ባለፈው ክፍል የዓለምን ፍጻሜ አመላካች የሆኑ ከአሁን ቀደም እኔ ክርስቶስ ነኝ ብለው የተነሱ ሃሰተኞችን እንዲሁም በየቦታው
እስከዛሬ የተካሄዱ ጦርነቶችን መረጃዎች ማየታችን ይታወሳል። ዛሬም ይህንኑ መረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል እየተፈጸመ እንደሆነ
እናያለን።
ማቴ ፳፬፣፯… ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ
ልዩ ስፍራ ይሆናል፤
ራብም፡
ከየትኛውም ዘመን ይልቅ በያዝነው ክፍለ ዘመን ሕዝቦች በተለይ በታዳጊ ሃገሮች የሚገኙ ወገኖች በከፍተኛ ደረጃ በረሃብ
እየተጠቁ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም። የዓለማችን የሃብት ክፍፍል እና የሕዝቦች ስብጥር ሲነጻጸር ምን ያህል ፍትሐዊ እንዳልሆንን
ያሳያል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት 80% የሚሆነው የምድራችን ሃብት
20% በሆነው የዓለም ሕዝብ እጅ ይገኛል። የሚከተሉት እውነታዎች የዓለም የምግብ ፕሮግራም /World Food Program/ በተለያዩ ጊዜያት ካወጣቸው መረጃዎች የተወሰዱ ናቸው።
- እ.ኤ.አ በ2009 ዓ/ም ከአንድ ቢሊየን በላይ የሚሆን ሕዝብ በቂ ምግብ ማግኘት አልቻለም። ይህም ማለት የአሜሪካ፡ የአውሮፓ
እና የካናዳ ሕዝብ ቢደመር እንኳ ይህን ያህል አይሆንም። በወቅቱ ከዓለማችን ከ6 ሰው አንዱ ለረሃብ የተጋለጠ ነበር ማለት ነው፡፡
ከእነዚህም 90 በመቶ በላይ የሚገኘው በታዳጊ ሃገራት ውስጥ ነው።
- ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ምክንያት በየቀኑ 25 ሺ ሕጻናት እና ወጣቶች ለህልፈት ይዳረጋሉ።
- ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ የሚኖርባቸው እስያ እና የፓሲፊክ አካባቢዎች በዓለም ከሚገኙት በረሃብ ከተጠቁት
2/3 ኛው ይገኝባቸዋል።
- በአሁኑ ሰዓት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት /malnutrition/ ከኤች አይ ቪ/ኤድስ፡ ከቲቢ እና ከወባ ከሶስቱም ድምር
በላይ ሕጻናትን እየቀጠፈ ያለ የዓለማችን ችግር ነው። ከአራት ሕጻናት አንዱ የተመጣጠነ ምግብ አያገኝም። በታዳጊ ሃገራት ከ10
ሚሊየን በላይ ለሚሆነው የሕጻናት ሞት 60 በመቶ ምክንያቱ ይሄው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነው። ከ9 ሚሊየን በላይ ለሆነው ከአምስት
ዓመት በታች ባሉ ሕጻናት ለደረሰው የሞት አደጋ ምክንያቱ ይሄው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነው። ይህ ማለት በየ6 ሴኮንድ አንድ
ሕጻን ይሞታል ማለት ነው።
- ከዓለማችን ሕዝብ ከ7 ሰው አንዱ ራቱን ሳይበላ ይተኛል።…….
እንግዲህ እነዚህ ሁሉ እውነታዎች ምን ያሳዩናል? ጌታ የዓለምን ፍጻሜ መቃረብያ ምልክት ራብም በምድር ላይ ይሆናል ያለው
ቃል እየተፈጸመ መሆኑን አይደለምን? ታዲያ ከኛ ምን ይጠበቃል?
ቸነፈርም
ቸነፈር ማለት እጅግ አደገኛ እና ገዳይ የሆነ በጊዜውም መድኃኒት (መፍትሄ) ያልተገኘለት ወረረሽኝ (በሽታ) ማለት ነው።
የሚከተሉት ከበርካታ የተለያዩ መረጃዎች በጥቂቱ የተወሰዱ ናቸው።
ቫይረሱ ከተገኘበት ከ1981 ዓ/ም አንስቶ እስከ አሁን በ30 ዓመት ውስጥ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ምክንያት ከ25 ሚሊየን
ሕዝብ በላይ ሕይወቱ አልፎአል። በየዓመቱ ከ800ሺ በላይ ሰው ይሞታል ማለት ነው።
በ1340ዎቹ መጨረሻ ዓ/ም በመከካከለኛው እስያና በምዕራብ አውሮፓ የተከሰተ ጥቁሩ ሞት (Black death) የሚል ቅጽል
ስም የተሰጠው ወረረሽኝ ከ75 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል። በዓለማችን በአንድ ጊዜ እንደዚህ ያለ የሰዎች እልቂት
በሌላም ምክንያት እንኳ ደርሶ አያውቅም። በ1918 በኢንፍሎዌንዛ ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎች በዓለማችን ሞተዋል። በእነዚህ ሁለቱ
ወረርሽኝ የደረሰው የሰው ልጆች ሞት በዓለም ታሪክ የመጀመሪያው ነው።
በኮሌራ፡ በወባ፡ በታይፈስ እና በኢንፍሎዌንዛ በሽታዎች በተለይ በግብጽ፡ በቻይና እና በራሻ እስከዛሬ ድረስ ወደ 75
ሚሊየን የሚሆን ሰው ሞቷል።
ይህስ ምን ያሳየናል? የጌታ ቃል እየተፈጸመ መሆኑን አይደለምን?
የምድርም
መናወጥ
ከምድር መናወጥ ተፈጥሮአዊ ክስተቶች አንዱ የመሬት መንቀጥቀጥ ነው። ይህም የሚለካው በሬክተር ስኬል ሲሆን መጠኑ ምንጊዜም
ከ10 በታች ነው። የተለያዩ መዛግብት እንደሚያሳዩት እ.ኤ.አ. ከ1900 ዓ/ም ጀምሮ ዓለማችን በተለያዩ ስፍራዎች በሬክተር ስኬል
9 እና ከዚያ በላይ በየ10 ዓመት አንድ ጊዜ፡ 8 እና ከዚያ በላይ የሆነ በየዓመቱ፣ 7 እና ከዚያ በላይ በየዓመቱ 15 የመሬት መንቀጥቀጥ ይከሰታል። እ.ኤ.አ. ከ2000 ዓ/ም ጀምሮ
እስከ አሁን ድረስ በጠቅላላው ከ290 ሺ በላይ የመሬት መንቀጥቀጦች በተለያየ ቦታ ተከስቷል፤ በዚህም ከ800 ሺ በላይ ሰዎች ሞተዋል።
በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ከሚደርስባቸው ሃገሮች ጥቂቶቹ ቺሊና ፔሩ /ደቡብ አሜሪካ/፣ አሜሪካ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ቻይና፣
ራሻ፣ ጃፓን ሲሆኑ እስከዛሬ በታሪክ የከፋ የተባለው የመሬት መንቀጥቀጥ በ1500 ዎቹ አካባቢ በቻይና የተከሰተው ሲሆን በወቅቱ የሬክተር ስኬል ባለመኖሩ
መጠኑን ማወቅ ባይቻልም ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ለሞት እንደተዳረጉ ይነገራል። የሬክተር ስኬል ከተጀመረበት ከ1930 ወዲህ
ከተመዘገቡት የከፋ የተባለው በቺሊ /ደቡብ አሜሪካ/ እ.ኤ.አ. በ1960 ዓ/ም የተከሰተው ሲሀን መጠኑም በሬክተር ስኬል 9.5
የደረሰ ነበር። በዚህም ከ1600 በላይ ሰዎች ሞተዋል፤ ግምቱ ከ800 ቢሊየን በላይ የሚሆን ንብረት ወድሟል።
በዚህና በሌሎችም ዙርያ ብዙ ብዙ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። የዓለምን ፍጻሜ ምልክቶች የሚያሳዩ እንደ ትንቢተ ዳንኤል፣
ዮሐንስ ራእይ ያሉ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ፤ ሁሉንም በየቦታቸው ስንደርስ እናያቸዋለን። በዚህ ክፍል ግን ማሳየት የተፈለገው
ጌታ ራሱ በወንጌል ከተናገረው ውስጥ በዓለማችን ባሉ መረጃዎች እያመሳከርን ቃሉ እንዴት እየተፈጸመ እንደሆነ ለማሳየት ያህል ነው፡።
እንግዲህ የሰማይ የምድር ባለቤት ቃሉ አያልፍምና ይሄው በተጨባጭ እየተፈጸመ መሆኑን እያየን ነው። «ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።» ማቴ ፳፬፣፴፮። ብሎ
የተናገረው ይህ አይደለምን? የጌታ ቃል ሳይፈጸም አይቀርም። ሳይፈጸም አለማለፉንም የዘመኑ ሳይንስና መረጃዎች ምስክር ናቸው። ራሳችንም
በዓይናችን እያየን ነው። ታዲያ የዓለም ፍጻሜ በዓይናችን እያየነው እየተቃረበ ከሆነ ምን ይሻለናል? የጽሑፉ ዓላማ ሽብር ለመልቀቅ
አይደለም። ዓለማችን ወደ ፍጻሜዋ እያመራች መሆኑን አውቀን እንድንዘጋጅ ነው። የምንዘጋጀውም አምላካችንን በሚያስከብር ሕይወት እንደቃሉ
በመኖር ነው።
« ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ
በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።» ማቴ ፳፬፣፵፬
No comments:
Post a Comment
አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment