Wednesday, January 18, 2012

የብሉይ ኪዳኑ- ዓለም ካርታ ፩


በዚህ ክፍል ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የሚረዱንን የተለያዩ ካርታዎች ከመግለጫ ጋር እንመለከታለን።
ካርታዎቹ የተወሰዱት ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መማሪያ ከተዘጋጁ ልዩ ልዩ መጻሕፍት ነው።
ለዛሬ ለመጀመሪያ በብሉይ ኪዳን የቀደመውን ታሪክ ይበልጥ እንድንረዳ የሚያግዝ ካርታ እንደ መግቢያ እናያለን።
ይህንን ካርታ ወደፊት ለተለያዩ ታሪኮች መግለጫ በተደጋጋሚ እንጠቀምበታለን።


ይህ ካርታ በአሁኑ ሰዓት መካከለኛው ምሥራቅ የሚባለው አካባቢ ነው።
በመጽሐፍ ቅዱሳችን በኦሪት ዘፍጥረት የምናነበው ታሪክ የተፈጸመው በዚህ አካባቢ ነው። አብዛኛው የመጸሐፍ ቅዱስ ታሪክ የተከናወነው በመካከለኛው ምሥራቅ  ነው።

አገሮች፡ መልክአምድሮች፡ ተራሮች፡ ወንዞች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክና ትምህርት አካሎች ናቸው። እነዚህን በካርታ መመልከቱ ታሪኩን / ትምህርቱን ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል።
በዚህ ካርታ ላይ የኖኅን፡ የአብርሃምን፡… ታሪኮች የሚያሳዩ መልክአ-ምድሮችን (ወንዞችን፡ ተራሮችን፡ አገሮችን…) በቀላሉ ማየት ይቻላል።
ለአብነት ያህል በኖኅ ዘመን በተፈጸመው የጥፋት ውኃ የዳኑባት መርከብ ያረፈችው በአራራት ተራራ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።
«መርከቢቱም በሰባተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ቀን በአራራት ተራሮች ላይ ተቀመጠች።» ዘፍ ፰፡፬
በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ-ቃላት እንደተገለጸው፡
« አራራት፡- ከእስራኤልና ከሶርያ በስተሰሜን ያለ ተራራማ አገር ነው። የኖኅ መርከብ በአራራት ተራራዎች ዐረፈች፡ ዛሬ አገሩ አርመን የሚባለው ሲሆን የሚገኘውም በቱርክ አገር ነው።»  ይላል።
ጥቅሱንና መግለጫውን በካርታ ላይ ስናየው ይበልጥ እንረዳዋለን።
ከጥፋት ውኃ በኋላ የኖኅ ሦስቱ ልጆች የሰውን ዘር ታሪክ ለመቀጠል የተነሱት እንግዲህ ከዚህ ቦታ ነው። ሦስቱ ልጆቹ ወደ ሦስት አቅጣጫዎች በመጓዝ የተከፋፈሉአቸውን ሃገራት (አህጉር) በቀጣይ በሌላ ካርታ እንመለከታለን።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ወደፊት በሚኖሩን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ታሪኮችና ትምህርቶች የተለያዩ ካርታዎችን እያየን እንማማራለን።
ይቆየን።

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment