Friday, January 20, 2012

የጥያቄ ፫ መልስ (ቀጣይ)

ባለፈው መመለስ የጀመርነው ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ፍጥረታትን በ፮ ቀን እንደጨረሰ በዘፍጥረት ፩ ተጠቅሶአል። አንድ ቀን የምንለው ፀሐይ ፡ወጥታ፡ ገብታ መልሳ እስክትወጣ ያለውን ፳፬ ሰዓት ነው። ፀሐይ ግን የተፈጠረች በአራተኛው ቀን ረቡዕ ነው። ቁ ፲፬። ታዲያ ከዚያ በፊት የነበሩት ፫ ቀናት (ከእሑድ- ማክሰኞ) በምን ተቆጠሩ?

መጽሐፍቅዱስ ከሰዎች የኑሮ ልማድ ጋር በየጊዜው መሻሻል የማያስፈልገው አንድ ጊዜ የተጻፈና ሁልጊዜ እየተነበበ ሕይወትን የሚመራ ልዩ መጽሐፍ መሆኑን፡፡ ባለፈው በጥያቄ ያነሳነው የመጀመርያው ክፍለ-ንባብ እንደየአካባቢዎቹ የዕውቀትና የመረዳት ደረጃ ሊስማማ ይችላል ብለን ብዙም ላልተማረ የኔብጤ መሃይም ሆነ በጥልቀት ለሚመራመር ሳይንቲስት ለሁለቱም በየራሳቸው በሚረዳ መልኩ መጻፉን አይተናል፡፡ ሁለቱም ሰዎች ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ለሰዎች ነው፡፡


ከፍጥረታት የመጀመርያ ጊዜ ሳንወጣ ስለሰባተኛው ቀን የተጻፈውን በመመርመር ሌላ ነጥብ ማየት ይቻላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ፍጥረታት በተፈጠሩበት ክፍል በምዕራፍ አንድ ውስጥ «ማታም ሆነ፤ጧትም ሆነ፤ አንድ ቀን፡፡» እያለ እስከ ስድስተኛው ቀን ይሄዳል፡፡ ዘፍ ፩፡፴፩፡፡ በሰባተኛው ቀን ግን እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ ይናገራል እንጂ እንደሌሎቹ ቀናት «ማታም ሆነ፤ ጧትም ሆነ፤ ሰባተኛ ቀን፡፡» የሚል ቃል አናገኝም፡፡ ዘፍ፪፤፪፡፡
 ከዚህ ምን እንረዳለን? ሰባተኛው ቀን አላለቀም ወይም አልተዘጋም፡፡ ስለዚህ ሁላችን እየኖርነ ያለነው በሰባተኛው ቀን ነው ማለት ነው፡፡

እስከ ስንት ዘመን እንደምንኖር ደግሞ አናውቀውም፡፡ ማለትም የዓለም ፍጻሜ ከባለቤቱ ከእግዚአብሔር በቀር የሚያውቅ የለም፡፡ ይህም ማለት እንግዲህ የተጀመረው ሰባተኛ «ቀን» መቼ እንደሚያልቅ ወይም በውስጡ ስንት ጊዜ እንደሚያካትት አይታወቅም፡፡ ከዚህ ሃሳብ ተነስተን አስከትለን ስንመረምር ምናልባት «ቀን» እየተባለ የተነገረላቸው ስድስቱም የፍጥረት ቀናት ርዝመት ምን ያህል እንደሆነ አይታወቅም ወደሚል መደምደሚያ ያመራናል፡፡
     አሁንም «ቀን» የተባለው ከተለመዱት 24 ሰዓት በላይ ሊሆን እንደሚችል ሌላ ጠቋሚ ማስረጃ ከዚያው ከሥነ-ፍጥረት ማየት ይቻላል፡፡በሦስተኛው ቀን በዕለተ-ማክሰኞ እግዚአብሔር አዝርዕትን፤ አትክልትን፤ ዕፅዋትን እንደፈጠረ ይናገራል፡፡ዘፍ፩፤፲፩-፲፪፡፡ «ምድር ...  ብቅል»  ባለው አባባል በተለየ ተአምራት ካልሆነ በስተቀር ምድር አሁን በምናውቀው የማብቀል ሥርዓቷ መሠረት በ24 ሰዓት ውስጥ በቅሎ አድጎ እስከፍሬ የሚደርስ ምንም ዓይነት አረንጓዴ ተክል የለም፡፡ ትላልቅ ዛፎች አድገው ለመድረስ የዓመታት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ የዚህ የሦስተኛው ቀን ርዝማኔ ምናልባት በዓመታት የሚቆጠር ዘመን ይሆን ይሆናል፡፡..... ሌላም ሌላም ማለት ይቻላል፡፡       
በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሰውን የጊዜ ልኬታ በግሌ የተገነዘብኩትን እንደመቋጫ  ላስቀምጥ፡፡የጊዜ አለካክን በተመለከተ 3 ሁኔ ዎች እንዳሉ መረዳት ይቻላል፡፡
፩. በመጀመርያ («መጀመርያ» ስንል አሁንም በጊዜ እይታ ሳይሆን ከጊዜ አስቀድሞ በነበረው ሁኔታ ማለታችን ነው፡፡) ጊዜ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ በዚህም ጊዜ ባልነበረበት ሁኔታ እግዚአብሔር አምላክ «አብ» አንድያ ልጁን «ወልድን» አስገኘ፡፡ መንፈስ ቅዱስም ተገኘ፡፡ በምሥጢረ-ሥላሴ ትምህርት እንደሚታወቀው በአብና በወልድ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ መካከል መቀዳደም የለም፡፡ ምክንያቱም እነደአሁን አባትና ልጅ እንዲቀዳደሙ የሚያደርግ ማነጻጸርያና ዕድሜ መቁጠርያ የሆነው ጊዜ አልነበረምና፡፡ ሦስቱም ዕሩያን (እኩል) ናቸው የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ ጊዜ መጀመርያ እንዳለውና ከጊዜና ከዘመን በፊት የእግዚአብሔር ሕልውና እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡፡ «... ስለዚህም ሕይወት የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት » (ዘመን ባልተጀመረበት ሁኔታ  ተስፋ ሰጠ፡፡) ቲቶ ፩፤፪፡፡ በመጽሐፈ ቅዳሴም እንዲህ ይላል፡፡ «ወለዶ አብ ለወልዱ ኢይትበሀል ዘ ጊዜ ወበከመዝ መዋዕል ወለዶ፡፡ አብ ልጁን ወለደው፤ በዚህ ጊዜ እንዲህ ባለ ዘመንም ወለደው አይባልም፡፡» /የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ቁ. 24፤ገጽ 194/ ይህ እንግዲህ ጊዜ ከመጀመሩ አስቀድሞ ጊዜ ያልነበረበት ሁኔታ  ነው፡፡
፪. ከዚያም እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር የነበረው የመጀመርያው ሁኔታ /ከመጀመርያው ቀን «እሑድ» ፀሐይ እስከተፈጠረችበት እስከ አራተኛው ቀን «ረቡዕ»  መጨረሻ ጊዜ በጽንሰ-ሃሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባር እየተነገረ «ቀን» እየተባለ የተሠራበት ነገር ግን መጠኑ ያልታወቀ ያልተገለጸ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ ቀን እየተባለ የተነገረው መለኪያ የተወሰኑ የምናውቃቸው መደበኛ ቀናት ይሁን ወይም ብዙ ሚሊዮን ዓመ ት በግልጽ የተቀመጠ ነገር የሌለበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
፫. በኋላ ግን ጊዜ ከአራተኛው ቀን «ረቡዕ» አንስቶ መለኪያዎቹ ፀሐይ ጨረቃና ከዋክብት ከተፈጠሩ በኋላ  ልኩና መጠኑ ታውቆ እየተቆጠረ፤እየተሰፈረ እስከ አሁን ድረስ ይገኛል፡፡ ወደፊትም ፍጻሜው እስከማይ ወቅበት ጊዜ ይቀጥላል፡፡
አሁንም ፀሐይ ከተፈጠረች በኋላ የተቆጠሩት ቀናት ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ አራተኛ ቀን፡(ረቡዕ) አምስተኛ ቀን፡ (ሐሙስ)፡ ስድስተኛ ቀን (ዓርብ) እየተባሉ ተደምድመዋል። ስለሰባተኛው ቀን ግን ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ ሰባተኛ ቀን የሚል መደምደሚያ አናገኝም። የሰባተኛውን ቀን መጀመር እንጂ መጠናቀቅ አናገኝም። ታዲያ ይህ ማለት ምን ማለት ነው? አስቀድመን እንዳልነው ሁላችንም አሁን እየኖርነ ያለነው በሰባተኛው ቀን ነው።/?/
ስለቀናት አለካክ ካነሳን ዘንድ በመጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሁለት ጥቅሶች እናገኛለን።
«ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን፥ እንደ ሌሊትም ትጋት ነውና።» መዝ ፹፱/፱፡፬።
«እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ።» ፪ጴጥ ፫፡፰።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ስለእነዚህ ጥቅሶች ማብራሪያ ወደፊት የምናይ ይሆናል።
ከላይ ስላነሳነው ሃሳብ ግን ተጨማሪ አስተያየት፡ ጥያቄ ካለ ከዚህ ጽሑፍ ሥር comments በሚለው ሥር ሃሳብ መስጠት ይቻላል። ከሌለ ወደ ሌላ ጥያቄ እናልፋለን።
ይቆየን።

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment