Thursday, August 9, 2012

ሚዛናዊነት

Mizanawinet, sebket, READ IN PDF


የሕይወታችን መመሪያ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ከምንረዳቸው ታላላቅ ቁምነገሮች አንዱ ሚዛናዊነት ነው።በውስጡ ታሪካቸው ስለሰፈረላቸው ሰዎች መልካም ተግባር ሲነግረን ደካማ የሕይወት ክፍላቸውንም ያስነብበናል።
ለምሳሌ፡-
o   የአብርሃም የእምነት አባትነትና  ------በእግዚአብሔር ፊት የነበረበትን መንፈሳዊ ድክመት
o   የዳዊትን እንደልቤነትና ----- የዝሙት ውድቀት
o   የሙሴን ጠንካራ መሪነትና---- የእምነቱን መዛል  እናነባለን።
ከውድቀታቸው እንድንማር ብርታታቸውን አርአያ እንድናደርግ መንፈስ ቅዱስ ይህን አድርጓል።
በእኛ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም። ብናወራና ቢወራልን የምንወደው የበረታንበትን ነገር ብቻ ነው። ለዚህም ይመስላል ቆመው አይደለም ሞተው እንኳ ስለድክመታቸው እንዲወራ በማይፈልጉ ሰዎች ምክንያት በየቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሚነበበው የሕይወት ታሪክ የጥቂት እውነትና የብዙ ውሸት ድምር ውጤት የሚሆነው።

ክርስቲያን ግን የእውነትና የማመዛዘንን በረከት የተረዳ ነው።
በአዲስ ኪዳንም ከኃጢአት በቀር በክርስቶስ ሕይወት የምንመለከተው ይህንኑ ነው።
o   የብዙዎችን የልብ ስብራት ከአፉ በሚወጣው የሕይወት ቃል ጠግኗል።  ----- ባልተቀበሉትና ባላወቁት አፍም ተሰድቧል።
o   በምራቁ  አፈር ለውሶ በደረቅ ግንባር ላይ ዓይን ፈጥሯል። ----- ርኅራሄ በሚነበብበት ፊቱ ላይም ምራቅ ተተፍቶበታል።
o   ጎባጣ አቅንቷል። ----- ጀርባው እስኪላጥ ተገርፎአል
o   የሞቱትን ከመግነዝ ፈትቶ ከመቃብር አስነስቷል። ------ በአደባባይ ተሰቅሎ ስለሁላችንም ሞቷል።
ይህም (ሚዛናዊነት) በቃሉ ውስጥ ያለማዳለል ሰፍሮልናል።
   ብዙ ሕመምን ያስከተሉ ነገሮች ያላቸው መልካም ጎን ቢታወቅ ኖሮ ሀሴትን ይፈጥሩ ነበር። ሁሉም ነገር መልካምና መጥፎ ጎን ሲኖረው ቁም ነገሩ ያለው ግን ነገሮችን በመልካም ጎናቸው መጠቀሙ ላይ ነው። የአንድ ነገር ገጽታ እንደ ተመለከትንበት አቅጣጫ ይወሰናል። ስለዚህ ነገሮችን በሚዛናዊነት እንመልከታቸው።
                               « በሚጠሉኝ መሀል የሚወደኝን አገኘሁት» ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ- ገጽ
                                                                                           በዲ/ ኢዮብ ይመር
የአንድን ነገር ሙሉ ገጽታ የምናገኘው ከሁሉም አቅጣጫ (በሚዛናዊነት) ስንመለከተው ነው።
በሥነ-ሕንጻ ትምህርት አራት መሠረታዊ እይታዎች አሉ፡ - የፊትለፊት፡ የጎን፡ የላይና የውስጥ (Front, side, top and section views) ስለዚያ ሕንጻ የተሟላ ስእል (ምስል) ለማግኘት እነዚህን አራቱንም አቅጣጫዎች  በሙሉ ማየትና መረዳት ያስፈልጋል።
ተፈጥሮአችን ራሱ ሚዛናዊ እንድንሆን ያስተምረናል። ሁላችንም በተቃራኒ  አቅጣጫ የተቀመጡ ሁለት ጆሮዎች አሉን። አእምሮአችን (ሕሊና) እና አንደበታችን (አፍ) ግን አንድ ነው። ስለአንድ ጉዳይ ተቃራኒ የሆኑ ብዙ ነገሮችን ልንሰማ እንችላለን።
 ስለአንድ ነገር በአንደበታችን ከመናገራችን በፊት ነገሮችን በማስተዋል አመዛዝነን ከግራ ከቀኝ መርምረን ቢሆን አድማጭን ከሚያቆስል ንግግር እንጠበቃለን፡ ራሳችንንም ከፍርድ እንጠብቃለን።
በስፍራም፡ በአቅጣጫም  የማይወሰነው እግዚአብሔር  ከላይ ሆኖ ሁሉን ፍጹም በሆነ ሚዛናዊነት ይመለከታል። እኛ በየተመለከትንበት አቅጣጫ ፍርድን ብናዛባ፡ ሁሉም በእርሱ ፊት ግልጽ ነውና በፍትሐዊነቱ ፍርድን ያደላድላል።
ስለዚህ በምንሰማቸው ብዙ ነገሮች ሚዛናዊነት ይኑረን።  ሳናመዛዝን ለመናገርም አንቸኩል። ሁላችንም ሁሉም በእግዚአብሔር ፊት በግልጽ የሚታይ ነውና።
« እግዚአብሔር በሰማይ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን። በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኩል፡ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን።» ምሳ ፭፡፪።

3 comments:

  1. እውነት ነው ትንቢት ተናጋሪዎችም እኮ ደግ ደጉን ብቻ እየነገሩን ድካማችንን ማየታ አልቻልንም ንስሀ የለ ሁልግዜ ሃሌሉያ ብቻ

    ReplyDelete
  2. Esmamalehu, tebareku!!!!!!!!!!

    ReplyDelete
  3. Slakafelachugn adis neger betam des blognal

    ReplyDelete

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment