በመጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር የመጀመሪያው ቃል (ንግግር)
በመጽሐፍ ቅዱሳችን በመጀመሪያው መጽሐፍ በመጀመሪያው ምዕራፍ እግዚአብሔር በመጀመሪያ የተናገረው ቃል ብርሃን ይሁን የሚል ነው። ከዚያ በፊት ባሉት ቁጥሮች በዝምታ (በአርምሞ) ሲሠራ ቆይቷል። ሰማይ፡ ምድር፡ ጨለማ፡ መላእክት…. የተፈጠሩት በዝምታው ነው። እግዚአብሔር በዝምታውም ይሠራል። በኀልዮ ይላሉ፡፡ ሲያስብ ይፈጸማል፡ ይከናወናል። የሰው ሃሳብ ምናባዊ የሆኑ ብዙ ነገሮችን ሊያወጣ ሊያወርድ ይችላል። እግዚአብሔር ግን በሃሳቡ ብቻ ተጨባጭ ነገሮችን ያስገኛል። ታላላቆቹና የፍጥረታት መሠረታውያን የተባሉት ፬ቱ ባሕርያት እሳት፡ ነፋስ፡ ውኃ፡መሬት የተፈጠሩት በኀልዮ፡ (በዝምታ) ነው።
እግዚአብሔር በምን ተናገረ?
እግዚአብሔርም፦ ብርሃን ይሁን አለ። እግዚአብሔርም… አለ። ይህ የተናገረበት ቃል ከሦስቱ አካላት አንዱ የሆነው አካላዊ ቃል ወልድ በኋላም ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ቃል ነው። እግዚአብሔር በሦስትነቱ ሥላሴ ሲባል አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው። ሥላሴ በአብ ልብነት ያስባሉ፡ በወልድ ቃልነት ይናገራሉ፡ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት ሕያው ሆነው ይኖራሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር የተናገረበት ቃል ወልድ ነበረ።
በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ዮሐ ፩፡ ፩።
ያ ቃል ወልድ በሐዲስ ኪዳን ሥጋን ለብሶ ሰው የሆነው፡ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው፡ ዓለምን ሁሉ ያዳነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ….. ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ዮሐ ፩፡ ፲፬።
ዛሬ እግዚአብሔር በምን ይናገራል?
- በብሉይ ኪዳን በዝምታ፡ በሕልም፡ በራእይ፡ በነቢያት፡…. በወልድ ቃልነት ይናገር ነበር።
ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ዕብ ፩፡፩
-በሐዲስ ኪዳን የሚያናግርበት መንገድ አንድ ብቻ ነው።
ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን። ዕብ ፩፡፪
እንግዲህ እግዚአብሔር ዛሬ እኛን የሚያናግረን በዚያው ቃል - በወልድ - በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንም የምናውቀው በተጻፈው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ እና በመምህራን አማካይነት ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር የሚያናግረንን ለማወቅ፡ ብሎም ለመታዘዝ ቃሉን - ይሄውም ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እና መጽሐፍ ቅዱስን - ማወቅ አለብን ማለት ነው። ይህ ቃሉ ዓለምን የፈጠረ - ፈጣሪ፡ ዓለምንም ያዳነ - አዳኝ ዛሬም የእኛን ሐይወት ያዳነ- የሚሠራ አካላዊ ቃል ነው። እግዚአብሔር ሲያናግረን ልናዳምጥና ልንጠቀምበት ይገባል።
እግዚአብሔር ምን ተናገረ?
እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን አለ። ብርሃንም ሆነ። ብርሃን ይሁን ። ይህ ብርሃን ጨለማውን ያስወገደ፡ ቀንና ሌሊትን እንዲለይ ያደረገ ብርሃን ነው። እግዚአብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ። ቁ. ፬። ጨለማና ብርሃን የተለየው ብርሃኑ ስለመጣ ነው። ከዚያ በፊት ዓለሙ ሁሉ ጨለማ ስለነበረ ከጨለማ ውጭ ሌላ ነገር ያለ አይመስልም ። ብርሃኑ ሲመጣ ግን ከጨለማ የተሻለ ነገር እንዳለ ታወቀ። የብርሃኑ መልካምነት፡ የሌሎችም ፍጥረቶች መልካምነት የተረጋገጠው ስለታዩ ነው። መልካም እንደ ሆነ አየ። ማየት የተቻለውም ብርሃን ስላለ ነው። ብርሃን ራሱ መልካም ሆኖ የሌሎችን መልካምነት አሳየ።
ዛሬ የተፈጥሮ ጨለማ ችግር አልሆነብንም። በጨለማው የፈረቃ ሰዓት ሳይቀር ብርሃንን አግኝተናልና - በኤሌክትሪክ። በምትኩ በተለያየ የሕይወት ጨለማ ውስጥ ያሉ ብዙ ወገኖች፡ በጨለማ የሕይወት ክፍሎች የምናልፍባቸው ብዙ ጊዜያቶች አሉ። ዓለም ያለባት ጨለማ - ጨለማው ራሱ የሚታይ ሌላውን ግን የማያሳይ ነው።
ደግሞም ኢየሱስ፦ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው። ዮሐ ፰፡፲፪።
ክርስቶስ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ካለ ዓለም ጨለማ አለባት ማለት ነው። የእርሱ ብርሃንነት ፀሐይን እንዳልሆነ ጨለማውም የተፈጥሮ ጨለማን ለማለት አይደለም። ስለዚህ ከተፈጥሮው ጨለማ ሌላ የሕይወት ጨለማ አለ ማለት ነው። ለመጀመሪያው የፍጥረት ቀን ጨለማ ብርሃን የሆነው ይህ አካላዊ ቃል ወልድ ብርሃን ይሁን ተብሎ ሲነገር እንደሆነ ሁሉ፡ ለዛሬውም የሕይወት ጨለማ ብርሃን የሚሆነው ያው አካላዊ ቃል ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሲነገር፡ ሲሰበክ ነው። ራሱም የዓለም ብርሃን ነኝ ብሎአል። እርሱ ራሱ የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ ካለ ሌላ ብርሃን ፍለጋ አንሄድም፡፡ ቃሉንም አንጠራጠርም። ከእርሱ ውጭ ሌላ ብርሃን የለም። ሊኖርም ከቶ አይችልም።
እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ። ካለ በኋላ በሌላ ቦታ ደግሞ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፡ ብሎአል። ማቴ ፭፡፲፬። የእኛ ብርሃንነት ግን እርሱን ለማንጸባረቅ እንጂ ከራሳችን ለማፍለቅ አይደለም። ---እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን (እያንጸባረቅን)--- ፪ቆሮ ፫፡፲፰። እርሱን ለመተካት፡ በጎን በተጨማሪ ለማብራት አይደለም። ያለው ፍጹም የሆነ፡ እንከን የሌለው ለዓለሙ ሁሉ ያበራ አንድ ብርሃን እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
እንግዲህ በመጀመሪያው የፍጥረት ቀን በመጀመሪያ የተናገረው ብርሃን ይሁን የሚለው ቃል ለጨለማው ዓለም ተስፋ የሚፈነጥቅ፡ የሌሎችንም ፍጥረቶች መልካምነት የሚያሳይ ግሩም ድንቅ ዘላለማዊ ቃል ነው። እግዚአብሔር የሚናገረው ለተስፋ፡ ለመዳን፡ ለመልካም እይታ ነው። ዛሬ እግዚአብሔር የሚናገርባቸው መምህራን / ስለርሱ የሚናገሩ አገልጋዮች ንግግራቸው ብርሃናዊ ነው ወይ? ተስፋን የሚሰጥ፡ ለፍቅር፡ ለመዳን፡ ለመልካም እይታ ነው ወይ? እውነተኛ አገልጋዮች ከዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትና ከእግዚአብሔር ቃል እንደምናየው ለብርሃናዊ አገልግሎት፡ መልካምነትን ለማሳየት ብቻ ይተጋሉ። ጥፋትና ክፋት የሚታይባቸው ሰዎች ቢኖሩ እንኳን አገልጋዮች ያጠፉትን ከአምላካቸው ጋር በንስሐ ለማስታረቅ ይጥራሉ እንጂ የነርሱን ጥፋት ለመዝራት አይፋጠኑም። እግዚአብሔር የሚናገረው ለብርሃን ለተስፋ ለመልካም እይታ ነውና እኛም የእግዚአብሔር የሆንነው ንግግራችን የተስፋ፡ የመልካም እይታ ይሁን። ብርሃን ይሁን።
ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ።
|
ሮሜ ፲፫፡፲፪።
Praise God 4 giving u such a precious vision.face bookin le melkaminnet yemmixeqem tiwuld bemahonih God bless u in abundance.10q
ReplyDeleteAmen mesmat &madreg yihunelen....
ReplyDelete