Sunday, May 5, 2013

አዲስ ኪዳን - የወንጌል ክፍል



ከአሁን ቀደም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የብሉይ ኪዳንን ዳሰሳ በየክፍሎቹ ማለትም በኦሪት፣በታሪክ፣ በቅኔና መዝሙራት እንዲሁም በትንቢት ክፍል ይዘታቸውን በአጭር በአጭሩ ማየታችን ይታወሳል። አሁን ደግሞ በአዲስ ኪዳን ያሉትን ክፍሎች ማለትም የወንጌል፣ የታሪክ፣ የመልእክትና የትንቢት ክፍሎችን እንዲሁ በየተራ እንዳስሳለን። ለዛሬ የወንጌል ክፍልን እናያለን።
የወንጌል ክፍል የሚባሉት አራቱ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ እንደሆኑ ይታወቃል። ወንጌል ማለት ምን ማለት ነው? ስንል ወንጌል ማለት የምሥራች ማለት ነው። በኃጢአት ለተያዘው የሰው ዘር መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱን…መሞቱን እና መነሳቱን የሚገልጽ የደስታ ቃል ማለት ነው። ከአንድ ወንድሜ እንደተማርኩት ወንጌል ማለት የምስራች መሆኑን ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚተረጉምልን እነዚህን ሁለት ጥቅሶች ማየት እንችላለን።
አስቀድሞ በነቢዩ በኢሳይያስ ስለ ክርስቶስ የተነገረው እንዲህ ይላል።
የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል። የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ፥ የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ» ኢሳ ፷፩፣፩-፪
ይህንኑ ክፍል ሉቃስ በወንጌል ሲጠቅሰው እንዲህ ይላል።
« የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ። የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ።»  ሉቃ ፬፣ ፲፯-፲፱።
ነቢዩ ኢሳይያስ የምስራች ያለውን ወንጌላዊው ሉቃስ ወንጌል ብሎ ይተረጉመዋል። ስለዚህ ወንጌል ማለት የምሥራች ማለት ነው። ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ያለው የምሥራች ወንጌል ነው። እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ወንጌል ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ያብራራል።

« ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ጳውሎስ በነቢያቱ አፍ በቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ለሰጠው ለእግዚአብሔር ወንጌል ተለየ።  ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።» ሮሜ ፩፣፩-፬
ወንጌል ማለት ስለኢየሱስ ክርስቶስ ከልደቱ እስከ ትንሣኤው ያለው የምሥራች ቃል ነው። በጥቅሱ እንደምናየው… ከዳዊት ዘር ስለተወለደ…. ከሙታን መነሣት የተነሣ…. ይላል። ከማቴዎስ እስከ ዮሐንስ ያሉት አራቱም ጸሐፍያን የክርስቶስን ነገር ከልደቱ እስከ ሞቱና ትንሣኤው ያለውን ነገር በሙሉ እንደዘገቡ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ወንጌላውያን ወይም የወንጌል ጸሐፊዎች ተብለዋል። ወንጌሉ ስለክርስቶስ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ራሱ ወንጌሉ ክርስቶስ ነው። በአራቱም ወንጌላውያን መጽሐፍ ርእሱን ብንመለከተው…. «የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ቅዱስ ማቴዎስ /ማርቆስ… እንደጻፈው»  ይላል። የአንድምታው መጽሐፍ ርእስም እንዲህ ይላል። «ወንጌል ቅዱስ ዘእግዚእነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ - የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል » በማለት ጌታ መድኃኒት መሆኑንም ይጠቅሳል።  ስለዚህ ወንጌል ማለት ስለ ልጁ ስለኢየሱስ ክርስቶስ መናገር ማለት ነው። ወንጌልም ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። መፍትሄ አልባ ሆኖ ለቆየው ለዓለሙ ሁሉ የኃጢአት በሽታ ብቸኛ መድኃኒት ሆኖ የመጣው የምሥራች እርሱ ነውና።
ስለወንጌል ትርጉም በአጭሩ ይህን ያህል ካልን  ቀጥለን የአራቱን ወንጌላውያን ዳሰሳ በአጭሩ እንቃኛለን።
ወንጌላውያኑ አራት መሆናቸው በአራቱ የኪሩቤል እንስሳ አምሳል / አርባእቱ እንስሳ/፣ በአራቱ ማዕዘናተ-ዓለም ወዘተ… ምሳሌነት እንደሚገለጹ በአንድምታው ተቀምጧል። ከአራቱ ወንጌላውያን ሁለቱ ማቴዎስና ዮሐንስ ከ፲፪ቱ ሐዋርያት፣ ሁለቱ ማርቆስና ሉቃስ ከ፸፪ቱ አርድእት ናቸው።
፩. ማቴዎስ፡-   ሥራው ቀራጭ ነበረ። ምልክቱ /ምሳሌነቱ በገጸ-ሰብእ (በሰው አምሳል) ነበረ። ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ ከዳዊትና ከአብርሃም ዘር የተወለደ ፍጹም ሰው መሆኑን ለማመልከት በሰዎች የዘር ሃረግ ቆጠራ ወንጌሉን ስለሚጀምር እንዲሁም በወንጌሉ ውስጥ ክርስቶስ የሰው ልጅ በመባል ብዙ ጊዜ ስለተጠራ ነው።
የማቴዎስ ወንጌል የተጻፈው ለአይሁድ ነው። ስለዚህ አይሁድ በሚመኩባቸው በዳዊትና በአብርሃም የክርስቶስን ዘር ቆጠራ ጀመረ። የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ… ይላል። ዳዊት ንጉሣችን፣ አብርሃም አባታችን እያሉ አይሁድ ስለሚመኩ ክርስቶስ የመጣው ከእነዚህ አበው አንደሆነ ለማጠየቅ ሌሎችን ለይቶ በእነርሱ ጀመረ። ከዚህም ሌላ አይሁድ በሚቀበሏቸው በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ያሉ ትንቢቶች በሙሉ በክርስቶስ መፈጸማቸውን ለማመልከት ስለፈለገ በእያንዳንዱ የክርስቶስ የሕይወት ምእራፍ-  በጽንሰቱ፣ በልደቱ፣ በስደቱ፣ በጥምቀቱ፣ ወዘተ ….እስከ ሞቱና ትንሣኤው ድረስ ትንቢቶችን እየጠቀሰ መፈጸሙን ይናገራል። .. በነቢዩ… እንዲህ እንዲህ የተባለው ይፈጸም ዘንድ.. እንዲህ ሆነ እያለ ይጠቅሳል። ዓላማው የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ የመጣው መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአይሁድ ዘር የሆነ የሰው ልጅ እና የብሉይ ኪዳን ትንቢት ፍጻሜ መሆኑን ለማሳየት ነው። የማቴዎስ ወንጌል በአዲስ ኪዳን መጀመሪያ በመደረጉ እና በብዛት ከብሉይ ኪዳን በመጥቀሱ ብሉይ ኪዳንን ከአዲስ ኪዳን ጋር እንዴት እንደሚያያይዝ ልብ ይሏል።
በአዳም በደልና በኃጢአታችን ከእግዚአብሔር እንደተለየን በብሉይ ኪዳን ይታወቃል። ስለዚህ በአዲስ ኪዳን መጀመሪያ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ (አማኑኤል) ከሰዎች ጋር መሆኑን /ለመሆን መፈለጉን/ ማቴዎስ በወንጌሉ መጀመሪያና መጨረሻ ሃሳቡን ይገልጻል።
በጌታ ልደት ሲጀምር ---«… ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤ የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፣ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።» ማቴ ፩፣፳፫
በጌታ ትንሣኤ ሲጨርስ.---«… እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።» ማቴ ፳፰፣ ፳።
እኛ በራሳችን ከእግዚአብሔር ተለየን። እግዚአብሔር ግን በክርስቶስ ከእኛ ጋር ሆነ /ይሆናል። አማኑኤል የሚለው ስም ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ኅብረት ያሳያል።
 ፪. ማርቆስ፡- ከአራቱም ወንጌላት አጭሩ ሲሆን ሥራ ለሚበዛባቸው ለሮማውያን /ለአሕዛብ/ የተጻፈ ነው። በመንገድ ጠራጊው በመጥምቁ ዮሐንስ ወንጌሉን ይጀምራል።

አራቱ ወንጌላውያን በወቅቱ ለተለያዩ ወገኖች ቢጽፉም አሁን ለእኛ ግን የክርስቶስን ሕይወት ከተለያየ አቅጣጫ እንድናየው ጽፈዋል። በሥነ-ሕንጻ ትምህርት የአንድ ምስል ሙሉ ገጽታ ለመረዳት አራት እይታዎች አሉ። የፊት ለፊት (front view)፣ የጎን (side view)፣ የላይ (top view) እና የውስጥ (section view). ስለዚህ አራቱም ወንጌላውያን የክርስቶስን ማንነት እንድናውቅ ከተለያየ እይታ ጽፈውልናል። ይሁንና አንዳቸውም የክርስቶስን እያንዳንዱን ተግባር በዝርዝር አልጻፉም። ሁሉ ይጻፍ ቢባል ዓለም እንደማይበቃ አራተኛው ወንጌላዊ ዮሐንስ  ምስክርነቱን በመስጠት ወንጌላቱን ደምድሟል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እስከመጨረሻው ያልተለየው ዮሐንስ መሆኑን ልብ ይሏል።
«ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል።» ዮሐ ፳፩፣፳፭ ።
የአራቱን ወንጌላውያን ምሳሌና ይዘት በሚከተለው ሰንጠረዥ ጠቅለል አድርገን ማየት እንችላለን።
ተ.ቁ.
ወንጌላዊ
ከ፬ቱ እንስሳ የተመሰለበት
የጻፈላቸው ወገኖች
ክርስቶስን የገለጸበት ዐቢይ ሃሳብ
ማቴዎስ
በሰው
ለአይሁድ
የአይሁድ ንጉሥ
ማርቆስ
በአንበሳ
ለሮማውያን
የእግዚአብሔር አገልጋይ
ሉቃስ
በላም
ለቴዎፍሎስ * ና ለግሪኮች
የሰው ልጅ
ዮሐንስ
በንስር
ለመላው ዓለም
የእግዚአብሔር ልጅ
* ሉቃስ የጻፋቸው ወንጌሉና የሐዋርያት ሥራ ሲጀምሩ ቴዎፍሎስ ሆይ በማለት እነደሆነ ከመግቢያቸው እናስተውላለን።
ስለአራቱ ወንጌላውያን ዝምድና በንጽጽር በተደረገ አንድ ጥናት እንዲህ ተገልጾአል፤
-      ከ90% በላይ የሚሆነው የማርቆስ ወንጌል በማቴዎስና በሉቃስ ውስጥ ይገኛል።
-      ወደ 60% የሚሆነው የማቴዎስ ወንጌል በማርቆስና በሉቃስ ውስጥ ተጽፎአል።
-      ወደ 40% የሚሆነው የሉቃስ ወንጌል በማቴዎስና በማርቆስ ውስጥ አለ።
-      በሌሎቹ ሦስት ወንጌላት የሚገኘው የዮሐንስ ወንጌል ይዘት ግን 8% ብቻ ነው። ዮሐንስ ከሌሎቹ ሦስት ወንጌሎች የተለየ አጻጸፍና አቀራረብን ይከተላል።
በአጠቃላይ ወንጌል ማለት የመጽሐፍ ቅዱስ አንኳር መልዕክት የሆነው የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ ሕይወትና ነገረ-ድኅነት የተፈጸመበት፣ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ቀድመው በትንቢትና በምሳሌ የተናገሩለት በኋላም እስከ ዓለም ዳርቻ የመሰከሩለት፡ ዛሬም ወደፊትም እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚነገር ታላቅ የምሥራች የሆነው የእግዚአብሔር የድኅነት መንገድ ነው።
ወንጌሉ በራሱ በባለቤቱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከተመሠረተ በኋላ በደቀ መዛሙርቱ በሐዋርያት በኩል ወደ ቀረው ዓለም መሰራጨቱን ቀጣዩ የአዲስ ኪዳን ክፍል ይነግረናል። በዚህም መሠረት ከጌታችን ዕርገት በኋላ በሐዋርያት በኩል ይህ የዓለም የምሥራች ቃል እንዴት መስፋፋት እንደጀመረ ቀጣዩ የአዲስ ኪዳን የታሪክ ክፍል የሐዋርያት ሥራ ያሳየናል።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በሚቀጥለው ክፍል የሐዋርያት ሥራን ዳሰሳ እናያለን።
ይቆየን።

1 comment:

  1. እግዚዓብሔር ይስጥልኝ!!!!

    ReplyDelete

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment