Wednesday, February 8, 2012

የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም

Bible Translation Septuagent, READ IN PDF
የትርጉም ሥራ በመጽሐፍ ቅዱስ
መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጽሐፍት ይልቅ በመጀመሪያ ፡ በብዛትና በሁሉም ቋንቋዎች የተተረጎመ አሁንም በፍጥነት እየተተረጎመ ያለ ብቸኛ መጽሐፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ከተጻፈበት ቋንቋ በኋላ በተለያየ ዘመን ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። ከመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራዎች ውስጥ የሰባ ሊቃናት ትርጉም (ሴፕትዋጅንት) የሚባለው በጣም የታወቀ፡ ቀደምት ትርጉም ሲሆን ለሌሎች የዓለም ቋንቋዎች ትርጉም ዋና መነሻ ነው ። ስለዚህ የትርጉም ሥራ ሰፊ ጥናት ካደረገ ከአንድ መጽሐፍ የሚከተለው ቀርቧል።

«በዚያን ጊዜም ኒሳን በተባለው በመጀመሪያው ወር ከወሩም በሀያ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠሩ መርዶክዮስም ስለ አይሁድ እንዳዘዘው ሁሉ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሀያ ሰባቱ አገሮች ላሉ ሹማምትና አለቆች አዛውንትም ለእያንዳንዱም አገር እንደ ጽሕፈቱ ለእያንዳንዱም ሕዝብ እንደ ቋንቋው ለአይሁድም እንደ ጽሕፈታቸውና እንደ ቋንቋቸው ተጻፈ።»  አስ ፰፣፱
ከክርስቶስ ልደት 2100 ዓመት በፊት በባቢሎን የነበረው ንጉሥ ሐሙራቢ ብዙ ጸሐፊዎች ስለነበሩት የንጉሦን አዋጆች በግዛቱ ውስጥ ባሉ በርካታ ቋንቋዎች እየተረጎሙ ሕዝቡ በሚገባ እንዲገዛለት ያደርግ ነበር። በነህምያ ጌዚም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በአምስተኛው መቶ በኋለኛው ክፍል በአይሁድ ዘንድ ልዩ የትርጉም ቅጽ ተዘጋጅቶ ነበር። በመጀመሪያ ይህ ዓይነት ትርጉም የቃል (የስማ በለው ዓይነት) ትርጉም ነበር፤ ሆኖም ቀስ በቀስ አደገና በጽሑፍ ላይ ዋለ። ከዚህም ሥራ ትርጉም የተባለው ቃል ቀስ በቀስ ተገኘ። በባቢሎን ምርኮ ጊዜ በሀገራቸውና በባቢሎን ይኖሩ የነበሩ አይሁድ የሚናገሩት አራማይክ ነበር። ሕገ ኦሪት (አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት) በምኩራቦች ውስጥ ለምእመናን የሚነበበው በዕብራይስጥ ነበር። ንባቡ በመጀመሪያ በዕብራይስጥ ቋንቋ በኋላም ሕዝቡ በዕብራይስጥ የተነበበውን መገንዘብ እንዲችሉ በአራማይክ ይተረጎም ነበር። (ዛሬም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያ በግዕዝ ተነቦ በኋላ በአማርኛ እንደሚተረጎመው ማለት ነው።)
ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ሕዝቡ የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብ ለመስማት «የውሃ በር» ከሚባለው ቦታ ፊት ለፊት ባለው አደባባይ ይሰበሰቡ እንደነበር ከነህምያ ም 8 ከቁጥር 1-8 እንረዳለን። የሕግ ምሁሩ ዕዝራ ቅዱሳት መጻሕፍትን በዕብራይስጥ ሲያነቡ ሌዋውያኑ (ዕብራይስጥና አራማይክ ስለማያውቁ) ሕዝቡ በዕብራይስጥ የተነበበውን እንዲረዱት የተነበበውን በአራማይክ ቃል በቃል ይተረጉምላቸው ነበር።  

የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ
ከመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራዎች ውስጥ ሰብዓ ሊቃናት (ሴፕቱዋጅንት) የዕብራይስጥ ብሉይ ኪዳን ወደ ግሪክኛ የተመለሰበት የመጀመሪያና በጣም ጥንታዊ ትርጉም ሲሆን ቅ.ል.ክ. ከ285-246 በዳግማዊ በጥሊሞስ ፊላደልፉስ ዘመነ መንግሥት በግብጽ አገር በእስክርድርያ የተተረጎመ ነው። ሰብዓ ሊቃናት /ሴፕቱዋጅንት የሚባለውም 70 የሚል ትርጉም ከነበረው ከላቲን ቃል የተገኘ ነው። ይህም ቁጥር መጽሐፍ ቅዱስን (ብሉይ ኪዳንን) ወደ ግሪክኛ ተርጉመዋል ተብለው የሚታመንባቸውን ሰባ ሁለት የአይሁድ ምሁራንን ያመለክታል።
የግሪክ ግዛት የሆነችው የመቄዶንያው ንጉሥ ታላቁ እስክንድር ቅ.ል.ክ. በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያደረገው የግዛት መስፋፋት ግብጽን በመቄዶንያ ግዛት ሥር እንድትወድቅ አድርጓት ነበር። በአዲስ መልክ የተመሠረተችው የእስክንድርያ ከተማ በግሪክ ግዛት ውስጥ በተሰበሰቡ በተለያዩ ሕዝቦች መካከል ግሪክኛ የጽሑፍና የንግግር መግባቢያ ቋንቋ ሆነ። (ዛሬ እንግሊዝኛ የመላው ዓለም ቋንቋ እንደሆነው ማለት ነው።) ግብጽ ሃገር በተለይም እስክንድርያ ከተማ ታላቁ እስክንድርን በተካው በበጥሊሞስ 1ኛ አገዛዝ ወቅት የብዙ አይሁዶች መኖሪያ ሆና ነበር። ስለዚህም የአይሁድ ቅዱሳት መጻሕፍት መኖር በእስክንድርያ ለሚኖሩ የግሪክ ሕዝቦች በቀላሉ የሚታወቅ ነበር።
የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ግሪክኛ ለመተርጎሙ ታሪክ በጣም የታወቀው ምንጭ አሪስትያ ለወንድሙ ለፊሎክራጥስ የጻፈው ደብዳቤ ነው። ይህ ደብዳቤ የግብጽ ንጉሥ ዳግማዊ በጥሊሞስ (ቅ.ል.ክ. 285 – 247) በእስክንድርያ ላቋቋመው አዲስ ቤተ መጻሕፍት ከተቻለ በዓለም ያሉ መጻሕፍትን ሁሉ ለማሰባሰብ ተመኝቶ እንደነበርና ብዙ መጻሕፍትም እንደሰበሰበ ይገልጻል። በጣም ተፈላጊ የሆነው የአይሁድ የሕግጋት መጽሐፍ ቅጅ በቤተ መንግሥቱ ቤተ መጻሕፍት አለመኖሩን ዘግይቶ በመረዳቱ ደብዳቤ ጽፎ እሪስቲያስ ራሱና ሌሎች ያሉበትን የመልእክተኞች ቡድን በኢየሩሳሌም ለሚገኘው ሊቀ ካህናት አልአዛር አነዚህን የአይሁድ መጻሕፍትና ወደ ግሪክኛ መተርጎም የሚችሉ ምሁራንን ወደ እስክንድርያ እንዲልክለት ጠየቀ። ሊቀ ካህናቱም በንጉሡ ጥያቄ ተስማምቶ በሚገባ የተጌጠ የአይሁድን መጽሐፍ ቅዱስና ይህን የሚተረጉሙ ከአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ከእያንዳንዱ ነገድ 6፡ 6 በአጠቃላይ 72 ሊቃውንትን ላከለት። በዚህም ምክንያት ትርጉሙ ሰብዓ ሊቃናት (ሰባው ለሊቃውንት- ሴፕቱዋጅንት) የሚል ስያሜ ተሰጠው።

እነዚህ ሊቃውንት ብሉይ ኪዳንን ከተረጉሙ በኋላ ትርጉሙ ለአይሁድ ካህናት፡ ሽማግሌዎችና ሕዝቡ በእስክንድርያ ተሰብስበው በተገኙበት ለብዙ ቀናት ተነበበ። ከምንጩ ከዕብራይስጡ ጋር ፍጹም ተመሳሳይነት ያለው ሆኖ በመገኘቱ ሁሉም በአድናቆት ተቀበሉት። ንጉሡም በዕብራውያን የሕግ መጽሐፍ በከፍተኛ ደረጃ ተደንቆ ትርጉሙን በጥሩ ጥራዝ አስጠርዞ አስቀመጠው። አይሁድም በየምኩራቦቻቸው እንዲጠቀሙበት የአዲሱ ትርጉም ቅጅዎች እንዲሰጣቸው ንጉሡን ጠይቀው ተሰጥቶአቸዋል። ይህ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ከዚያ በኋላ በተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አስተያየቶችና ትችቶች ቢሰነዘርበትም እስከዛሬ ድረስ ለሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራዎች መሠረት የጣለ፡ ቀደምት ሥራ መሆኑ ግን አይካድም።

ለሰብዓ-ሊቃናት ትርጉም የተሰጡ ምስክርነቶች፡-
 - በእስክንድርያ በሚኖሩ የአይሁድ ማኅበረሰብ በከፍተኛ ክብር ተይዞ እውቅና አግኝቷል። በኋላም ከእስክንድርያ ውጭ ተበትነው ላሉ አይሁድ ሁሉ ተሰራጭቷል።
 - በግሪክ ቋንቋ በፍልስፍናና በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ ዕውቀት የነበረው ፊሎ የተባለው ምሁር ለሰብዓ ሊቃናት ከፍተኛ ግምት ስለነበረው ፦ «… በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ከዋናው ምንጭ ከዕብራይስጥ የተተረጎመና ትክክለኛ መጽሐፍ ነው።» የሚል ምስክርነት ሰጥቷል።
 - በ1ኛው ክፍለ-ዘመን ቅ.ል.ክ የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ሰብዓ ሊቃናትን ይጠቀምበት ነበር።
 -  ጠርጥልያኖስ፡ ቅዱስ አውግስጢኖስ እና ሰማዕቱ ጀስቲን የሰብዓ ሊቃናት ተርጓሚዎች በእግዚአብሔር መንፈስ አነሳሽኘት እንደተረጎሙት አምነው ተቀብለውታል።
 - ቅዱስ ኢሬኒዮስ እና የእስክንድርያው ቅዱስ ቀሌምንጦስ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል። « ሲተረጉሙ እርስ በርስ አልተማከሩም። በተለያዩ ክፍሎች በነጠላ ወይም በቡድን ሆነው ነው የተረጎሙት። ትርጉሞቻቸውም ሲወዳደሩ ከመተርጎሚያው መጽሐፍና ከእያንዳንዱ ጋር በስሜትም በአገላለጽም የሚስማሙና የማይለያዩ ሆነው ተገኝተዋል።
ይህ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ከክርስቶስ ልደት በኋላ ለክርስትና መስፋፋት ዋና ምንጭ ሆኖ አገልግሎአል። በመጀመሪያዎቹ አንድ ሺ ዓመታት ክርስትና በየቦታው ሲሰራጭ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሲተረጉሙ በሰብዓ ሊቃናት መሠረትነት ነበር። ስለሆነም ብሉይ ኪዳን ወደ ቅብጥ፡ ግእዝ፡ የጥንቱ ላቲን፡ አረብኛ፡ አርመን፡ ጆርጂያና ወደ ጥንቱ ስላቮኒክ የተተረጎመው ከሰብዓ ሊቃናት ነበር። በአሁኑም ጊዜ ሁሉም የምሥራቅና የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የሚጠቀሙት ሰብዓ ሊቃናትንና ከእርሱ የተገኙ ትርጉሞችን ነው።

ምንጭ፡- በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በግእዝ ቋንቋ
በቀ/ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል
አዲስ አበባ 2000 ዓ/ም፡

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment