በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተከታታይ
ትምህርታችን ባለፉት ጊዜያት ለጥናታችን የሚያስፈልጉንን ነጥቦች ካየን በኋላ ለአጠቃላይ ግንዛቤ የብሉይ ኪዳንን እና የአዲስ ኪዳንን
ጠቅለል ያለ ታሪካዊ ዳሰሳ ተመልከተናል። በቀጣይ የመጽሐፍ ቅዱስ ሁለቱ ኪዳናት በተከፋፈሉባቸው ሥነ-ጽሑፋዊ ይዘት ቅደም ተከተል
መሠረት እያንዳንዳቸውን በየተራ እንመለከታለን።
ብሉይ ኪዳን በሥነ-ጽሑፋዊ ይዘቱ በአራት እንደሚከፈል ቀደም ብለን ተመልክተናል። እነዚህም፡
፩. ሕግ፡ - ከኦሪት ዘፍጥረት - ኦሪት ዘዳግም --- ፭ መጻሕፍት
፪. ታሪክ ፡- ከመጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ- መጽሐፈ አስቴር-- ፲፪ መጻሕፍት
፫. ጥበብ፡- ከመጽሐፈ ኢዮብ- መኃልየ መኃልይ
ዘሰሎሞን-- ፭ መጻሕፍት
፬. ትንቢት፡- ከትንቢተ ኢሳይያስ - ትንቢተ ሚልክያስ---፲፯ መጻሕፍት ናቸው።
ለዛሬ የሕግ ክፍል የሆነውን አምስቱን የኦሪት መጻሕፍት ጠቅለል አድርገን እናያለን።
ኦሪት የሚለው ቃል አራይታ ከሚለው የጥንት የሶርያ ቋንቋ እንደተገኘ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ይናገራል። ትርጉሙም
ሕግ፣ ትምህርት ማለት ነው። ይህም ሕግ ወይም ትእዛዝ ከእብራይስጡ ቶራህ ከሚለው ቃል እንደተገኘም ምሁራን ይናገራሉ። የሕግ ክፍል
የተባለው የኦሪት መጻሕፍት ኦሪት ዘፍጥረት፣ ኦሪት ዘጸአት፣ ኦሪት ዘሌዋውያን፣ ኦሪት ዘኊልቁ እና ኦሪት ዘዳግም የተባሉትን የመጀመሪያ
አምስት መጻሕፍት ያጠቃልላል። አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት ፔንታቱክ በመባልም ይታወቃሉ። አሁን ድረስ የአይሁድ እምነት ተከታዮች ዋና
መጻሕፍቶቻቸው እንደሆኑ ይነገራል።
አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት በአብዛኛው የተለያዩ ነገሮችን አጀማመር ይገልጹልናል። ከእነዚህም፡-
የፍጥረትን አጀማመር -የሰማይን የምድርን እና በውስጡ የሚገኙ ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ጅማሬ፣
በአዳምና በሔዋን መፈጠር መላው የሰው ዘር እንዴት እንደተባዛ እና ምድርን እየሞላ እንደሄደ፣
ኃጢአት እንዴት ወደዓለም እንደገባ እና ሰው እግዚአብሔርን ማምለክ እንዴት እንደተወ፣
እግዚአብሔር ከሰው ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ ከኖኅ፣ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን እንደጀመረ፣
በብሉይ ኪዳን ዋና የታሪክ ባለቤት የሆኑት የእስራኤል ሕዝብ አመጣጥ እንዴት እንደተጀመረ፣
የተጻፈ ሕግ፣ ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ግንኙነት ሊጠብቃቸው የሚገቡ በርካታ ሥርዓቶች…. ወዘተ አጀማመር ይገልጻል።
በኦሪት መጻሕፍት ውስጥ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያደረገለትን እንክብካቤ እና ትድግና፡ ሕዝቡም ለእግዚአብሔር ሊፈጽሙ የሚገባቸውን
ሥርዓትና ቅድስና ይዘረዝራል። የተሰጡት ሕግና ሥርዓቶች በጣም በርካታ፡ በዝርዝር እና ሁለመናቸውን የሚመለከት ነበረ። በሁለንተናቸው
አምላካቸውን በቅድስና እንዲመስሉ ለእርሱ የተለየ ሕዝብ እንዲሆኑ ስለእያንዳንዱ የሕይወት ክፍላቸው በዝርዝር እና በጥልቅ ተነግሯቸዋል።
አብዛኛው የኦሪት ክፍል ለጊዜው አሰልቺ የሚመስል በኋላ ግን ጠቃሚነቱ የሚጎላ በበርካታ ዝርዝር ሕግጋትና ሥርዓት የተሞላ ታሪካዊ
ፍሰት ያለው ክፍል ነው።