Friday, November 11, 2011

-የመጽሐፍ ቅዱስ አከፋፈል


የመጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ታላላቅ ክፍሎች የሆኑትን ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ስያሜና አጠቃላይ ይዘት ባለፈው ጽሑፋችን አይተናል። እነዚህ ሁለቱ ኪዳናት ያሉበት ታላቅ መጽሐፍ ለማጥናት እንዲረዳን መከፋፈል ደግሞ ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስን  በተለያዩ መንገዶች መከፋፈል ይቻላል።

፩. በተጻፉበት ዘመን
-      በሕገ-ልቦና ዘመን የተጻፉ፡- እንደ መጽሐፈ ኢዮብ
-      በሕገ-ኦሪት ዘመን የተጻፉ፡- እንደ ዘፍጥረት፡ ዘጸአት…
-      በምርኮ ዘመን የተጻፉ፡- እንደ ትንቢተ ዳንኤል
-      ወዘተ…
፪. በጸሐፊዎቻቸው፡
ለምሳሌ፡--የሙሴ፡ የኢያሱ… የዮሐንስ፡ የጳውሎስ… መጻሕፍት
፫. በተጻፉላቸው ሰዎች፡
-      ለግለሰብ የተጻፉ፡-  እንደ ቲቶ፡ ፊልሞና…
-       ለሕዝብ/ለአይሁድ/ የተጻፉ፡-  እንደ ማቴዎስ ወንጌል
-      ለሁሉም ሰው የተጻፉ፡-  እንደ ዮሐንስ ወንጌል   ወዘተ…
፬. በተጻፉበት ቦታ፡
-      በሲና ተራራ (በበረሃ) የተጻፉ፡- እንደ ዘፍጥረት - ዘዳግም
-      በምርኮ (በባቢሎን) የተጻፉ፡- እንደ ትንቢተ ዳንኤል፡ ሕዝቅኤል
-      በእስር ቤት የተጻፉ፡ እንደ ኤፌሶን፡ ፊልጵስዩስ…
-      ወዘተ…
በእነዚህና በተመሳሳይ መንገዶች መከፋፈል ይቻላል። ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን እንዲመቸን የሚከተለውን አንድ ዓይነት አከፋፈል እንከተላለን።


«በምድር ላይ እንደ ተፈተነ ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ ብር                      የእግዚአብሔር ቃላት የነጹ ቃላት ናቸው። » መዝ ፲፩ (፲፪)፡ ፮
« በዙፋኑ ላይም በተቀመጠው በቀኝ እጁ ላይ በውስጥና በኋላ የተጻፈበት በሰባትም ማኅተም የተዘጋ መጽሐፍን አየሁ።» ራእ ፭፡፩
ሰባት ቁጥር በእስራኤላውያን ፍጹም የሆነ ነገርን ያመለክታል። በመጽሐፍ ቅዱስ በሰባት የሆኑ ብዙ ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል።  ሰባቱ የአይሁድ በዓላት ዘሌ፳፫፡ አስ ፱ ፡ ሰባቱ ከዋክብት ኢዮ ፴፰፡ ሰባቱ አብያተ-ክርስቲያናት ራእ ፪-፫
በዚህ መነሻነት የመጽሐፍ ቅዱስን አከፋፈል በሰባት ደረጃዎች  ማስቀመጥ እንደሚቻል ከአንድ መምህር ያገኘሁትን ቀጥሎ አቀርባለሁ።
ይህ አከፋፈል ከላይ ወደ ውስጥ የሚዘልቅ፡ አንዱ በአንዱ ውስጥ የሚጠቃለልበት ፯ ደረጃዎች ናቸው።
ኪዳን - ሥነ ጽሑፍ - መጽሐፍ - ምዕራፍ - ቁጥር - ቃል - ፊደል
፩. ኪዳን፡ ትልቁ አከፋፈል ሲሆን እነዚህም ኪዳናት ሁለት ናቸው
-      ብሉይ ኪዳን
-      አዲስ ኪዳን
፪. ሥነ-ጽሑፍ   በሥነ-ጽሑፍ ይዘት ከኪዳናቱ ሥር ከ፰ ይከፈላል።
ብሉይ ኪዳን፡ ከ፬ ይከፈላል
-      ሕግ፡ - ከኦሪት ዘፍጥረት - ኦሪት ዘዳግም --- ፭ መጻሕፍት
-      ታሪክ ፡- ከመጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ- መጽሐፈ አስቴር-- ፲፪ መጻሕፍት
-      ጥበብ፡-  ከመጽሐፈ ኢዮብ- መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን-- ፭ መጻሕፍት
-      ትንቢት፡- ከትንቢተ ኢሳይያስ - ትንቢተ ሚልክያስ---፲፯ መጻሕፍት
አዲስ ኪዳን ከ፬ ይከፈላል
-      ወንጌል፡-  ከማቴዎስ ወንጌል- ዮሐንስ ወንጌል---፬ መጻሕፍት
-      ታሪክ፡-  የሐዋርያት ሥራ-- ፩ መጽሐፍ
-      መልእክት፡-  ከ ወደሮሜ ሰዎች- የይሁዳ መልእክት--፳፩ መጻሕፍት
-      ትንቢት፡-  የዮሐንስ ራእይ---፩ መጽሐፍ
፫. መጽሐፍ፡- መጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ መጻሕፍት ስብስብ ነው። በየሥነ-ጽሑፋዊ ክፍፍላቸው ሥር ከላይ እንዳየነው የተለያዩ መጻሕፍት አሉ።
እያንዳንዱ መጽሐፍ በየራሱ ሙሉ ነው። እያንዳንዱ መጽሐፍ ከሌላው ጋር የተሳሰረ ነው።  
በአብዛኛው ዓለም ተቀባይነት ያለው ብሉይ ኪዳን ፴፱፡ አዲስ ኪዳን ደግሞ ፳፯ በጠቅላላ ፷፮ መጽሐፍ ነው። የኛ ቤተ ክርስቲያን ፲፭ መጻሕፍትን ጨምራ በአጠቃላይ ፹፩ መጻሕፍት ትቀበላለች።
፬. ምዕራፍ፡-  በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኙት እያንዳንዱ መጽሐፍ በምዕራፍ የተከፋፈለ ነው። ምዕራፍ ያስፈለገው ለጥናት፡ ለንባብ እና ለአቀራረብ እንዲመች ነው።
ለመጽሐፍ ቅዱስ የምዕራፍ ከፍፍል የተደረገው በእንግሊዝ ሃገር በስቲፈን ላንግተን   በ1928 ዓ/ም ነው።
ብሉይ ኪዳን 929፡ አዲስ ኪዳን 260 በጠቅላላ መጽሐፍ ቅዱስ 1189 ምዕራፎች አሉት።
፭.ቁጥር ፡- የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች ደግሞ በቁጥር ተከፋፍለዋል። ይህም ያስፈለገው አንድን ድርጊት / ሃሳብ በቀላሉ ለመጥቀስ፡ ለማገናዘብ፡ ለማመሳከር እንዲረዳ ነው። የተለያዩት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የሚተሳሰሩት በምዕራፍና በቁጥር ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ የግርጌ ማስታወሻውን ይመልከቱ።
ለመጽሐፍ ቅዱስ የቁጥር ክፍፍል የተደረገው በፈረንሳይ ሃገር ለብሉይ ኪዳን በሮበርት ናታን በ1448 ዓ/ም ሲሆን ለሐዲስ ኪዳን ደግሞ በሮበርት ስቲፈንስ በ1551 ዓ/ም ነው።
ብሉይ ኪዳን 23,214 አዲስ ኪደን 7,959 በድምሩ መጽሐፍ ቅዱስ 31,173 ቁጥሮች አሉት።
፮.ቃል፡-  ቃላት የአእምሮን ሃሳብ የሚገልጹ የቋንቋ መዋቅሮች ናቸው። እግዚአብሔር ሃሳቡን የገለጸው የሰውን ቋንቋ ቃላት በመጠቀም ነው። እግዚአብሔር የሃሳቡን ዘላለማዊነት ዋስትና የሰጠውም በቃል ደረጃ ነው።  «ሰማይና ምድር ያልፋሉ፡ ቃሌ ግን አያልፍም።» ማቴ ፳፬፡፴፭።            «የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል።» ፩ጴጥ ፩፡፳፭።
መደዳውን ሲቆጠር በመጽሐፍ ቅዱስ በጠቅላላ 773,746 ቃላት አሉ። ሳይደጋገሙ ያሉት የተለያዩ ቃላት ግን ባጠቃላይ 8,000 ናቸው። ታዋቂው ጸሐፊ ሼክስፔር 25,000 ቃላት እንደተጠቀመ ይነገራል። እግዚአብሔር ከሼክስፔር ባነሰ በጥቂት ቃላት የበለጠ በርካታ ሃሳብ አስተላልፎአል።
፯. ፊደል፡ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ክፍፍል ፊደል ነው። ፊደላት ድምጾችን ወክለው በመገኘት ቃላትን የሚፈጥሩ ናቸው። የፊደል ለውጥ የቃል ብሎም የሃሳብ/የትርጉም ለውጥ ስለሚያመጣ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ሳይፈጸም እንደማይቀር ማረጋገጫ የሰጠው የፊደልን እና የነጥብን ዋጋ በመናገር ነው።
«እውነት እላችኋለሁ፡ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ከሕግ አንዲት የውጣ (ፊደል) ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፡ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ።» ማቴ ፭፡፲፰።
እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስ ከነጥብ እና ከፊደል አንስቶ በየደረጃው የተዋቀረ የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ሃሳብ የያዘ፡ በዓለማችን፡ በሕይወታችንም  በሁሉም መለኪያዎች ትልቁን ሥፍራ የያዘ ግሩም ድንቅ መጽሐፍ ስለሆነ በጥንቃቄና በማስተዋል ልናጠናው ይገባል።
አከፋፈሉን በዚህ መልኩ ካየን፡ እስካሁን በተከታታይ ያየነው እንደ መግቢያ ሆኖ ወደ ዝርዝር ጥናታችን ከማለፋችን በፊት ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚረዱን መመሪያዎችን ማየት ያስፈልጋል።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣዩ ጽሑፋችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መመሪያዎችን እናያለን።
 ---------------ይቆየን----------------

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment