Friday, January 6, 2012

ምሥጢረ ሥላሴ (ክፍል ፪ )

Mistre Selasie Part-2, READ IN PDF here
ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ማወቅ ከሚገባን ጉዳዮች መካከል በእግዚአብሔርና በክርስቶስ ማመን (ምሥጢረ-ሥላሴና ምሥጢረ-ሥጋዌ) አንዱ መሆኑን በመጥቀስ ምሥጢረ ሥላሴን ባለፈው በመጀመር የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት ማየታችን ይታወሳል። እግዚአብሔር (ሥላሴ) በስም፡ በአካል፡ በግብር ሦስት መሆኑን በቀሩት ነገሮች በመፍጠር፡ በማዳን፡ በመለኮት፡ በሕልውና… አንድ መሆኑን ተመልክተናል።
የእግዚአብሔር ባሕርይ እጅግ ምጡቅና የማይመረመር ስለሆነ እኛም ካለብን የቋንቋና የአእምሮ ውስንነት የተነሳ ሙሉ በሙሉ መረዳት እንደማንችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በመጠኑ ስለርሱ ለማወቅ በምሳሌ አባቶች ያስተምራሉ። እግዚአብሔርን የሚመስለው ነገር ባይኖርም የእኛን የመረዳት ችግር ለማገዝ ለማስተማሪያ ይናገራሉ። በዚህ ክፍል ለምሥጢረ-ሥላሴ የሚቀርቡ ምሳሌዎችንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችን በመጠኑ እናያለን።
ለምሥጢረ-ሥላሴ የሚቀርቡ ምሳሌዎች፡
፩. ፀሐይ፡ ፀሐይ ሦስት ነገሮች አሉአት፡ ክበብ፡ ብርሃን፡ ሙቀት፡፡ ነገር ግን አንድ ፀሐይ ትባላለች። በክበቧ -አብ፡ በብርሃኗ-ወልድ፡ በሙቀቷ-መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ። (ሰው የሆነው ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ» ማለቱን ልብ ይሏል፡ ዮሐ ፰፡፲፪።)። አንድ ፀሐይ በመባሏ አንድ አምላክ ይባላል። ፀሐይ ሦስት ነገሮች ስለአሉአት ሦስት ፀሐይ ሳይሆን አንድ ፀሐይ እንደምትባል ሁሉ እግዚአብሔርም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የሚሉ ሦስት ስሞች፡ ፫ አካሎች፡ ፫ ግብሮች ቢኖሩትም አንድ አምላክ ይባላል እንጂ ሦስት አማልክት አይባልም።
የፀሐይ ክበብ በላይ በሰማይ ሆኖ ብርሃንና ሙቀት ወደ ምድር ይደርሳሉ። አብ በሰማይ ሆኖ ወልድ ና መንፈስ ቅዱስ ወደ ምድር መጥተዋል። ወልድ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆኖ በመወለድ፡ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በርግብ አምሳል በሐዋርያት በመውረድ። ስለዚህ ፀሐይ በመጠኑም ቢሆን የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት እንድንረዳ ትረዳናለች።


፪. የሰው ነፍስ፡- ነፍስ ሶስት ነገሮች አሉአት፡፡ ልብ፡ ቃል እስትንፋስ። እነዚህም የሦስቱ የነፍስ ባሕርያት ምንጭ የሆኑት ለባዊነት (ማሰብ)፡ ነባቢነት (መናገር)፡ ሕያውነት (ዘላለማዊነት) ናቸው።  እነዚህ ግን በአንድ ሰው ነፍስ ነው ያሉት። በልብ-አብ፡ በቃል-ወልድ፡በእስትንፋስ-መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ። ነገር ግን አንድ ነፍስ እንደመሆኗ አንድ አምላክ ይባላል።
በዚህ ምሳሌነት አንጻር እግዚአብሔር ሥላሴ ነው (ሦስትነት አለው) ስንል  አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ይባላል።
 ሥላሴ            - በአብ ልብነት ያስባሉ።
                   -በወልድ ቃልነት ይናገራሉ።
                   -በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት ሕያው ሆነው ይኖራሉ።
 እግዚአብሔር በሥላሴነቱ የሚያስበው በአብ ነው፡ የሚናገረው በወልድ ነው፡ ሕያው ሆኖ የሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ነው።
፫. በክፍል ውስጥ የበሩ ሦስት ሻማዎች፡- በአንድ ክፍል ውስጥ ሦስት ሻማዎችን ብናበራ ክፍሉ በብርሃን ይሞላል። በክፍሉ ውስጥ ያለው ብርሃን ከየትኛው ሻማ የመጣ ነው? ቢባል ከዚህኛው ለማለት አይቻልም። በዚሁ አንጻር እግዚአብሔርም ሦስት አካላት አሉት ብንልም በመለኮት፡ በሕልውና ግን አንድ ነው። ይህ መለኮትና ሕልውና የማንኛው ነው ማለት አንችልም፡፡ የሦስቱም በእኩልነት ነው። በመከፋፈል ሳይሆን በአንድነት ነው።
የምሥጢረ-ሥላሴ አመላካች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች፡
መጽሐፍ ቅዱሳችን ስናጠና እግዚአብሔር ራሱን በብዙ ቁጥር የጠራባቸውን ክፍሎች እናገኛለን። ለአብነት ያህልም፡-
እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፡ ዘፍ ፩፡፳፮።
እግዚአብሔር አምላክም አለ። እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፡ ዘፍ ፫፡፳፪
እግዚአብሔር ለምን ራሱን በብዙ ቁጥር ተናገረ? አንዳንድ ወገኖች እንደ ነገሥታት አነጋገር በክብር መናገሩ ነው ይላሉ። ነገሥታት «እንዲህ አደረግን….» እንደሚሉት። እንደዚያ ከሆነ ግን በሁሉም ቦታ ራሱን በብዙ ቁጥር መናገር ነበረበት። እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር ከአንድ በላይ ማንነት እንዳለው ያመለክታሉ። ሦስት መሆኑን አያሳዩም። ወደ ሐዲስ ኪዳን ስንመጣ ሦስትነቱ ግልጽ ይሆናል።
ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤  እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ። ማቴ ፫፡፲፮-፲፯።
እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ማቴ ፳፰፡፲፱።
እንግዲህ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነብ እነዚህን ጥቅሶች ለመረዳት የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት (ምሥጢረ-ሥላሴን) አስቀድሞ መማርና ማወቅ አለበት ማለት ነው። ካለበለዚያ እግዚአብሔር ለምን ራሱን አንድ ጊዜ ብዙ፡ አንድ ጊዜ ነጠላ እያደረገ እንደሚናገር ሊገባው አይችልም። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በአግባቡ አይረዳውም ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ አብን- እግዚአብሔር፡ ወልድን-የእግዚአብሔር ቃል (ልጅ)፡ መንፈስ ቅዱስን- የእግዚአብሔር መንፈስ ይለዋል። እግዚአብሔር የሚለው ቃል ራሱ የአንድነትም የሦስትነትም ስም ነው። በሰዋሰው እግዚአብሔር የሚለው ቃል በሁለት አቅጣጫ ይተረጎማል፡-
፩. እግዚአብሔር የሚለው ቃል እግዚእ-  አብ - ሔር ከሚሉ ሦስት ቃላት የተገኘ ነው። እግዚእ-ጌታ ማለት ነው፡ ወልድ ነው። አብ- አብ ነው። ሔር- ቸር ማለት ነው ፡መንፈስ ቅዱስ ነው። ይህ ሦስትነቱን ያሳያል፡፡
፪. እግዚአብሔር፡- እግዚአ እና ብሔር ከሚሉ ቃላት የተገኘ ነው። እግዚአ ማለት ገዥ/ጌታ፡ ብሔር-ሃገር/ዓለም ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ማለት የሃገር (የዓለም) ጌታ ማለት ነው። አንድ ጌታ ነው፡፡ ይህ አንድነቱን ያሳያል፡፡
እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለው ቃል የአንድነትም የሦስትነትም ስም ነው።
የምሥጢረ-ሥላሴ አመላካች የሆኑ ጥቅሶች ብዙ ናቸው። በየቦታቸው ስንደርስ እናብራራቸዋለን። ዋናው ነጥብ መጽሐፍ ቅዱስን በአግባቡ ለመረዳት ምሥጢረ-ሥላሴን ማወቅ አንድ ቅድመ-ሁኔታ መሆኑን ለማመልከት ያህል ብቻ እነዚህን ጥቅሶች አይተናል። በመቀጠል ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ማወቅ የሚገባን ስለ እግዚአብሔር ልጅ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ነው፡ይህም ምሥጢረ-ሥጋዌ ይባላል።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣይ ምሥጢረ-ሥጋዌን በአጭሩ እናያለን።
ይቆየን።
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን።
 አሜን። ፪ቆሮ ፲፫፡፲፬።


2 comments:

  1. ምስጢረ ሥላሴን ከልጅነታችን ጀምሮ ተነግሮን አድገናል። ያም ጠቅሞናል። ለዛሬው ማንነታችን መሠረት የተጣለው በዚያ ላይ ስለሆነ መልካምነቱን አሌ የሚል የለም። ነገር ግን የተማርነው ሁሉ ነገር ትክክል ይሁን አይሁን የምናውቀው ነገር አልነበረም። በባዶ ማንነታችን ላይ የሚቀመጥ እውቀት ስለነበረ እስካልሞላ ድረስ ወይም ሌላ እውቀት በተለየ ማመዛዘኛ እስካልቀረበ ያለውን መቀበል የግድ ምክንያታዊ የሚሆነው። ለዚህም ነው የየትኛውም ሃይማኖት አስተምህሮ ለራሱ ትክክል፣ የሌላው ግን ስህተትና ክህደት ሆኖ የሚታየው። የኔ በየትኛውም መመዘኛ ከሌላው ይበልጣል የማይል ሃይማኖት የለም። ለጊዜው ይህን ላቆይና ስለተማርነውና አንተ ስለዘገብከው ምስጢር ጥቂት አስተያየት ልስጥ።
    አብ ፀሐይ፣ ወልድ ፀሐይ፣ መንፈስ ቅዱስ ፀሐይ፣ አሀዱ ውእቱ ፀሐየ ጽድቅ ዘላእለ ኵሉ( ቅዳሴ ማርያም) የሚለውን ኃይለ ቃል በመተንተን ምስጢሩን የፈታህበት መንገድ እነዚህ ችግሮች ይታዩበታል።(ይህ የኔ ቃል የሚረጋገጥ እውነት እንጂ ምንፍቅና ወይም ተሀድሶነት አይደለም)
    ሦስቱን አካላት በፀሐይ ስንመስል ችግሮቹ፣
    1/ፀሐይ ውሱን አካል ናት። ዓለምን በምልዓት አትደርስም።
    2/ፀሐይን ሕልፈት ያገኛታል። የሰማይ አካላት እንደሚያልፉ የተነገረው እሷን ውጪ አያደርግም።
    3/በሙቀት የተመሰለው መንፈስ ቅዱስና በብርሃን የተመሰለው ወልድ ከዚያው ከአንዱ በአብ ከተመሰለው ክበብ ባንድ ጊዜ የሚገኙ በመሆናቸው ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ የሰረጹ አይደሉም ልትል አትችልም።
    ስለሆነም እግዚአብሔርን በፀሐይ መስሎ ማስተማር በፍጹም አሳማኝ አይደለም። ይልቁንም አመሰጠርን ብሎ ፈጣሬ ኵሉ ዓለማትን ከእጆቹ ፍጥረታት በአንዱ መስ'ሎ ለማስተማር መሞከር እጅግ አደገኛ ነገር ነው። ቃሉም እንደዚያ የሚያደርጉ ሁሉ እንዲጠነቀቁ፣
    ትንቢተ ኢሳይያስ 46፥5 በማን ትመስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ? ሲል ይጠይቃቸዋል።
    ከፍጥረትና ከምድራዊ ነገር ማመሳሰል አግባብ አይደለም። የምትነግረኝ ነገር ካለ በሦስቱ ነጥቦቼ ዙሪያ በጭብጥ እንድታስረዳኝ እጠብቃለሁ።
    በሻማ መብራት፣ በሰው፣ በሌላም በሌላም ምሳሌ ምስጢረ ሥላሴን ለመተንተን መሞከር ሦስትነቱን በምልዓት መግለጽ የማይችሉና የድኩም ሃሳብ መገለጫዎች ናቸው።
    ለመሆኑ ዋሕድ እግዚአብሔር በስም፣በአካልና በግብር የተገለጠበትን አምላካዊ ማንነት (ሰዎች ምስጢር የሚሉትን) በሰጠን ቃሉ ውስጥ ሰዎች የሚመስ-ሉትን ምሳሌ ለምን እኔ በዚህ፣ በዚህ እመሰላለሁ ብሎ ያላስቀመጠው ለምንድነው?
    እግዚአብሔር ስሙን ደብቆ የሰው ልጆች ፈልገው እንዲያገኙ፣ ድብብቆሽ ይጫወት ዘንድ ባህርይው አይደለም። አብ(አባት) መሆኑን «እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ፣ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ» ማቴ 3፣17 ሲል ሰምተነዋል። ኢየሱስ(ልጅ) መሆኑን «በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ» ማቴ 10፣33 ላይ አባቴ ሲል እንሰማዋለን። «ዮሐ 14፥26 አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል»ያለው
    መንፈስ ቅዱስ አጽናኝና ስለወልድ የሚያስተምር በተለየ አካሉ እንደሚመጣ የተነገረ መሆኑን ያስረዳናል። የሦስቱን የሥልጣን እሪና በማቴ 28፣19 ላይ እናገኛለን።
    እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለእኛ በሚበቃን መልኩ የተሰጠውን ትተን ከዚያ አልፈን ምስጢር አለ፣ እያልን የማይመስለውን በመመሰል የምስጢር ቁፋሮ ሥራ ማከናወን ተገቢ አይደለም።
    በዚህ አድራሻ ለማስተማር ብትጽፍልኝ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።
    lilay2009@aol.com

    ReplyDelete
    Replies
    1. በቅድሚያ ስለአስተያየቱ አመሰግናለሁ ወንድሜ/እህቴ፡ ይቅርታ ማንነትህን/ሽን ስላላወቅሁ ነው።
      በአስተያየትህ፡-
      - « …አብ ፀሐይ፣ ወልድ ፀሐይ፣ መንፈስ ቅዱስ ፀሐይ፣ አሀዱ ውእቱ ፀሐየ ጽድቅ ዘላእለ ኵሉ( ቅዳሴ ማርያም) የሚለውን ኃይለ ቃል በመተንተን ምስጢሩን የፈታህበት መንገድ እነዚህ ችግሮች ይታዩበታል።» ላልከው በመሠረቱ እኔ መነሻየ ቅዳሴ ማርያምን ለመተንተን እንዳልሆነ ግልጽ እንዲሆን እፈልጋለሁ።
      ስለእግዚአብሔር ማወቅ የሚገባን ና የሚጠቅመን ጉዳይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በበቂ ሁኔታ ተቀምጧል። አነሳሳችን የጎደለ ነገር ኖሮ ለመጨመር ሳይሆን የተቀመጠውን እውነት በሚገባን መልኩ ለመማማር ነው።
      በመሠረቱ እኔ የእገሌ ሃይማኖት ከእገሌ ይበልጣል/ያንሳል የሚል አመለካከት የለኝም። ወደዚያ ክርክር ውስጥ መግባት አለፈልግም። በማንም ላይ ምንፍቅና ወይም ተሃድሶነት የሚል ነገርም የለብኝም፡፡ በንጹሕ ሕሊና ለመማማር ለሚመጣ ሁሉ ለመወያየት ዝግጁ ነኝ፡፡ ዋናው ጉዳይ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ማድረስ ነው።
      ስለእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት (ምሥጢረ-ሥላሴ) ምሳሌ ማቅረብ አይገባም የሚሉ ብዙ ወገኖችና፡ አባቶች እንዳሉ የታወቀ ነው። ለእግዚአብሔር ክብር ካላቸው ቅንዓት ነውና መልካም ነው። እንደእኔ አስተያየት የእግዚአብሔርን ነገር (አንድነት ሦስትነቱን) በቅጡ ያላወቁ ና ያልተረዱ ብዙ ደግሞ ወገኖች ስላሉ ቀለል ባለ አቀራረብ በምሳሌ ስለእግዚአብሔር ማስተማሩ የእኛን አላዋቂነት ለማገዝ ይረዳል እንጂ የርሱን ክብር ዝቅ የሚያደርግበት አንዳች ምክንያት የለም።
      - ኢሳ ፵፮፡፭ ላይ በማን ትመስሉኛላችሁ? ብሎ የተናገረው ስለምን እንደሆነ ክፍሉን ማጤን አለብን። ይህ የተነገረው እግዚአብሔርን በአምልኮ ጣኦት ስለለወጡት እስራኤላውያንን ለመውቀስ ነው። ጣኦታት የሚመለኩት በምሳሌ ነው። በተቀረጸ ምስል። እግዚአብሔር ግን የሚመለከው በመንፈስና በእውነት ነው እንጂ በምሳሌ አይደለም።
      «ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል ዮሐ ፬፡፳፫።
      ልክ ነው በአምልኮት ከሄድን መመለክ የሚገባው አንድና ብቸኛ አምላክ እርሱ ብቻ ነው። የሚመለከውም በመንፈስና በእውነት ነው። በአምልኮ የሚመሳሰለው የሚተካከለውም የለም።
      እኛ እዚህ ጋ እያወራን ያለው ስለትምህርት ነው። እግዚአብሔርን ስለማወቅ ምሳሌን ተጠቅመን እንማማር አልን እንጂ እግዚአብሔርን ለማምለክ ፀሐይን አምሳያው (ምሳሌው) እናድርግ አላልንም። እርሱን ማንም የሚመስለው የለም። ይሄ ግልጽ ነው።
      - ሦስትነቱን በምልዓት መግለጽ የማይችሉና የድኩም ሃሳብ መገለጫዎች ናቸው።» ላልከው የእግዚአብሔርን ሦስትነት ብቻ አይደለም ማንኛውም ማንነቱን ለመግለጽ የሚቸል አንዳች ነገር የለም፡ ሊኖርም አይችልም። እንኳን ፈጣሪን ፍጥረቱን መች ገልጸን መርምረን ጨረስን?... የድኩም ሃሳብ የሚለው ግን ተገቢ ንግግር አይደለም። ከፋም ለማም የማንም ሃሳብ ሊነቀፍ አይገባም። አሳማኝ ነጥቦችን በማምጣት በፍቅር መወያየት ይሻላል።

      እስኪ የሚከተሉትን አራት ነጥቦች እንይ።
      ፩. በመጀመሪያ እግዚአብሔርን የሚመስለው እንደሌለ አስቀድሜ የጠቀስኩ መሆኔንና ይህም የማይካድ ሃቅ መሆኑን እንድታውቅልኝ እፈልጋለሁ።
      ፪. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተቀመጡት ትምህርቶች ከወተት - አጥንት በተለያየ ደረጃ ያሉ መሆኑን እና በአጥንት ደረጃ ያሉትን ለመረዳት በመምህራን እየታገዝን እና ቀለል ባለ አቀራረብ እየተማርን ማደግ እንደሚገባን ለዚህም ምሳሌ አንዱ የማስተማሪያ መንገድ መሆኑን ማወቅ አለብን።
      ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ ፩ቆሮ ፫፡፪። እንዳለ ሐዋርያው።
      ፫. ነገሮችን በምሳሌ ማስተማር መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን ጌታም በወንጌል እንደተጠቀመበት በብዙ ቦታ እናገኛለን።
      ፬. ምሳሌ ከሚመሰልለት ነገር በጣም እንደሚያንስ፡- ምሳሌ ዘየሐጽጽ እንደሚሉት። ይመሳሰላል ማለት ይተካከላል ማለት አይደለም። ምሳሌ ያሰኘውም በማነሱ ነው። ለአብነት ያህል ጌት መንግሥተ-ሰማያትን ያህል ታላቅ ነገር እጅግ በጣም ታናሽ በሆነችው በሰናፍጭ ቅንጣት መመሰሉን እናያለን። ማቴ ፲፫፡ ፴፩። ጌታም ይህን በማድረጉ የመንግሥተ-ሰማያት ክብር አሳነሰ እንደማያሰኘው ግልጽ ነው።
      ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ? አሉት።
      እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፥ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ማቴ ፲፫፡ ፲-፲፩።
      ምሳሌ ያስፈለገው የኛን አላዋቂነት እና የመረዳት ውስንነት ለማገዝ ብቻ ነው።
      ወንድሜ ነገሩን እስኪ ከበጎ እንመልከተው። አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እያነበበ ዘፍ፩፡ ፳፮ … ላይ ሲደርስ ለምን እግዚአብሔር ራሱን በብዙ ቁጥር ተናገረ? ቢለን። እግዚአብሔር አንድነቱን ብቻ በሚገልጽ ሁኔታ በነጠላ ንግግር ብዙ ቦታ ተናግሮ ማቴ ፳፰፡፲፱ ላይ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሲል ለምን ሦስትነት መጣ? ቢል - እኛም {ያለምሳሌ ሳናስረዳ} በደፈናው እግዚአብሔር አንድ እና ሦስት ነው ብንለው በደምብ ሊገባው ይችላል? አንድ ነገር እንዴት በአንድ ጊዜ አንድም ሦስትም ሊሆን ይችላል ቢለን ተመሳሳይ ነገሮችን በማቅረብ ብናስረዳ ክፋቱ ምንድን ነው? ወይስ ይህን በማለታችን እንዴት የእግዚአብሔር ክብር ዝቅ ይላል? እግዚአብሔር ልዑልና ታላቅ አምላክ ነው። ክብሩም ፍጽም ስለሆነ ማንም የፈለገውን ቢል ሊጨምርለት፡ ሊቀንስበትም አይችልም።
      እንደኔ በምሳሌ ማስተማሩ ለተማሪው እርዳታ በሚሆን አቅጣጫ መልካም ጎኑ ይታየኛል እንጂ ከእግዚአብሔር ክብር ጋር የሚጋጭ ነገር እንደሚሆን አላስብም።
      የሚነሳ ነጥብ ካለ እንቀጥል።አመሰግናለሁ።

      Delete

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment