Tuesday, March 5, 2013

ብሉይ ኪዳን - የትንቢት ክፍል



ባለፈው ጥናታችን በብሉይ ኪዳን የሚገኙት መጻሕፍት በሥነጽሑፋዊ ይዘታቸው ከአራት እንደሚከፈሉ በመግለጽ ሦስቱን የኦሪት፣ የታሪክ እና የመዝሙርና የቅኔ ክፍሎችን አይተናል። ለዛሬ የብሉይ ኪዳን የመጨረሻ ና ፬ኛ ክፍል የሆነውን የትንቢት ክፍል ዳሰሳ እናያለን።
ትንቢት ማለት በአጭሩ ስለመጪው ሁኔታና ዘመን አስቀድሞ መናገር ነው።  ነቢያት የእግዚአብሔርን ቃል በቀጥታ ድምጽ፣ በራእይ፣ በሕልም ወዘተ… በተለያየ መንገድ በመቀበል ለሕዝቡ ያስተላልፉ ነበር። የእግዚአብሔር ሃሳብ ቃል አቀባይ ስለሆኑም ሲናገሩ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡-.. » እያሉ በማስረገጥ ነበረ። በአዲስ ኪዳን ግን ባለቤቱ ራሱ ሰው ሆኖ በመምጣት ፊት ለፊት « እኔ እላችኋለሁ..» እያለ መናገሩን እናስታውሳለን።
በትንቢት ክፍል ውስጥ በስማቸው ራሱን የቻለ መጽሐፍ ካላቸው ነቢያት ውጭ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ሌሎች ብዙ ነቢያት የተነሱ መሆኑ ይታወቃል፤ ለምሳሌ ከብሉይ ኪዳን እንደ ሙሴ፣ ሰሙኤል፣ ዳዊት፣ ኤልያስ፣… ከአዲስ ኪዳን እንደ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ወንጌላዊው ዮሐንስ (በዮሐንስ ራእይ) እነዚህ ሁሉ ትንቢቶችን ተናግረዋል።
የትንቢት መጻሕፍቱ በብሉይ ኪዳን መጨረሻ በአንድ ላይ ቢቀመጡም ነቢያቱ ትንቢቶችን የተናገሩት ግን በአብዛኛው በመጽሐፈ ነገሥት ታሪክ ውስጥ ነበር። የትንቢት መጻሕፍት ይዘት በወቅቱ እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ከእስራኤላውያን ጋር ባደረገው ቃል ኪዳን (ብሉይ ኪዳን) ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነበር። የተሰጣቸውን የቃል ኪዳን ትእዛዝ ከጠበቁ ስለሚያገኟቸው በረከቶች፣ ትእዛዛቱን እንዳይጥሱ የተለያዩ  ማስጠንቀቂያዎችና ትእዛዛቱን ከጣሱ ስለሚያገኛቸው ቅጣቶች ይናገራሉ። ከዚህ ሌላ ስላለፈው ዘመን፣ ስለመጪው ዘመን፣ ስለአዲስ ኪዳን፣ ስለ ክርስቶስ የሚናገሩት የትንቢት ክፍሎች አሉ። አብዛኛው የትንቢት ክፍል ይዘት ግን ከወቅቱ የእስራኤላውያን ሁኔታ ጋር የተያያዘ እና በአሁኑ ሰዓትም ፍጻሜን  ያገኘ ነው። የትንቢቶችን ይዘት በተናገሩባቸው ዘመናት ብንከፍላቸው እንደሚከተለው በሦስት ዘመናት ማየት ይቻላል።


፩. ከእነርሱ ዘመን በፊት ስለነበረው ሁኔታ የተናገሩ፡-
ለምሳሌ ሰው ከመፈጠሩ አስቀድሞ በነበረው የመላእክት ዓለም የነበረውን የሣጥናኤልን (የዲያብሎስን) አመጽ እና  ውድቀት የሚናገር ክፍል አለ።
« አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህ! አንተም በልብህ። ወደ ሰምይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ። ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጕድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ።»  ኢሳ ፲፬፣፲፪-፲፭።
በዚህ መልኩ እጅግ በጣም ጥቂት የሆነው የትንቢት ክፍል ስላለፈው ይናገራል።
፪. በነበሩበት ዘመን ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ የተናገሩ፡
አብዛኛው የትንቢት ክፍል እስራኤላውያን በነበሩበት ነባራዊ ሁኔታ የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያዎች፣ የሚደርስባቸውን ቅጣቶች ይናገራል። ይህም ሁኔታ ከምርኮ በፊት፣ በምርኮ ጊዜ እና ከምርኮ በኋላ ተብሎ የሚከፈለው መሆኑን ዝቅ ብለን እንመለከታለን።
፫. ከወቅታዊው የእስራኤላውያን ጉዳይ ባሻገር ስለመጪው ሩቅ ዘመን የተናገሩ
ይህ ክፍል እስራኤላውያን የነበሩበትን ወቅታዊ ሁኔታ ሳይሆን ስለቀጣዩ ዘመን ስለ አዲስ ኪዳን ስለ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለሐዋርያት፣ ስለቤተክርስቲያን፣ ስለመጨረሻው ዘመን ወዘተ… የተናገሩ ናቸው። ለአብነት ያህል በነቢዩ በኢሳይያስ ስለ ክርስቶስ የተነገረው መፈጸሙን ማቴዎስ ጽፎአል። ትንቢት ፍጻሜ ያገኘ መሆኑን እንደዚህ እያደረጉ የሚጠቅሱ የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ብዙ ናቸው።
« ነገር ግን ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም። በመጀመሪያው ዘመን የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር አቃለለ በኋለኛው ዘመን ግን በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ ያለውን የአሕዛብን ገሊላ ያከብራል። በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው።»  ኢሳ ፱፣፩-፪።
« ኢየሱስም ዮሐንስ አልፎ እንደ ተሰጠ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ፈቀቅ ብሎ ሄደ። ናዝሬትንም ትቶ በዛብሎንና በንፍታሌም አገር በባሕር አጠገብ ወደ አለችው ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ።
በነቢዩም በኢሳይያስ። የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ የባሕር መንገድ፥ በዮርዳኖስ ማዶ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፥ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው  የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።»  ማቴ ፬፣፲፪-፲፯
ከላይ ባየነው ከይዘታቸው ሌላ የትንቢት መጻሕፍትን በተለያየ መንገድ በመከፋፈል ማጥናት ይቻላል። ከምርኮ ጋር በተያያዘ በተናገሩበት ዘመን፣ በትንቢታቸው ስፋት መሠረት፣ የተናገሩት ለማን እንደሆነ በመሳሰሉት ይከፋፈላሉ።
ሀ. ከምርኮ ጋር በተያያዘ በሦስት ይከፈላሉ።
፩. ከምርኮ በፊት የተጻፉ፡  ኢሳይያስ ፣ኤርሚያስ፣ ሚክያስ፣ ኢዩኤል፣ ናሆም፣                                                        
             ዕንባቆም፣ ሶፎንያስ፣  ሆሴዕ፣ አሞጽ፣  አብድዩ፣ ዮናስ
፪. በምርኮ ጊዜ የተጻፉ፡ ሕዝቅኤልና ዳንኤል
፫. ከምርኮ በኋላ የተጻፉ፡ ሐጌ፣ ዘካርያስና ሚልክያስ
ለ.  በትንቢታቸው ስፋትና መጠን በሁለት ይከፈላሉ፡፡
      ፩. ዐበይት ነቢያት፡ ኢሳይያስ፣ ኤርሚያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤል
      ፪. ደቂቅ ነቢያት፡  ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ   
ሐ. በሚናገሩላቸው አገሮች በሦስት ይከፈላሉ።
      ፩.  ለደቡብ መንግሥት (ለይሁዳ) የተነገሩ፡ ኢሳይያስ ፣ኤርሚያስ፣ ሚክያስ፣ ኢዩኤል፣ ናሆም፣ 
                                                    ዕንባቆም፣ ሶፎንያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤል፣
፪. ለሰሜኑ መንግሥት (ለእስራኤል) የተነገሩ፡ ሆሴዕ፣ አሞጽ፣  አብድዩ
፫. ለነነዌ የተጻፈ፡ ዮናስ
መ. በሚናገሩላቸው ሰዎች በሦስት ሊከፈሉ ይችላሉ።
         ፩. እግዚአብሔር ስለመረጠው አንድ ሕዝብ (ስለ እስራኤላውያን)
         ፪. በእስራኤላውያን ዙርያ ስላሉ ሌሎች ሕዝቦች (አሕዛብ)
፫. ስለ መሲሑ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በዚህ አከፋፈል እያንዳንዳቸው ከአንድ በላይ ላሉ ሰዎች ስለሚናገሩ መጻሕፍቶችን ማመልከት አይቻልም።
በአጠቃላይ ነቢያቱ ስላለፈውም ተናገሩ ስለመጪው ፡ ከምርኮ በፊትም ሆነ በኋላ መጨረሻ የሁሉም መድረሻ  ሃሳብ ወይም ግብ አንድ ነው። እርሱም አዳኙ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በትንቢት ክፍሎች ብቻ ሳይሆን መላው ብሉይ ኪዳን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ በምሳሌም ይሁን በትንቢት የሚናገረው ስለ ክርስቶስ መሆኑን ራሱ ባለቤቱ እንዲህ ሲል ተናግሯል።
« ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው። ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው።…… እርሱም፦ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው። » ሉቃ ፳፬፣ ፳፯ ና ፵፬።
ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ሲል መላው ብሉይ ኪዳን መሆኑን፡ ቀጥሎም በሙሴ ሕግ ማለት በኦሪት ክፍል ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም፣ በነቢያት ሲል አሁን ባየነው የትንቢት ክፍል እና በታሪክ ክፍል በሚገኙት ነቢያት፣ በመዝሙራት ሲል በመዝሙርና በቅኔ መጻሕፍት መሆኑን እናስተውላለን።
    « ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን  ተግተው እየፈለጉ መረመሩት፤ በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ፥ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ፥ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር።»        ፩ጴጥ ፩፣፲-፲፪፤
ከዚህ በተጨማሪ በትንቢት ክፍል ውስጥ እግዚአብሔር ከብሉይ ኪዳን ወደ አዲስ ኪዳን የሚያደርገውን አስደናቂ የቃል ኪዳን ሽግግር ይገልጻል። ኪዳን ማለት ውል፣ ስምምነት መሆኑን ካሁን ቀደም አይተናል። እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የሚሰራው በውል ነው። እንደኛ ውል የለሽ አይደለምና። ስለሆነም ቀደም ሲል በተናጠል ከአብርሃም፣ ከኖኅ ወዘተ.. ጋር ቃል ኪዳን (ውል) የነበረው ቢሆንም ከመላው እስራኤላውያን ጋር በሙሴ በኩል የገባው ቃል ኪዳን ብሉይ ኪዳን ተብሎ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ቃል ኪዳን ውል ተቀባዮቹ እስራኤላውያን ሊጠብቁት ባለመቻላቸው፣ ወይም ሕጉን በመጣሳቸው ያ ቃል ኪዳን ፈረሰ፤ ስለዚህም ብሉይ - ያረጀ፡ ያለፈ ተባለ። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ሌላ አዲስ ቃል ኪዳን እንደሚያዘጋጅ በዚያው በብሉይ ኪዳን አስቀድሞ በትንቢት ተናገረ።
« እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፦  ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል።»  ኤር ፴፩፣ ፴፩-፴፬።
ይህም አዲስ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዓለሙ ቤዛነት ባፈሰሰው በደሙ የመሠረተው በስሙ ለሚያምኑ፡ አምነውም ለጸኑ፡ ሁሉ የተዘጋጀው አዲስ ኪዳን እንደሆነ ጌታ ተናግሯል።
« እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ፦ ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው። » ሉቃ ፳፪፣፳።
እንግዲህ ብሉይ ኪዳን በዚህ መልኩ ወደ አዲስ ኪዳን ያሸጋግረናል ማለት ነው።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣይ የአዲስ ኪዳንን አራቱን ክፍሎች በሥነ ጽሑፋዊ ይዘታቸው መሠረት እንዲሁ በየተራ በዳሰሳ መልኩ እያየን ጥናታችን እንቀጥላለን። ስለዚህ በሚቀጥለው ክፍል የወንጌልን አጠቃላይ ይዘት እናያለን።
ይቆየን።

1 comment:

  1. You're so cool! I do not think I've read anything like that
    before. So wonderful to discover someone with
    genuine thoughts on this issue. Seriously.

    . thanks for starting this up. This website is one thing
    that is required on the internet, someone with a little originality!


    Feel free to surf to my page http://tinyurl.com/c42ketu

    ReplyDelete

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment