Tuesday, April 24, 2012

ትንሣኤና ሕይወት

Resurrection and Life, read in pdf here
«ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤» ዮሐ ፲፩፣፳፭
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ዋናው ዓላማ ለሕይወት እንደሆነ ራሱ ባለቤቱ ይነግረናል። ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል አደረገ ስንል የሞት ተቃራኒ የሆነውን ሕይወትን ሰጠን ማለታችን ነው። ከትንሣኤ ቀጥሎ ያለው ሕይወት እርሱም ሞት የማይከተለው የዘላለም ሕይወት ነው። ትንሣኤ እና ሕይወት።
ሞት ለዘመናት አስፈሪ ሆኖ የኖረ፡ ሁሉንም የሰው ዘር የተቆጣጠረ፡ መፍትሔም መድኃኒትም ያልተገኘለት፡ ነበር። አሁንም እንኳ መንግሥታት ስለሞት ለመነጋገር አጀንዳ ይዘው አያውቁም፡ ተመራማሪዎች የሞትን መድኃኒት ለመፈለግ ጥናት አድርገው አያውቁም። ሞት ሁሉንም ዝም ያሰኘ፡ ሁሉንም ጠቅልሎ የገዛ የምድራዊው ኑሮ የመጨረሻው ባለሥልጣን ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ በሞተ ጊዜ ግን ሁሉ ተለወጠ። መድኃኒት ተገኘ፡፡ ለሞትም ሞት ታዘዘ። ይሄውም ትንሣኤ ነበረ።
ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደረገው በሌላ በምንም ነገር ሳይሆን በሞቱ መሆኑ ያስገርማል። ሰው በቁሙ በሕይወት እያለ ብዙ ታላላቅ ነገሮችን ሊሠራ ይችላል። ከታመመ ምናልባት ጥቂት ነገሮችን ይሠራል። ከሞተ በኋላ ግን አንዳች ነገር ሊሠራ አይቻለውም። ሞት የሰው ልጆች የመጨረሻው ደካማ ባሕርይ፡ ምንም ሊሠራበት የማይችል ነው። አሁንም ሞት የሰው ልጆችን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረ የመጨረሻው ኃይለኛ ጉዳይ ነው። ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በጣም ኃያል የሆነውን ሞትን ድል ያደረገው በጣም ደካማ በሆነው ባሕርያችን በሞት ነው። እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በድካማችን ኃያሉን ጠላታችንን ሞትን ድል አደረገው።  «ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና»  ፩ቆሮ ፩፡፳፭።