ጥያቄ ፪- ዕጸ-በለስ ባትኖር አዳም አይሳሳትም ነበር? እግዚአብሔር ለምን ዕጸ-በለስን ፈጠረ? ወይም ለምን እንዳይበላት ከለከለ?
እግዚአብሔር በገነት የፈጠራቸው ዛፎች ከሰው ጋር ባላቸው ግንኙነት አንጻር በጥቅሉ ፬ ዓይነት እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እነዚህም በዘፍ ፪፡፱ የተጠቀሱት-
፩ ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፥ ፪ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ
፫ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፥ ፬ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ
የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ለማየትና ለመብላት የተፈጠሩት ብዙ ሲሆኑ የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ግን አንድ አንድ ብቻ ናቸው። የሕይወት ዛፍ ዕጸ-ሕይወት ትባላለች። ዕጽ ማለት ተክል ሲሆን በብዙ ቁጥር ሲነገር ዕጽዋት ይሆናል። መልካሙንና ክፉን የሚያስታውቀው ዛፍ ዕጸ-በለስ ትባላለች። በለስ ቅጠሉ ሰፋፊ የሆነ ነጭ ደም ያለው ፍሬው የሚበላ አጭር ዛፍ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ይናገራል። በለስ በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ተጠቅሶአል። ለአብነት ያህልም፡-
«እግዚአብሔርም፦ ኤርምያስ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። በለስን አያለሁ እጅግ መልካም የሆነ መልካም በለስ፥ ከክፋቱም የተነሣ ይበላ ዘንድ የማይቻል እጅግ ክፉ የሆነ ክፉ በለስ ነው አልሁ።….» ኤር ፳፬፡ ፪-፫።
እግዚአብሔር አዳምን እንዳይበላ የከለከለው ዛፍ ይህ እጸ-በለስ በባሕርይው/በተፈጥሮው ከሌሎች እጽዋት የተለየ የሚያደርገው ምንም ነገር የለም። እንደማንኛውም ተክል ነው። ምናልባት የተለየ የሚያደርገው ትዕዛዝ የወደቀበት መሆኑ ብቻ ነው። ስለዚህ ጥያቄአችንን እግዚአብሔር ዕጸ-በለስን ለምን ፈጠረ? ከሚሆን ለምን ከለከለ? ቢባል ይሻላል።
|
ዛፊቱ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀው ዛፍ ተብላ ተጠቅሳለች። ይህ ማመዛዘንን የሚያመለክት የሰው ጠባይ ነው። ይህን የሰውን ጠባይ ከሚያመላክት አቅጣጫ እግዚአብሔር አዳም ዕጸ-በለስን እንዳይበላ የከለከለው በ፫ ምክንያት ነው፡-
|