ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ከሚያስፈልጉን ጉዳዮች ቀዳሚዎቹ በእግዚአብሔርና በክርስቶስ ማመን (ምሥጢረ-ሥላሴና ምሥጢረ-ሥጋዌ)፡ መሆኑን በመጥቀስ ምሥጢረ-ሥላሴን ባለፈው ጽሑፋችን በጭሩ አይተናል። በዚህ ክፍል በክርስቶስ ስለማመን የምንማርበትን ምሥጢረ-ሥጋዌን እንዲሁ አጠር አድርገን እናያለን።
ሥጋዌ የሚለው ቃል ተሠገወ- ሥጋን ለበሰ፡ ሰው ሆነ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ነው። ምሥጢር ማለት የማይነገር ሳይሆን የማይመረመር ለማለት ነው። ቀደም ሲል በምሥጢረ-ሥላሴ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ብለን ካየናቸው ከሦስቱ አካላት አንዱ የሆነው ወልድ አዳምንና የሰውን ልጅ ለማዳን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ለብሶ ሰው መሆኑን የምናይበት ትምህርት ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን እና እንዴት ሰው ሆነ?
ለምን የሚለውን ወደታች እናያለን። እንዴት ለሚለው ግን ከድንግል ፡ያለወንድ ዘር፡ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ብለን ከመግለጽ በቀር ሰማይና ምድር የማይችሉት የማይወሰነው አምላክ እንዴት እንደተወሰነ፡ ለመመርመር አንችልም። ምሥጢር ያሰኘውም ይህ ነው። ለምን ሰው ሆነ? የሚለው ምሥጢር አይደለም፣ ሊነገርና ሊመሰከርለት የሚገባ ግልጽ የምሥራች ቃል ነው። ይሄውም እርሱ ሞቶ እኛን ለማዳን ነው።
ወልድ ሰው ከመሆኑ በፊት አምላክ ብቻ ነው። ሥጋን ለብሶ ሰው ከሆነ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ በአንድነት(በተዋሕዶ) አምላክም ሰውም ይባላል። ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና ሰው አይደለም፡ አምላክም ሰውም ነው። ፍጹም የሆነ አምላክ ፍጹም የሆነ ሰው። አምላክነቱን ብቻ እያየን ሰውነቱን መዘንጋት የለብንም፡ ሰውነቱንም ብቻ እያየን አምላክነቱን መዘንጋት የለብንም። ሁለቱንም አጣምረን በአንድነት /በተዋሕዶ/ ማመን መቀበል አለብን።