Friday, September 7, 2012

በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ


ይህን ቃል የምናገኘው በመዝሙረ ዳዊት መዝ ፷፭፣ ቁጥር ፲፩ ላይ ነው።  «በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል።» በግዕዙ «ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ - የምሕረትህን ዓመት አክሊል ትባርካለህ» ይላል።
በቸርነትህ፡- እግዚአብሔር የዓለማት እና የዘመናት ፈጣሪ፡ ብቻ ሳይሆን አስተዳዳሪም ነው። ዓለማት የተፈጠሩት፣ ዘመናት የሚቆጠሩት በቸርነቱ ነው። ማንም ሰው በዚህ ሃገር፣ በዚህ ዘመን ልፈጠር ብሎ ሃሳብ አላቀረበም። የሕልውናችን ምንጩ ቸርነቱ ነው። የተፈጥሮ ዑደት፣ የዘመናት መፈራረቅ፡ የዕፅዋት ዕድገት፣ የእንስሳት ሕይወት… ሁሉ የቸርነቱ ውጤት ነው። አንድ መምህር «ክረምቱ የሚገባው በባለሥልጣኖች ፊርማ ቢሆን ኖሮ ዝናብ ሳይጥል ኅዳር ታኅሳስ ይሆን ነበር።» ብሏል፤ እግዚአብሔር ከመላው ፍጥረት እና ከሕይወት ጋር የተያያዙትን ነገሮች በራሱ ብቻ ቁጥጥር ሥር አድርጓቸዋል። ፀሐይ የምትወጣው፣ ክረምት የሚገባው፣ እህሉ የሚበቅለው…. በቸርነቱ ነው። እኛ ክፉ ብንሆንም፣ በኃጢአት ብንጸናም፡ የእርሱ ቸርነት አልተቋረጠችም። የእግዚአብሔርን መጋቢነት ከኛ ደግነት/ክፋት ጋር የሚያገናኘው ነገር ስለሌለ እርሱ ሁልጊዜም ፍጥረቱን መመገቡን አያቋርጥም። እግዚአብሔር ሰውን ፈጥሮ ሰውም እየበዛ ሲሄድ በዚያው ልክ ክፋቱ በመብዛቱ በኖኅ ዘመን አንድ ጊዜ ምድርን ካጠበ በኋላ የተናገረው ቃል እንዲህ ይላል፡-
«በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም።» ዘፍ ፰፣፳፪።
የሰው ልጅ ክፋት ቢበዛም ቸርነቱ እንዳልተቋረጠች ያሳያል፤ አሁንም እንደዚያው ነው። እርሱ እግዚአብሔር አይለወጥምና። ዛሬም ቸርነቱ ስላልተቋረጠ ሕልውናውን ለካዱት እንኳ ሳይቀር ፀሐይን ያወጣል፣ ዝናብን ያዘንባል።
«…እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።» ማቴ ፭፣፵፭።
የቸርነቱን ነገሮች ዘርዝረን አንጨርሰውም።

እግዚአብሔር በፈጣሪነቱ ሰውን ፈጥሮአል፤ መላውን ፍጥረት እኩል ይመግባል። በማዳኑ ደግሞ ያመኑትን ልጆቹ ያደርጋል፤ በሰማይ በዘላለም ሕይወት ያኖራቸዋል። እግዚአብሔር ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ ለሰው ልጆች ያደረገው ልዩ ቸርነቱ ሕያውነቱን ማካፈሉ ነው። ሁሉም ፍጥረታት ያልፋሉ፤ በምድር ካሉት ፍጥረታት ሁሉ የሰው ልጆች ብቻ (በሰማይ ካሉት መላእክት ብቻ) ከእግዚአብሔር ጋር ሕያው ሆነው ይኖራሉ።
ቸርነቱ በእኛ ላይ ስለበዛ፡
ይክበር ይመስገን መድኃኔዓለም የዓለም ቤዛ።
ዓመትን ታቀዳጃለህ፡-ሰው በተፈጥሮ ላይ የተገደበ ስልጣን ተሰጥቶታል። ተፈጥሮን እንዲገዛ፣ እንዲጠብቅ፣ እንዲንከባከብ እግዚአብሔር አዞታል። ሰውም ከእግዚአብሔር በተሰጠው፣ ከእንስሳት በተለየበት አሳቢ አእምሮው አማካኝነት በዓለም የሚገኙትን እግዚአብሔር የፈጠራቸውን ጥሬ ሃብቶች ተጠቅሞ ምድራችን ምን ያህል አንደለወጣት፣ ለኑሮም አመቺ እንዳደረጋት የምናየው ሃቅ ነው። አንድ መምህር «እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር ወደፊት መኪና እንደሚሠራ አውቆ ነዳጅን በምድር ውስጥ ደብቆ አስቀመጠለት፤» ሲል ሰምቼ ተገርሜያለሁ። እግዚአብሔር የሰውን ሙሉ ነጻነት ያከብራልና አሁንም ያው ሰው በዚያው አሳቢ አእምሮው ተጠቅሞ በፈጠራቸው የጦር መሣሪያዎች ምድርን የጥፋት አውድማ ማድረጉም በሌላ ጎኑ የምናየው የሥልጣኔያችን ውጤት አንደሆነም አይካድም።
የሰው ልጅ በተፈጥሮ ላይ የተገደበ ሥልጣን አለው ያልንበት ምክንያት በዘመናት ዑደት ላይ አንዳች ስልጣን እንደሌለው ለማሳየት ነው። በዘመናት ዑደት፡ የምሽትና የንጋት፣ የቀንና የሌሊት፣ የበጋና የክረምት፣ የሳምንታትና የወራት፣ የወቅታትና የዓመታት፣ …. መፈራረቅ ሂደትን ይመለከታል፤ ይቀበላል እንጂ አንዳች ተጽእኖ ማሳደር አይችልም። ጊዜውን ማዘግየት፣ ማቆም፣ ማፍጠን ወይም ወደኋላ መመለስ አይችልም። ይህ ማለት ጊዜ መቆም/ መፍጠን… አይችልም ማለት አይደለም። እግዚአብሔር ጊዜን ያስቆመበትና ያዘገየበትን ሁኔታዎች ቃሉ/መጽሐፍ ቅዱስ/ ይናገራል፡-
«እግዚአብሔርም በእስራኤል ልጆች እጅ አሞራውያንን አሳልፎ በሰጠ ቀን ኢያሱ እግዚአብሔርን ተናገረ በእስራኤልም ፊት እንዲህ አለ፦ በገባዖን ላይ ፀሐይ ትቁም፥ በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃ::
ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመ፥ ጨረቃም ዘገየ። ይህስ በያሻር መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ፀሐይም በሰማይ መካከል ዘገየ፥ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለም።»  ኢያ ፲፣ ፲፪-፲፫።
ይህ ማለት ጊዜው ቆመ ማለት ነው። ጊዜ የሚቆጠረው በፀሐይ መውጣት፡መግባት እንደሆነ መቼም ግልጽ ነው። ስለጊዜ ወደኋላ መመለስ በሌላ ቦታ እንዲህ ይላል፡-
« እነሆ፥ በአካዝ የጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ ከፀሐይ ጋር የወረደውን በደረጃዎች ያለውን ጥላ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ። ፀሐይም በጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ የወረደበት አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰ።»
ኢሳ ፴፰፣፰።
እግዚአብሔር የዘመናት ፈጣሪ ባለቤት ስለሆነ የፈለገውን ማድረግ ይችላል። ጊዜውን ማቆም/ማዘግየት ብቻ ሳይሆን በመጨረሻ ራሱን ዘመኑን ከናካቴው ያሳልፈዋል።
የምንኖርባት ዓለም ሕልውና መዋቅር ሥፍራ እና ጊዜ ነው። የሰው ልጅ በስፍራ በምድር እና በሚታዩት ፍጥረታት በተሰጠው ስልጣን ከምድር አልፎ ጨረቃ ላይ ቢወጣም በጊዜ ግን የአንዲት ሴኮንድ ተጽእኖ ማድረግ አይችልም። ምክንያቱም የጊዜያትና የዘመናት ዑደት ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር እጅ ብቻ ነውና። የሰው ልጅ «በሥልጣኑ» /በነጻ ፈቃዱ/ ወደ ጨረቃ ይሄዳል። እግዚአብሔር በቸርነቱ ዓመታትን ያቀዳጃል። ግን ልብ አድርጉ ወደ ጨረቃ መሄድ የሚቻለው ጊዜ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በምድርም ላይ ማንኛውም ነገር የሚከወነው ጊዜ ሲኖር፣ ዕድሜ ሲኖረን (ስንኖር-ካልሞትን) ብቻ ነው። ስለዚህ ሁሉም የሰው ልጅ እንቅስቃሴ- ልማቱም / ጥፋቱም በጊዜ ላይ የተመሠረተ ነው። ጊዜ ደግሞ በእግዚአብሔር እጅ ነው። እንግዲህ ፍጥረት ሁሉ ባያውቀውም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በእግዚአብሔር ቸርነት ሥር ነው ማለት ነው።
ዘመናት የሚለዋወጡት በቸርነቱ ነው። ሁላችንም በእድሜያችን ላይ ይችን ዓመት፣ በዘመናችን ላይ ይችን ዕለት፣ በውሎአችን ላይ ይችን ሰዓት ስለሰጠን እጅግ አድርገን ልናመሰግነው ይገባል። ይህ የቸርነቱ ውጤት ነውና። በየዓመቱ በአዲስ ዓመት እና በበዓላት «እንኳን አደረሰህ/ሽ» እንባባላለን። ስለዚህ አድራሽ አለ ማለት ነው። እርሱም ቸርነቱ ያልተቋረጠው፣ የፈጠረን እና የሚያኖረን ታላቁ አምላካችን የዘመናት ባለቤት እግዚአብሔር ነው።
«እንኳን አብሮ አደረሰን»።
«…ብቻውን ጥበብ ላለው ለእግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።» ሮሜ ፲፮፣፳፯።

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment