Lekalu Metazez, read in pdf here
ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በዋናነት የሚያስፈልጉንን እግዚአብሔርንና ክርስቶስን ማወቅ በምሥጢረ-ሥላሴና በምሥጢረ-ሥጋዌ
፣ እንዲሁም ጸሎት የሚሉትን ርእሶች ባለፉት ተከታታይ ትምህርታችን ማየታችን ይታወሳል። ቀጣዩ ዋና አስፈላጊ ጉዳይ ለቃሉ መታዘዝ የሚለው ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው፡ ለታሪክ፡ለምርምር፡ ለጠቅላላ ዕውቀት፡ ለግንዛቤ፡ ወይም ለመረጃ አይደለም። የተጻፈበት ቀዳሚ
ዓላማ ለሕይወት ነው። ቃሉ በሁለት ወገን እንደተሳለ ሰይፍ ላመኑበት መዳንን ላላመኑት ደግሞ ፍርድን የሚያስከትል እንዲሁም ተናጋሪውንም አድማጩንም የሚነካ ኃይል ያለው፡ እና የሚሰራ ነው።
የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር
ቃል ነው። ኤፌ ፮፡፲፯
የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ
ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም
እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ ዕብ ፬፡፲፪
መጽሐፍ ቅዱስን መታዘዝ አለብን ስንል መጽሐፉ ከዳር እስከ ዳር ይህን አድርግ ይህን አታድርግ በሚሉ ትእዛዛት የተሞላ
መጽሐፍ ነው ማለታችን አይደለም። እግዚአብሔር እንድንታዘዘው የሚፈልገውን ሃሳብ በቃሉ ውስጥ በተለያየ መንገድ አስቀምጧል። ይህንንም
ማስተዋል የኛ ድርሻ ይሆናል።
« እግዚአብሔር በአንድ መንገድ በሌላም ይናገራል ሰው ግን አያስተውለውም።» ኢዮ ፴፫፥፲፬፤
እግዚአብሔር ከሚያስተምርባቸው መንገዶች የሚከተሉት ዋናዎቹ ናቸው።