በመጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን የሚገኙት
መጻሕፍት በሥነጽሑፋዊ ይዘታቸው ከአራት እንደሚከፈሉ በገለጽነው መሠረት ካሁን ቀደም የመጀመሪያዎቹን ሁለቱን ማለትም የኦሪት እና
የታሪክ ክፍል የሚሉትን በየተራ አይተናል። ፫ኛው የብሉይ ኪዳን ክፍል የሆነው የመዝሙርና የጥበብ መጻሕፍት ጠቅለል ያለ ዳሰሳ ለዛሬ
እናያለን።
የመዝሙርና የጥበብ መጻሕፍት የቅኔ፣
የግጥም መጻሕፍት በመባል የሚታወቁ ሲሆን እነዚህም በሦስት ጸሐፍያን- በኢዮብ፣ በዳዊትና በሰሎሞን የተጻፉት አምስት መጻሕፍት መጽሐፈ-ኢዮብ፣
መዝሙረ-ዳዊት፣ (የመዝሙር መጻሕፍት) መጽሐፈ-ምሳሌ፣ መጽሐፈ-መክብብ እና መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን (የጥበብ መጻሕፍት) ናቸው።
ኢዮብ በየትኛው ዘመን ይኖር እንደነበረ በግልጥ የተቀመጠ ነገር የለም። ብዙ መምህራን ኢዮብ በቀደምት አበው በነያዕቆብ እና በነኤሳው
ዘመን የነበረ መሆኑን ይናገራሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት (ከ፷፮ቱ) መጽሐፈ ኢዮብ ቀደምት ሲሆን በ፹፩ዱ መጽሐፈ ሄኖክ የመጀመሪያው
መሆኑ ይታወቃል። ዳዊትና ሰሎሞን ከሳኦል ቀጥሎ እስራኤልን የገዙ የመጀመሪያዎቹ ነገሥታት ሲሆኑ የቅኔና የመዝሙር መጻሕፍቶቻቸው
እስራኤላውያን ምድረ-ርስት ከነዓንን ከወረሱ በኋላ በነበረው የተረጋጋ ዘመን ማለትም በመጽሐፈ-ሳሙኤል እና መጽሐፈ-ነገሥት ዘመን
ታሪክ ውስጥ የተጻፉ ናቸው።
መዝሙር/ግጥም በቀላሉ እና በሚስብ
መልኩ መልእክትን ለማስተላለፍ የሚያገለግል አንድ የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ነው። እግዚአብሔር ቃሉንና መልእክቱን ለሰዎች ለማስተላለፍ
ከተጠቀመበት ዘዴ አንዱ በግጥም መልክ ማድረጉ ነው። ከስድ ንባብ ይልቅ ግጥም ምን ያህል እንደሚቀል መልእክቱን በቀላሉ ለመረዳት
እንደሚያስችል በተለይም ግጥሙ ሰምና ወርቅ ለበስ ቅኔያዊ ከሆነ በጥቂት ቃላት ብዙ ሃሳብ መግለጽ እነደሚቻል ሁላችን በአማርኛ ቋንቋችን
እናውቀዋለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግጥም/በመዝሙር መልክ የተጻፉ መጻሕፍት እነዚህ የመዝሙርና የጥበብ የተባሉት አምስቱ መጻሕፍት
ብቻ አይደሉም። በኦሪትና በታሪክ እንዲሁም በትንቢት መጻሕፍት ውስጥ በተለያዩ ምዕራፎች ግጥም/መዝሙሮችን እናገኛለን። እንዲያውም
የብሉይ ኪዳን አንድ ሦስተኛው መዝሙር/ግጥም እንደሆነ ይነገራል። እነዚህ የመዝሙር መጻሕፍት በመጀመሪያ በተጻፉባቸው ቋንቋዎች ግጥም
ስለሆኑ ቤት ይመቱ ነበር። ወደ ሌላ ቋንቋ ሲተረጉሙ ግን ቤት መምታት እንዳልቻሉ መምህራን ይናገራሉ።
የመዝሙርና የቅኔ መጻሕፍትን ከሌሎች
በስድ ንባብና በታሪክ መልክ ከተጻፉት መጻሕፍት በተለየ መልኩ ማንበብና መረዳት ይጠይቃል። መቼም አንድ ገጣሚ የሚጽፍልንን ግጥም
በግጥም ደንብ ካላየነው ወይም በስድ ንባብ አካሄድ ብናነበው ውበቱንም፡ መልእክቱንም እናጠፋዋለን። ምናልባት ገጣሚውም ቢሰማን ቅር
ይለዋል። የሚከተለውን ግጥም እንመልከት።
አብ አልሰጠኝ ብየ ምነው መናደዴ፣
ለወልድ አልነግርም ወይ ለሥጋ ዘመዴ።
ለወልድ አልነግርም ወይ ለሥጋ ዘመዴ።
ይህ ግጥም አጻጻፉ ፡ በየስንኙ (በየመስመሩ) ቤት በመምታት- ቤት በመድፋት፤ አነባበቡ በተለየ ቅላጼ ና በማስረገጥ፣ መልእክቱም ቅኔያዊ ስለሆነ በሰምና ወርቅ መሠረት ልናነበው ልንረዳው ያስፈልጋል። ስለዚህ የግጥም/የመዝሙር መጻሕፍትን ማንበብ፣ መተርጎም፣ እና መረዳት ያለብን በግጥም ደንብ መሠረት ሊሆን ይገባል። ይህን ግጥም ወደ ሌላ ቋንቋ እንተርጉመው ብንል ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን፡ ውበቱም እንደሚጠፋ፣ መልእክቱም በአግባቡ ሊተላለፍ እንደማይችል ግልጽ ነው። ከዚህም ጋር የግጥም አጻጻፍ ደንብ በየቋንቋው የተለያየ መሆኑ ነገሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል። ይሁንና ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ እነዚህን መጻሕፍት በምናነብበት ጊዜ በተቻለ መጠን በግጥም /በመዝሙር የሥነ-ጽሑፍ አግባብ መሠረት ልናነባቸውና ልንተረጉማቸው እንደሚገባ አስቀድመን ማወቅ አለብን።