Monday, September 17, 2012

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ዳሰሳ - አዲስ ኪዳን


ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን አጠቃላይ ግንዛቤ ይረዳን ዘንድ በሁለቱ ኪዳናት ያሉትን ታሪኮች ጠቅለል አድርገን ለማየት የብሉይ ኪዳንን ታሪካዊ ፍሰት ባለፈው ትምህርታችን ማየታችን ይታወሳል። ለዛሬ የአዲስ ኪዳንን አጠቃላይ ይዘት እንዲሁ እንመለከታለን።
አዲስ ኪዳንን አዲስ ያሰኘው ብሉይ ኪዳን ያለፈ፣ ያረጀ ወይም የቆየ ስለሆነ ነው። ብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር የገባው ቃል ኪዳን ሲሆን በእነርሱ አለመታዘዝ ምክንያት ኪዳኑ ሊጸኛ አልቻለም።
«ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር።…. አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ »  ዕብ ፯፣ ፯ና ፲፫።
እስራኤላውያን እንታዘዛለን ብለው ቃል የገቡበትን ሕግ ሊያከብሩ ባለመቻላቸውና ሕጉን በመጣሳቸው እግዚአብሔር በዚያው በብሉይ ኪዳን ዘመን ሌላ አዲስ ኪዳን እንደሚመሠርት መናገሩን ካሁን ቀደም ጠቅሰን መማማራችን ይታወሳል። ዘጸ ፳፬፣፯።
« እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር
ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፦ ኤር ፴፩ ፣ ፴፩ - ፴፬
አዲስ ኪዳን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሠረተ ለእስራኤል ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም /የሰው ዘር የሚመለከት እግዚአብሔር በልጁ ሞት ለሰው ያደረገው የቸርነቱን ሥራ የሚያሳይ ኪዳን ነው።
እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ፦ ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው። ሉቃ ፳፪፣፳።
ካሁን ቀደም እንዳየነው ብሉይ ኪዳን ስለአንድ ሕዝብ - ስለ እስራኤላውያን ይናገራል፤ አዲስ ኪዳን ግን ስለ አንድ ሰው - ስለኢየሱስ ክርስቶስ ይናገራል። ስለዚህ መላው አዲስ ኪዳን ከክርስቶስ ምጽአት እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ይናገራል ማለት ነው። አዲስ ኪዳን በሥነ ጽሑፋዊና ትምህርታዊ ይዘቱ ወንጌል፣ ታሪክ፣ መልእክትና ትንቢት ተብሎ ከአራት ይከፈላል።
ወንጌል ማለት የምሥራች ቃል ነው። ይህም ወንጌል ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

«ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።» ሮሜ ፩፣፫-፬።


ወንጌሉ አንድ ነው። ጸሐፍያኑ ግን አራት ናቸው። ወንጌሉ የክርስቶስ መሆኑን በአራቱም ወንጌላውያን መጻሕፍት መግቢያ ላይ «የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል….» ይላል። አራቱ ጸሐፍያን ግን ከተለያየ አቅጣጫ በጊዜው ለተለያዩ ተደራስያን ያንኑ የምሥራች ቃል (ወንጌል) በተለያየ መልክ ጽፈውታል። ሁሉም ግን የክርስቶስን ነገር ከልደቱ እስከ ሞቱና ትንሣኤው ዘግበዋል። አራቱም ወንጌላውያን የክርስቶስን ነገር ከአራት አቅጣጫ እይታ ይጀምራሉ። የአንድ ምስል እይታ የተሟላ የሚሆነው ከአራት አቅጣጫ ሲታይ መሆኑን ልብ ይሏል። ከፊትለፊት፣ከላይ፣ ከጎን፣ እና ከውስጥ። አራቱ ወንጌላውያን በአራቱ እንስሳ (ኪሩቤል)፣ በአራቱ ማዕዘናተ-ዓለም… እንደሚመሰሉ ይታወቃል። ወንጌላውያኑ የጀመሩበት ሁኔታ ሲታይ ማቴዎስ በዘር ሃረግ ቆጠራ፣ ማርቆስ በመንገድ ከፋቹ በመጥምቁ ዮሐንስ፡ ሉቃስ በብሥራቱና በበረት እንዴት እንደተወለደ፡ ዮሐንስ በመለኮታዊ ማንነቱ ቀዳማዊ መሆኑን  በመጥቀስ የክርስቶስን ልደቱን ጽፈዋል። ሲጨርሱ ግን አራቱም መከራና ሞቱን (ትንሣኤውንም) በመዘገብ በአንድ ዓይነት አጨራረስ ነው። ምክንያቱም የሞቱና የትንሣኤው ነገር የአዲስ ኪዳን ዋናው እና ሊታለፍ የማይችል መሠረታዊ ጉዳይ ነውና። ስለዚህ ጠቅለል ባለ መልኩ ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ፣…..ሞቶ ተነሳ ብሎ የሚናገር የምሥራች ቃል ነው።

የሐዋርያት ሥራ ኢየሱስ ክርስቶስ የመረጣቸውን ደቀ መዛሙርት ካዘዛቸው በኋላ የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ተቀብለው ወንጌሉን እንዴት ወደ ዓለም እንዳሰራጩ፣ ሐዋርያትም ለዚህ ወንጌል የከፈሉትን ዋጋ እና የቤተ ክርስቲያንን መመሥረት ይናገራል። «ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላእለ ኩሉ ጉባዔ ዘሐዋርያት - ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።» እንዲል ጸሎተ-ሃይማኖት። ቤተ-ክርስቲያን ሲባል የክርስቲያኖችን ኅብረት የሚያመላክት ነው። ለዚህም የወንጌል ስርጭት ሐዋርያዊ ተልዕኮ የጳውሎስና የጴጥሮስ ሚና ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው።

መልእክታቱ በጌታ የተመረጡት ሐዋርያት ያስተማሯቸውን ግለሰቦች እና የመሠረቷቸውን አብያተ ክርስቲያናት (የክርስቲያኖች ኅብረት) ለማጽናት የጻፏቸው ናቸው። አብዛኞቹም ሲጀምሩ በዚች አገር ላለች ቤተ ክርስቲያን፣ ምእመናን ይላሉ። የቆሮንቶስ፣ የገላትያና የተሰሎንቄን መልእክት መጀመሪያ መመልከት ይቻላል። በዚያ ያሉ የክርስቶስ ወገኖችን -ክርስቲያኖችን- ማለታቸው ነው። ክርስቲያን - የክርስቶስ ማለት ነው። በእንግሊዝኛው ቅጽል/adjective/ ነው። Christ – Christian ። ቤተ-ክርስቲያን - የክርስቲያን/የክርስቶስ ወገን ማለት ነው፤ ቤተ-እስራኤል- የእስራኤል ወገን/ዜጋ እንደሚባለው።

መልእክታቱ በይዘታቸውም ስለድኅነት መንገድ፣ ስለሙታን ትንሣኤ፣ ስለማኅበራዊ ኑሮ፣ ስለ ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር ስለ ሥርዓት፣ ከሐሰት ትምህርቶች ስለመጠንቀቅ… የመሳሰሉትን በርካታ ጉዳዮች እያነሱ ሰፊ አስተምህሮዎችን ይዳስሳሉ። ከእነዚህም ተጠቃሽ የሆነው የአሕዛብ ሐዋርያ በመባል የሚታወቀው ጳውሎስ ብዙ መልእክቶችን በመጻፍ፣ ብዙ ጉዳዮችን በመዳሰስ፣ ብዙ ቦታዎችን በወንጌል በመድረስ ዋና ተጠቃሽ ሐዋርያ ነው።

የመጨረሻው የአዲስ ኪዳን ክፍል የትንቢት ይዘት ያለው የዮሐንስ ራእይ ነው። የክርስቶስ ወንጌል በሐዋርያት በኩል ወደ ዓለም ከተስፋፋ በኋላ ስላለው የመጨረሻው ዘመን የቤተ-ክርስቲያን ሁኔታ እና የዓለም ፍጻሜ እንዲሁም ይህች ዓለም ካለፈች በኋላ ስለሚገለጸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንዲሁም መንግሥተ ሰማያት ይናገራል። አሁንም ቤተ ክርስቲያን ከሚለው የክርስቲያኖች ኅብረት ሃሳብ ሳንወጣ ይህ የዮሐንስ ራእይ በመጀመሪያው ክፍሉ በእስያ የሚገኙትን ሰባቱን አብያተ ክርስቲያናት በመውቀስ እንደሚጀምር እናያለን። ራእ ፩ - ፫። ኢየሱስ ክርስቶስን የታረደው በግ ብሎ በመጥቀስ የበጉ ሠርግ፣የበጉ ሙሽራ፣ የበጉ የሕይወት መጽሐፍ … እያለ የክርስቶስን ሥራወች በልዩ አገላለጽ ይናገራል። የዮሐንስ ራእይ በመጽሐፍ ቅዱስ ከሚገኙት መጻሕፍት ሁሉ በአጻጻፉ ረቂቅ የሆነ በሥዕላዊ መግለጫዎች የተሞላ ለየት ያለ መጽሐፍ ነው።

በአጠቃላይ አዲስ ኪዳን እግዚአብሔር በልጁ ደም የመሠረተው፣ የክርስቶስ የሆኑ ነገሮችን የሚናገር የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ዋና ክፍል ነው። የክርስቶስ ስለሆኑ ብዙ ነገሮች ሲባል የክርስቶስ ልደት፣ ጥምቀት፣ ጾም ጸሎት፣ ትምህርት፣ ተአምራት። የክርስቶስ መከራ፣ ሞት፣ ትንሣኤ፡ ዕርገት፡ ዳግም ምጽአት። የክርስቶስ ወንጌል፡ የክርስቶስ ደቀ-መዛሙርት/ሐዋርያት፣ የክርስቶስ ወገን- ቤተ ክርስቲያን…. ወዘተ የሚሉት ይጠቀሳሉ።

በአጠቃላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ዳሰሳ በብሉይ ኪዳን ስለአንድ ሕዝብ ስለእስራኤላውያን በአዲስኪዳን ደግሞ ስለ አንድ ሰው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ጠቅለል ባለ መልኩ  መልኩ ማየት ይቻላል። ስለብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን ንጽጽር ካሁን ቀደም የተማርነውን ለመከለስ ይህንን ይጫኑ

እንግዲህ በዚህ መልኩ የመጽሐፍ ቅዱስን ጠቅለል ያለ ይዘት ካየን በመቀጠል የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሚከፋፈሉበት ሥነ-ጽሑፋዊ አከፋፈል መሠረት የእያንዳንዳቸውን ይዘት ደግሞ ጠለቅ ብለን እያየን ጥናታችን እንቀጥላለን።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣይ ከብሉይ ኪዳን የመጀመሪያ የሆነውን የኦሪትን ክፍል ይዘት እናያለን።
ይቆየን። 

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment