Thursday, October 4, 2012

ፍልስጥኤምና ዙርያዋ

Plestine map, read in pdf
ባለፈው ካርታ ከተመለከትነው ከኖኅ ልጆች ምድርን መከፋፈል በኋላ ብዙ ተባዙ ምድርም ሞሉአት ተብሎ በተነገረው አምላካዊ ቃል መሠረት የሰው ዘር እየበዛ እየተባዛ ሄደ። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረትና ዋና መልእክት ስለመላው ዓለም ሕዝቦች ታሪክ መዘገብ ሳይሆን ስለአንድ ሕዝብ ስለእስራኤላውያን በኋላም ከእነርሱ ስለሚገኘው ስለአንድ ሰው ስለኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ የታሪክ ፍሰቱ ከመካከለኛው ምሥራቅ አልወጣም። በዚህም ምክንያት መካከለኛውን ምሥራቅ በጥልቀት ማየት ያስፈልጋል። ከዚህ በታች የምንመለከተው ፫ኛ ካርታ ይህንን የመካከለኛውን ምሥራቅ የቀድሞ ዘመን አገሮች ያሳየናል።

ከካርታው እንደምንመለከተው ይህ የቀድሞው ዘመን የእስራኤል እና የዙርያዋ አገር በተራሮች፣ በወንዞች፣ በበረሃ፣ በባሕር፣ በሜዳም… የተሞላ ሁሉም የመልክአ ምድር ገጽታዎች የሚገኝበት ነው።
ፍልስጥኤም፣ ፍልስጥኤማውያን በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት መግለጫ መሠረት ከካም ነገድ የመጡ በደቡብ ከነዓን በባሕር (በታላቁ ባሕር) ዳር ባለው ሜዳ የነበሩ ሕዝቦች ናቸው። 
ፍልስጥኤማውያን እየበዙና እየበረቱ ሲሄዱ አካባቢያቸውን ሁሉ በመቆጣጠራቸው መላው ከነዓን ፍልስጥኤም እየተባለ ይጠራ ነበር። እስራኤላውያን ከግብጽ ምድር በሙሴ መሪነት መጥተው ይህችን ምድር ሊወርሱ ሲሉ ፍልስጥኤማውያንን ፈርተው በዙርያ መንገድ ወደ አገራቸው ገብተዋል። /የእስራኤላውያንን ጉዞ በቀጣዩ ክፍል ፬ ካርታ እንመለከታለን።/
በዚህ ካርታ ወደፊት በተያያዥነት ከምናያቸው ታሪኮች ውስጥ የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው።
፩. በዘመነ ቀደምት አበው አብርሃም በፍልስጥኤም ምድር በእንግድነት መኖሩ፡ ዘፍ ፳፩፣ ፳፪-፴፬።
፪. በዘመነ መሳፍንት መጨረሻ ፍልስጥኤማውያን እስራኤላውያንን መዋጋታቸው፣ ታቦቱን መማረካቸው ፩ሳሙ ፬-፭።
፫. በዘመነ ነገሥት ዳዊት ፍልስጥኤማዊ የነበረውን ጎልያድን ድል ማድረጉ ፩ሳሙ ፲፯. ወዘተ….  
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ሁሉንም በየቦታቸው ስንደርስ እናያቸዋለን።
ይቆየን።



No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment