Sunday, August 26, 2012

የጥያቄ፩- መልስ


 1.  እግዚአብሔር  አዳምን  ከመፍጠሩ  በፊት  አዳም  እንደሚሳሳት ያውቃል/አያውቅም?  እንደሚሳሳት  ካወቀ ለምን  ፈጠረው?  
  ወደጥያቄው መልስ ከመግባታችን በፊት ስለእግዚአብሔር ና ስለ ሰው ባሕርያት በጥቂቱ ማወቅ  ያለብን ጉዳይ አለ። እግዚአብሔር የማይመረመር፡ ልዑልና ኃያል አምላክ ስለሆነ ስለራሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ እናውቃለን እንጂ ሙሉ በሙሉ ልንደርስበት አንችልም። የሰው ልጅ በሁለንተናው ውሱን ነው። ዓይናችን የሚያይበት፡ ጆሮአችን የሚያደምጥበት፡ እጃችን የሚዘረጋበት…. ሁለንተናችን ገደብ አለው።   ስለፈጣሪ ማወቅ አይደለም ስለፍጥረታት እንኳን ገና ያልደረስንባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ስለሆነም በአስተሳሰባችን ተነስተን የእግዚአብሔርን ሃሳብና አሠራር እንዲህ ቢሆን እንዲህ ይሆናል ብለን የራሳችን ግምት ልንወስድ አንችልም። ከውስንነታችን የተነሳ።


እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ነው። ያለፈውን፡ የአሁኑን፡ የሚመጣውን ሁሉ ያውቃል። ዕውቀቱ ፍጹምና ገደብ የሌለው በመሆኑ አዳምን ከመፍጠሩ በፊት እንደሚሳሳት ያውቃል። በልጁ በክርስቶስ ሞት እንደሚያድነውም ያውቃል። ይህ ማለት ግን አዳም እንዲሳሳት ወስኖበታል ማለት አይደለም። አዳም በአሳቢ አእምሮው ተጠቅሞ ትእዛዙን የመጠበቅ/የመጣስ (ዕጸ-በለስን የመብላት/ያለመብላት) መብት የነበረው ነጻ ሰው ነው።
እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ የሚያከናውነው በዕቅድ ነው። ከዘላለማዊነቱ የተነሳ ይህ ዕቅዱ  በሰዎች ምርጫና  ድርጊት (ክፉም ይሁን ደግ) የማይለወጥ ነው። ነገሮች ሁሉ አስቀደመው በርሱ ዘንድ መታወቃቸው የሰዎችን ነጻ ፍላጎትና ድርጊት አይገድበውም። ማንኛውም ድርጊት ደግሞ  ከርሱ ሥልጣንን ና ቁጥጥር ውጪ ነው ማለትም አይደለም። ልንመረምረው በማንችለው ሁኔታ በሰዎች ምርጫና ድርጊት ውስጥ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ ይፈጸማል።
እንግዲህ በአንድ በኩል የሰዎች ድርጊት በሙሉ የዘላለማዊ ዕቅዱ ማስፈጸሚያ አካል ሲሆኑ  በሌላ በኩል ሰዎች በነጻነታቸው ለሚፈጽሙት ድርጊት ሁሉ ደግሞ ኃላፊነቱን ይወስዳሉ፡ ተጠያቂም ይሆናሉ።
አንድ መምህር እንዲህ ብሏል። ለሰው ልጅ የተሰጠውን ነጻ ፈቃድ እግዚአብሔርም ሆነ ሰይጣን አይጋፉትም። ይህ ማለት እግዚአብሔር በግድ ሰዎችን አያጸድቅም። ሰይጣንም በግድ ሰዎችን ኃጢአት አያሰራም። «ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል።» ያዕ ፩፡ ፲፬። እግዚአብሔር የመዳን (የሕይወት) ጥሪ፡ ሲያቀርብ ሰይጣን የኃጢአት (የሞት) ጥሪ ያቀርባል። ሰው ከሁለቱ አንዱን መምረጥ ይችላል። የመረጠውን ነገር ውጤት ግን ይቀበላል እንጂ አይመርጥም።
ስለሆነም ምንም እንኳ በዘላለማዊ ዕቅዱ እግዚአብሔር አዳም እንደሚሳሳት ቢያውቅም አዳም ግን የተሳሳተው በራሱ ሙሉ ነጻነት በወሰደው ምርጫ እንጂ እግዚአብሔር ያሳደረው አንዳች ተጽእኖ አልነበረም። እንዲያውም እንዳይሞት ባይበላ እንደሚሻለው መክሮታል። በዚያም ሆነ በዚህ የእግዚአብሔር ዕቅድ (አሳብ) ተፈጻሚ ነው።
ግን የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ ምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ በሚነግረን መሠረት።
«ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን። በበጎ ፈቃዱ እንደወደደ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ  ወሰነን።---- በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም  በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።»  ኤፌ ፩፡ ፬ ፭ ፲
«እድፍ እንደሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ።» ፩ጴጥ ፩፡ ፳።
እግዚአብሔር ዓለሙን ከመፍጠሩ በፊት በሰው ኃጢአት አንደሚበላሽ ስለሚያውቅ መድኃኒቱንም አስቀድሞ አዘገጅቷል። ዓለሙን ሳይፈጥር ቢቀር፡ ለርሱ የሚጎልበት አንዳች ነገር የለም። ሲጀመር የኛ መፈጠር ለርሱ የጨመረለት፡ የኛም አለመኖር ለርሱ የሚያስቀርበት አንዳች ነገር የለም።
ከጥያቄው ቀጥተኛ መልስ አንጻር ሊኖሩ የሚችሉት ሀሉት አማራጮች ናቸው።
F አዳምን እንደሚሳሳት አወቆ ባይፈጥረው እኛ አንኖርም፡ እርሱ ግን አለ። እንደነበረም ይኖራል። እዚህ ላይ ያበቃል።
F  ነገር ግን ቢፈጥረውና ከወደቀበት ኃጢአት በልጁ በክርስቶስ ሞት ቢያድነው  ይበልጥ እንድናውቀው አድርጎናል። ይህም የተፈጸመውና ያየነው አሳቡ ነው፡፡
ተጨማሪ ሃሳብ፡ ማብራሪያ ወይም ጥያቄ ካለ ከዚህ ጽሑፍ ስር comments የሚለውን በመጫን post comment በሚለው ሥር ማቅረብ ይቻላል።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ሃሳብ ይሰጥበትና እንቀጥላለን። ካልሆነ ወደ ሌላ ጥያቄ እናልፋለን።
ይቆየን። 



12 comments:

  1. ሰማይ ወምድር የሀልፍ ወቃልየሰ ኢየሀልፍ::

    ReplyDelete
  2. I don't think this question has an answer. Honestly, this is a question which I never got the answer. I am not satisfied with your answer.
    Egziabher lemin sewun benetsa fekad feterew???dn please find another answer.
    What I lately convinced is it is beyond human knoledge! no one can answer it. I heard your answer through out my life.
    ende, lemin tiru yeminasib bicha adirgo ayifetirenim?
    Ye esun menor lemasawok lela menged yelem woi?
    A'EMIRO'ACHIN WUSIN NEW ZIM MALET SAYISHAL AYIKERIM.

    ReplyDelete
  3. ሠላም ወንድሜ/እህቴ/
    ስለአስተያየቱ/ጥያቄው አመሰግናለሁ። የእግዚአብሔርን አሠራር ውስን በሆነው አእምሮአችን መረዳትም፣ መመርመርም እንደማንችል ጠቅሻለሁ። በተሰጠን አገናዛቢ አእምሮ ግን የቻልነውን ያህል እንማራለን፤ ስለርሱም ለማወቅ እንጥራለን፤
    ጥያቄው መልስ የለውም ብሎ መቀመጥ ቀላል ነው። ግን ከመወያየት ብዙ ነገር ይገኛል። የጥያቄው መልስ አላረካኝም ማለት ይቻላል። ግልጽ ያልሆኑትን ጉዳዮች በነጥብ፣ በነጥብ ማየት ግን ይሻላል። ጥያቄውን ማንም ሊመልሰው አይችልም ብሎ መደምደም ግን ያስቸግራል፤ እግዚአብሔር ዕውቀቱን የገለጸለት ሊኖር ይችላልና፤ መድረኩም የተከፈተውም ለዚህ ነው። እንድንማማር። በበኩሌ የምችለውን ልበል። ሌሎችም እንዲሳተፉ እጋብዛለሁ። ከተነሱት ሶስት ነጥቦች በአንዱ ልጀምር።
    እግዚአብሔር ሰውን በነጻ ፈቃድ ለምን ፈጠረው? ጥሩ ጥያቄ ነው። እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው ሙሉ ነጻነት ካልሰጠው በተዘዋዋሪ እና በግድ የእርሱ ተገዢ እንዲሆን ይፈልጋል ማለት ነው። እርሱ በነጻነት፡ በፍላጎታችን እንጂ በግድ እንድናመልከው አይፈልግም። ከፍጥረታት ሁሉ ሰውን እና መላእክት ብቻ ከሙሉ ነጻነት ጋር ተፈጥረዋል። ነጻነቱ የፍቅሩ መግለጫ ነው። ፍቅር እውነተኛ የሚሆነው የመጥላት አማራጭም ሲኖርህ ነው። ነጻነት ማለት ነው። ካለዚያ በግድ እንድትወደው ከተደረግህ አንተ ነጻነት ያለው ሰው ሳትሆን ዕቃ ሆንክ ማለት ነው። እውነተኛ ፍቅር ለወዳጁ ሙሉ ነጻነትን ይሰጣል እንጂ እንደ ዕቃ ካልተለየኀኝ አይልም። ሁላችንም ሞባይላችን እንወዳለን፣ እንዲለየንም አንፈልግም። ዕቃ ነው። በራሱ ምንም ማለትም ማድረግም አይችልም። እግዚአብሔር ሰውን እንደ ዕቃ አይደለም የወደደው። አገናዛቢ አእምሮ ሰጥቶ በዚያው ተጠቅሞ አምኖበት እንዲወደው እና ከእርሱ ጋር እንዲቀጥል ይፈልጋል እንጂ በማስገደድ አይደለም። ነጻ ፈቃድ ከሌለንማ ከሌሎች ግዕዛን ፍጥረታት በምን ተለየን? ዕፅዋት አይንቀሳቀሱም፣ እንስሳት አያስቡም... ሰው ግን ከእነዚህ ሁሉ በላይ ነው። ሙሉ ነጻነት አለው፤ ያም የሰውነቱ መገለጫ፣ የእግዚአብሔርም የፍቅሩ መግለጫ ነው።
    በዚህ ጉዳይ እንስማማ እና ወደ ቀጣዮቹ አልፋለሁ።
    «መንፈሱና ሙሽራይቱም። ና ይላሉ። የሚሰማም። ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፥ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ።» ራእ ፳፪፣፲፯።

    ReplyDelete
  4. "netsa fekad setichehalehu ena endefelegihew hun" ayi dn!
    lemin endemelayikit ayifetirenim neber? mela'et netsa fekad yelachewum malet new?
    Yemejemeriawun yemelaekitin fetena sayichemir malete new? I will say more

    ReplyDelete
  5. ሠላም ወንድሜ/እህቴ
    በቅድሚያ ስለውይይቱ አመሰግናለሁ። ይሄውልህ ነጻ ፈቃድ ሰጥቶ እንደፈለግህ ሁን አላለውም። የሚጠቅመውን ምክር እና ማስጠንቀቂያ በትዕዛዝ መልክ ሰጥቶታል።
    «እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ
    ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።» ዘፍ ፪፣፲፮-፲፯።
    እግዚአብሔር የሚበጀንን ነገር ይመክረናል፤ የሚጎዳንን ነገር ያስጠነቅቀናል። በነጻነት መምረጥ የኛ ድርሻ ነው። ይሄ ማለት እንደፈለግን እንድንሆን ለቀቀን ማለት አይደለም። ነግሮናል፤ ካልሰማን የራሳችን ችግር ነው።
    ለምን እንደመላእክት አይፈጥረንም ነበር? ለተባለው ነጻ ፈቃዳችን ለማለት ከሆነ መላእክትም እንደሰው ሙሉ ነጻ ፈቃድ አላቸው። ይሄንንም ከላይ በመጀመሪያው አስተያየቴ ጠቅሻለሁ። በደንብ አስተውለህ አንብበው። ከፍጥረታት ሁሉ ሰውን እና መላእክት ብቻ ከሙሉ ነጻነት ጋር ተፈጥረዋል። በዚያም ተጠቅመው አይደል ከመላእክት ሣጥናኤል ወደ ዲያብሎስ የተቀየረው? ራሱን ፈጣሪ ለማድረግ በመሞከሩ የተዋረደው?
    በአፈጣጠር ሰው ከመላእክት ይለያል፤ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሮአልና፡፡ ሁለቱም ነጻ ፈቃድ አላቸው። ሰው ግን ትዕዛዝና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ነው የተሳሳተው። ሣጥናኤል በራሱ ነጻነት ትዕቢትን አመንጭቶ ከፍ ለማለት ሞከረ፤ ግን በኋላ ተዋረደ።
    «አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህ!
    አንተን በልብህ። ወደ ሰምይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ
    ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ።
    ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጕድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ።» ኢሳ ፲፬፣፲፪-፲፭።
    ......ሃሳብ ይሰጥበትና እንቀጥላለን።

    ReplyDelete
  6. I know everything what you are saying. that is why I quest you and argue that the question has not proper answer. I don't know why? it is not like any other questions which you answer just mentioning a chapter and a verse from the bible.

    bachiru ye'ene hasab, lesew netsa fekad mesetet yelebetim! mikiniatum letifat enji le tikim alihonenim.
    ende! ende ensesat kemehonina wode gehaneb kemegibat yetu yishalal? ene ende ensesat mehon elalehu. ante ende eka endalikew malet new.
    In general, your answer is the as same to all others. but I have never been convinced. let me ask you a question, which one is better; going to hell with free will or entering heaven with no free will?????????? yalitemeleselign tiyake yihe new.

    I know that man is created with free will!!!!!!!

    ReplyDelete
  7. ሠላም ወንድሜ
    ስለሃሰብህ አመሰግናለሁ። ለሰው ነጻ ፈቃድ መሰጠት የለበትም የምትለው አሁን ባለህ ግንዛቤ ተመስርተህ ነው። እግዚአብሔር ግን ከኛ በላይ ያውቃልና ለሰው ነጻ ፈቃድ መሰጠት አለበት ብሎ ሰጥቶናል። ለምን? እኔም አንተም አሁን ላይገባን ይችላል። ያልገባኝን ነገር ግን አልቀበልም አልልም፤ እስኪገባኝ ጥረት አደርጋለሁ። እንዲገልጥልኝ ጌታየን እለምነዋለሁ።
    ይሄውልህ መጽሐፍ ቅዱስ ዋናው የክርስትና መመሪያችን፡ እግዚአብሔርም በዋናነት አሁን የሚናገርበት መንገድ ስለሆነ ከርሱ መጥቀስ ግድ ይለናል። ማንኛውም ነገር የሚዳኘው በቃሉ ነውና።
    ነጻ ፈቃዳችን ለጥፋት እንጂ ለጥቅም አላዋልነውም እንዴት ይባላል? ለጥፋትም ሆነ ለልማት ያዋልነው ራሳችን ነን። በኑሮ ጉዳይ ብንመለከት በነጻ ፈቃዳችን የሠራነው፡ ልማት አለ- በቤት፣ መኪና፣ ልብስ .. ምድርን አመቺ የኑሮ ስፍራ ማድረጋችን። ጥፋትም አለ፡- ይሄውም፡ የጦር መሣሪያ፣ እልቂት. ምድርን አስቸጋሪ መኖሪያም ማድረጋችን። በሕይወት ጉዳይም እንደዛው ነው፤ ከመረጥን ወደ ዘላለም ሕይወት ካልፈለግን ወደ ዘላለም ቅጣት የመሄድ ምርጫው የራሳችን ነው።
    «እንደእንስሳት /ዕቃ ሆኖ መንግሥተ-ሰማያት ከመግባት እና ከነጻ ፈቃድ ጋር ገሃነም ከመግባት» ላልከው ጥያቄው ራሱ ችግር አለበት። ጥያቄው ሊመለስልህ የማይችለው ትክክለኛ ጥያቄ ስላልሆነ ነው። እንደዚያ የሚባል ምርጫ የለም፣ ሊኖርም አይችልም። መንግሥተ ሰማያትም ሆነ ገሃነም እሳት ለመግባት ምርጫ ቀርቦልናል፤ የምንመርጠውም የምንወስነውም አሁን በምድር እያለን ነው። ነጻ ፈቃድህን ከጥፋት እና ከገሃነም ጋር ከምታያይዘው ለምን በርሱ መንግሥተ-ሰማያት የመግባት ዕድል አለኝ ብለህ አታስብም? ታዲያ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሞተው ለምንድን ነው? ሰው እንዲሁ ያለፈቃዱ እንደ እንስሳ/ዕቃ ወደ ዘላለም ሕይወት የማስገባት የተሻለ አማራጭ ካለ (አንተ እንደምትለው) እግዚአብሔር እርሱን አጥቶት ነው? ከሁሉም በላይ ጌታችን ለምን ሞተ? በርሱ አምነንበት እንድንድን እና ወደ ዘላለም ሕይወት እንድንገባ አይደለምን?
    በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሐ ፫፣፲፮።
    አንድያ ልጁን እስከሞት የሰጠው ሰዎች ነጻ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው (ፈቅደው) በእርሱ አምነው እንዲድኑ ነው።
    የተፈጸመ እና የተረጋገጠ እውነታ እያለ እንዴት እንዲህ ቢሆን እንዲህ አይሻልም ነበር እያልን ወደ መላምት እንሄዳለን?
    ሃሳብ ይሰጥበትና እንቀጥላለን።

    ReplyDelete
  8. Why do you think people are asking this question???? because there is no convincing answer!
    yesew lij netsa fekadun tetekimo wode mengiste semayat endemayigeba eyawokew lemin netsa fekadin setew? new yene tiyake. The best and very convincing answer as I mentioned earlier is , it is beyond human knowledge. I wish you can accept this. I know the way you argue since long time ago.I literally believe what you have said but not a convincing answer.

    ReplyDelete
  9. ሠላም።
    ውይይቱን ስለቀጠልክ አመሰግናለሁ። ሰዎች ይህን ጥያቄ የሚጠይቁት አጥጋቢ መልስ ስላልተገኘለት ነው ላልከው ለተወሰኑት እንደዚያ ሊሆን ይችላል፤ ለሁሉም እንደዚያ ነው ብለን መደምደም ግን ያስቸግራል።
    የሰው ልጅ ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደማይገባ እያወቀው ለምን ነጻ ፈቃድን ሰጠው? ነው ያልከኝ። እያወቀው ስትል እግዚአብሔርን ማለትህ ነው። ባልሳሳት። በመጀመሪያ ደረጃ እግዚአብሔር ያወቀው እንደዚያ መሆኑን እንዴት እርግጠኛ ሆነህ ልትናገር ቻልክ?
    ስማ ወንድሜ የምንናገረውን ነገር ከቃሉ እና ከተፈጸሙ እውነታዎች አንጻር መፈተሽ አለብን። አንድን ነገር ሕሊናችን ስላመነበት ብቻ እንዲሁ በራሳችን ሃሳብ መመራት ያለብን ይመስልሃል? ለመሆኑ የሰው ልጅ ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደማይገባ በምን ታወቀ? ማስረጃ አምጣ። ይሄውልህ ማስረጃ ከሌለህ ወይ ሌላው ሁሉ ተሳስቷል፣ ወይ አንተ ተሳስተሃል፤ አንተ ትክክል እንደሆንክ ለራስህ ቢሰማህም እንኳ።
    መቼም ሁለት ተቃራኒ የሆነ እውነት ሊኖር አይችልም። ሰው በነጻ ፈቃዱ መንግሥተ ሰማያት መግባት ይችላል፣ ወይ አይችልም። ከሁለት አንዱ።
    ግን የታወቀውና የታየው እውነታ ሰዎች ነጻ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው በእርሱ አምነው ሲድኑ ነው፡፡ በቀኝ የተሰቀለውን ወንበዴ አስታውስ። ጌታን እና መንግሥቱን አምኖ አስበኝ በማለቱ ወደ ገነት ገባ። «እንደማይገባ እያወቀው» ባልከው ባንተ ሃሳብ መሠረት ይሄ ሰው ወይ ነጻ ፈቃድ አልነበረውም፤ ወይ መንግሥተ-ሰማያት አልገባም፤ ወይስ አሁን እኛ ላይ ያለው ነጻ ፈቃድ መንግሥተ ሰማያት የማያስገባ ሌላ ልዩ ነጻ ፈቃድ (እገዳ ነገር) ነው እንበል?
    ነጻ ፈቃድን ከመጥፋት ጋር ብቻ ለምን ታያይዘዋለህ? ከመዳን ጋርስ? ነጻ ፈቃድ ማለት ምርጫ አይደለምን? በነጻነትህ በራስህ ምርጫ መጥፋትን ወይም መዳንን አሁን ለመምረጥ። የመጥፋትን አማራጭ ለማጥፋት (በቀላሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት) ነጻ ፈቃድ መኖር የለበትም ካልን ሰው መሆናችን ይቀርና ቀደም ብለን እንዳልነው እንስሳ/ዕቃ እንሆናለን። ሳንወድ እና ሳንፈልግ የምንሄድ። ይሄ ደግሞ ያልሆነ እና የማይሆን ነገር ነው።
    ላንተ መልካም መስሎ እንደታየህ የጥያቄው አጥጋቢ መልስ ከሰዎች አእምሮ በላይ ነው። ለእኔ ግን በበቂ ሁኔታ እውነታው መልስ ሆኖልኛል። ደግሞስ በመሠረተ-ሃሳብ ደረጃ የተቀበልከውን ለምን በተግባር መቀበል ከበደህ? መልሱ አሳማኝ ያልሆነው ምኑ ጋ ነው?
    ሃሳብ ከሰጠህበት እቀጥላለሁ።

    ReplyDelete
  10. "እያወቀው ስትል እግዚአብሔርን ማለትህ ነው። ባልሳሳት። በመጀመሪያ ደረጃ እግዚአብሔር ያወቀው እንደዚያ መሆኑን እንዴት እርግጠኛ ሆነህ ልትናገር ቻልክ?" I don't need to read the bible or books of all the the world to know the above mentioned question. anyone can intuitively know that the Creator Lord, God knows every thing. "ለመሆኑ የሰው ልጅ ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደማይገባ በምን ታወቀ? ማስረጃ አምጣ" same thing to above question. I don't have to read bible. Generally, I don't want to keep in such a dialogue. For sure you will not answer it. I hold what I believe, we can not say more about God. we are too much limited. We can not know more than what we are able to know. Ye Egziabher Neger Ayimeremerim. ewuneten new .... You need to accept this. It is beyond your capacity. in the first place, it is no need to ask such a question. " is God know this or not?" . this is improper to ask. God Knows everything!. think about those who haven't heard about bible (about 5 billion people in the world). Don't try to convince me mentioning here there. do on

    ReplyDelete
  11. ሠላም ወንድሜ
    መጽሐፍ ቅዱስን ሆነ ምንም መጽሐፍ ማንበብ ካልፈለክ፣ ውይይቱንም መቀጠል ካልፈለክ መብትህ ነው። እንዳልከው ያመንከውን ይዘህ መቀጠል ትችላለህ። ይህም ነጻ ፈቃድህ ነው።
    የእግዚአብሔርን ሁሉን አዋቂነት፣ እርሱን ለመመርመር የኛን ውስንነት እና የማይመረመር መሆኑን መቀበልህ አንድ ነገር ሆኖ ቃሉን (መጽሐፍ ቅዱስን)ማንበብ አልፈልግም ማለትህ ይገርማል። የሆነ ሆኖ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እስከሆነ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ካልፈለግህ አዚህ ላይ ማቆምህ መልካም ነው።
    ስለ ፭ ቢሊየኑ ሕዝብ ግን አትጨነቅ። እግዚአብሔር እንዴት እንደሚደርስላቸው እርሱ ያውቃል። ብዙ ሰዎችና አሠራሮች አሉት። ካዘንንላቸው እኔም አንተም እነጸልይላቸው፣ ከቻልንም በእውነት ቃል እንድረስላቸው።
    በተረፈ ስለውይይቱ አመሰግናለሁ። መልካሙን ሁሉ እመኝልሃለሁ።
    «Trust in the Lord with all thine heart; and lean not unto thine own understanding.»
    «በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ» ምሳ ፫፣፭።

    ReplyDelete

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment