Friday, November 25, 2011

የጥያቄ ፪ መልስ


ጥያቄ -  ዕጸ-በለስ  ባትኖር አዳም አይሳሳትም ነበር?   እግዚአብሔር ለምን ዕጸ-በለስን ፈጠረ? ወይም ለምን እንዳይበላት ከለከለ? 

እግዚአብሔር በገነት የፈጠራቸው ዛፎች ከሰው ጋር ባላቸው ግንኙነት አንጻር በጥቅሉ ፬ ዓይነት እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እነዚህም በዘፍ ፪፡፱ የተጠቀሱት-
 ፩ ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፥              ፪  ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ
 ፫ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፥  ፬  መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ
የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ለማየትና ለመብላት የተፈጠሩት ብዙ ሲሆኑ የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ግን አንድ አንድ ብቻ ናቸው። የሕይወት ዛፍ ዕጸ-ሕይወት ትባላለች። ዕጽ ማለት ተክል ሲሆን በብዙ ቁጥር ሲነገር ዕጽዋት ይሆናል። መልካሙንና ክፉን የሚያስታውቀው ዛፍ ዕጸ-በለስ ትባላለች። በለስ ቅጠሉ ሰፋፊ የሆነ ነጭ ደም ያለው ፍሬው የሚበላ አጭር ዛፍ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ይናገራል። በለስ በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ተጠቅሶአል። ለአብነት ያህልም፡-
«እግዚአብሔርም፦ ኤርምያስ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። በለስን አያለሁ እጅግ መልካም የሆነ መልካም በለስ፥ ከክፋቱም የተነሣ ይበላ ዘንድ የማይቻል እጅግ ክፉ የሆነ ክፉ በለስ ነው አልሁ።….» ኤር ፳፬፡ ፪-፫።
እግዚአብሔር አዳምን እንዳይበላ የከለከለው ዛፍ ይህ እጸ-በለስ በባሕርይው/በተፈጥሮው ከሌሎች እጽዋት የተለየ የሚያደርገው ምንም ነገር የለም። እንደማንኛውም ተክል ነው። ምናልባት የተለየ የሚያደርገው ትዕዛዝ የወደቀበት መሆኑ ብቻ ነው። ስለዚህ ጥያቄአችንን እግዚአብሔር ዕጸ-በለስን ለምን ፈጠረ? ከሚሆን ለምን ከለከለ? ቢባል ይሻላል።
ዛፊቱ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀው ዛፍ ተብላ ተጠቅሳለች። ይህ ማመዛዘንን የሚያመለክት የሰው ጠባይ ነው። ይህን የሰውን ጠባይ ከሚያመላክት አቅጣጫ እግዚአብሔር አዳም ዕጸ-በለስን እንዳይበላ የከለከለው በ፫ ምክንያት ነው፡-




፩. ከእርሱ በላይ ፈጣሪ (ገዢ) የሆነ ጌታ እንዳለ እንዲያስታውስ፡፡ አዳም ሁሉንም ግዛ ንዳ ተብሎ ያለገደብ ቢለቀቅ እንደ ዲያብሎስ ከኔ በላይ ማን አለ? ብሎ ወደ ስህተት ይገባ ነበር። ኢሳ ፲፬፡ ፲፪-፲፭። ነገር ግን ሁልጊዜ በገነት ሲዘዋወር እጸ-በለስ ጋ ሲደርስ ያቺን እንዳይበላ የከለከለው ከርሱ በላይ የሆነ ጌታ ፈጣሪ እንዳለ ያስታውሳል።
፪. እርሱ ከእንስሳት በላይ የሆነ፡ አሳቢ አገናዛቢ አእምሮ እንዳለው እንዲገልጽ ነው። አሳቢነት (ለባዊነት) ሰው ከእንስሳት የሚለይበት ባሕርይ ነው። አዳም ሁሉንም ብላ ቢባል ከእንስሳት በምን ይለያል? እንስሳት ሥራቸው መብላት ብቻ ነውና።ነገር ግን አትብላ የተባለውን በማስታወስ ከእንስሳት የላቀ ማንነት እንዳለው ያስታውቃል።
፫. የኑሮ መመሪያ ሆኖ ተሰጥቶታል። ለመኖር ሌሎችን ተክሎች ብላ የሚል፡ ላለመሞት ደግሞ ይህችን አትብላ የሚል የኑሮ መመሪያ (ትዕዛዝ) ሆኖ ተሰጥቶታል።  «ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።» ዘፍ ፪፡፲፯።  «ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እግዚአብሔር አለ፦ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም።» ዘፍ ፫፡፫።
እንግዲህ እግዚአብሔር አዳምን ዕጸ-በለስን እንዳይበላ የከለከለው ነፍጎት/ተመቅኝቶት አይደለም። ለራሱ ለአዳም ጥቅም ሲባል ነው። አዳምም ዕጸ-በለስን እንዲበላ የሚያደርግ ምክንያት አልነበረውም። የሚበላው አላጣምና። ከላይ እንዳየነው ለተገዢነቱ መግለጫና ለአሳቢነቱ (ለባዊነት-የነፍስ ባሕርይ) ማሳያ የተሰጠው ነው። ሥጋ ያለመብል አትቆምም። ስለዚህ ለሥጋው ሌሎችን ብላ የሚል ትዕዛዝ ሲሰጠው  ለነፍሱ ግን ዕጸ-በለስን አትብላ የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቶታል። ነፍስ የምትቆመው በመብላት አይደለም። በነፍስ ዘላለማዊ መኖሪያ በሰማይ ቤት መብል መጠጥ የለም።
እንግዲህ ችግሩ ያለው ከዕጸ-በለስ ሳይሆን ከአመለካከቱ ፡ከተገዢነቱ መግለጫ ፈቃደኝነት፡ ከአሳቢነቱ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ዕጸ-በለስ ባትኖር አዳም አይሳሳትም ማለት አንችልም። ዕጸ-በለስ በአዳም ያሳደረችው አንዳች ተጽዕኖ አልነበረምና። ጎትታ እንዲበላት አላደረገችም።   እግዚአብሔርም አዳም ዕጸ-በለስን እንዳይበላ አጥር አላስቀመጠም ወዶ እንዲታዘዘው ፈልጎአልና። ሰይጣንም አዳምን (እባብ ሔዋንን) አፋቸውን ይዞ  በግድ አላጎረሳቸውም፡ በማግባባት አታለላቸው እንጂ።
ዕጸ-በለሰ መብላትን በተመለከተ አዳም ሁለት ተቃራኒ ነገሮችን ሰምቷል።
…..በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።  ዘፍ ፪፡፲፯--- እግዚአብሔር
………………ሞትን አትሞቱም።      ዘፍ ፫፡፬--- እባብ (ሰይጣን)
አዳም በተሰጠው ነጻ ፈቃድ በወሰደው ምርጫ ከእግዚአብሔር ይልቅ የሰይጣንን (የእባብን) ቃል አምኖ ተቀብሎ በገዛ እጁ በላ። ስለሆነም ራሱ ተጠያቂ ነው እንጂ ዕጸ-በለስ፡ እግዚአብሔር ወይም ሰይጣን ተጠያቂ አይደሉም።

ተጨማሪ ሃሳብ፡ ማብራሪያ ወይም ጥያቄ ካለ ከዚህ ጽሑፍ ስር comments የሚለውን በመጫን post comment በሚለው ሥር ማቅረብ ይቻላል።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ሃሳብ ይሰጥበትና እንቀጥላለን። ካልሆነ ወደ ሌላ ጥያቄ እናልፋለን።


No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment