርስቶስ ነገር ተነግሮ ተጽፎ አያልቅም። ባለን ጊዜ ና ዕድሜ ስለርሱ በመጻሕፍት የተጻፈውን የምናውቀውን ሁሉ እንመሰክራለን፡ እንናገራለን። መጽሐፍም፡-
«ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል።» ዮሐ ፳፩፡፳፫።
ብሎአልና።
«ወንድሞች ሆይ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን።» ገላ ፮፡፲፰።
 ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣይ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የሚያስፈልጉንን ቀሪ ነገሮች ጸሎት፡ መታዘዝ የሚሉትን እያየን እንቀጥላለን።
ይቆየን።

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment