Wednesday, October 24, 2018

መጽሐፍ ቅዱሳዊ የመዳን አስተምህሮ


 ·        ሁሉም ሰው ኃጢአተኛ ነው።
o   ሁሉም በክርስቶስ ከማመኑ በፊት ኃጢአተኛ ነው
ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ ሮሜ ፫፣ ፳፫
- ከዚህ ኃጢአት /እና ሞት/ መዳን አለብን፤ መድኃኒቱም ኢየሱስ ነው፤
እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።  ማቴ ፩፣ ፳፩

o   በክርስቶስ ካመንን በኋላም እንኳ ኃጢአት ይኖርብናል - ባልዳነ ሥጋ ባልዳነች ዓለም ስለምንኖር
ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።
ዮሐ ፩፣
- ከዚህ ኃጢአት መንጻት አለብን፤ /ከዳንን በኋላ በየጊዜው ስለምንቆሽሽ/
የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።  ዮሐ ፩፣

·        ሁሉም የሚድነው በክርስቶስ በማመን ብቻ ነው።
በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤  ዮሐ ፫፣ ፴፮
·        ሌላ መድኃኒት የለም
መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።  የሐዋ ፬፣ ፲፪
·        አምነን መዳናችንን የምረጋግጠው አሁን ነው።
እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። ሮሜ ፰፣
·        ካላመንንም ፍርዱ አሁን ነው።
በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።። ሮሜ ፰፣

Wednesday, October 4, 2017

እግዚአብሔርን ማወቅ - ክፍል ፲፪


የእግዚአብሔር ሥራ


ለሚጠፋ መብል አትሥሩ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። እንግዲህ። የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ? አሉት። ኢየሱስ መልሶ፦ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው።    ዮሐ 6፣ 27 – 29

-      ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕዝቡ እንጀራና አሳ አበርክቶ ስለሰጣቸው - ለዚያ ሲሉ ነበር የተከተሉት። ለዚህ መልስ ሲሰጣቸው - ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፡፡ የምትከተሉኝ ለምን ዓላማ ነው?

እንደ ክርስቲያን /የክርስቶስ ተከታዮች/ በዚች ምድር የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው? ብንል መልሱ የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ነው።

-      እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታል፡- ወልድ የአብ ልጅ ነው። አብን መስሎ፣ አብን አክሎ የተገኘ፣ - ማኅተም፡- ሲደረግ ቅርጹ በወረቀቱ ላይ በትክክል ያርፋል። የአብን ማንነት በሥጋ /በሰው/ ታትሞ ያየነው በክርስቶስ ነው። - ወልድ ሰው ሲሆን አብ አትሞታል። የምወደው ልጄ ይህ ነው ብሎ ማረጋገጫ /ማኅተም/ አድርጎበታል።

-      ስለዚህ በክርስቶስ የሆነውን ማንኛውም መንፈሳዊ ሥራ እግዚአብሔር ከእኔ ነው ብሎ እውቅና /ማረጋገጫ / ይሰጠዋል- ማለት ነው።

Saturday, September 16, 2017

እግዚአብሔርን ማወቅ - ክፍል ፲፩


(የእግዚአብሔር መልክ - ቀጣይ)
የእግዚአብሔር መልክ መታየት - ለውስን ፍጡር - ፊት ለፊት

በብሉይ ኪዳን - ለሙሴ

እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፥ በምሳሌ አይደለም የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ስለ ምን አልፈራችሁም? አለ።     ዘኁ ፲፪፡ ፰

ሙሴ ክብርህን አሳየኝ ባለው ጊዜ፡-

እግዚአብሔርም አለ፦ እነሆ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፥ በዓለቱም ላይ ትቆማለህ

ክብሬም ባለፈ ጊዜ በሰንጣቃው ዓለት አኖርሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ

እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፥ ጀርባዬንም ታያለህ ፊቴ ግን አይታይም።    ዘጸ ፴፫፣ ፲፰ - ፳፫፡

-      በኋላ ከሲና ተራራ ሲወርድ ፊቱ አንጸባረቀ፡- ጨርቅ ሸፈነው።

አሮንና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ሙሴን ባዩ ጊዜ፥ እነሆ የፊቱ ቁርበት አንጸባረቀ ወደ እርሱም ይቀርቡ ዘንድ ፈሩ።  ዘጸ ፴፬፣ ፳፱ - ፴፭

-      በትክክል ከእግዚአብሔር ጋር በመንፈስ ከተገናኘን የእግዚአብሔር መልክ ይሳልብናል። እርሱን እናንጸባርቃለን። ለእኛ ላይታወቀን ይችላል። የሚያዩን ግን ያውቃሉ።

በአዲስ ኪዳን፡- ፫ ቱ ሐዋርያት- በደብረ ታቦር

በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ።

እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ።….  ማቴ ፲፯፣ ፩ - ፰

-      በእግዚአብሔር መልክ - በእርሱ ፊት መኖርን የመሰለ መልካም ነገር የለም።

ለአሕዛብ ሐዋርያ ሳውል - ጳውሎስ

ሲሄድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ ድንገት በእርሱ ዙሪያ ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ፤

በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ። ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለውን ድምፅ ሰማ።… የሐዋ ፱፣ ፩ - ፰

-      ጌታን ፊት ለፊት በብርሃን መልክ አየው። በቀን በቀትር ስለሆነ ያየው ጌታ ከፀሐይ ብርሃን ይበልጥ አብርቷል ማለት ነው። /የሐዋ ፳፪፣፮/

Sunday, September 3, 2017

እግዚአብሔርን ማወቅ - ክፍል ፲


፬. የእግዚአብሔር መልክ


እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።  ዘፍ ፩፣ ፳፯

መልክ፡- ሲባል የማይታየውን የሰውን ረቂቅ ማንነት /መንፈስ/ ለማመልከት ነው።

፩. የእግዚአብሔር መልክ በሰው፡ በ፫ መልክ ይታያል፤

፩. በነፍሱ፡  እግዚአብሔር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ ሲፈጥረው ማንኛችንን ነው የሚመስለው? የሰው መልክ የተለያየ ነው። ጥቁሮች፣ ነጮች፣ ቀዮች፣….

ü በሰው ላይ ያረፈው መልክ በሥጋ ሳይሆን በነፍስ። ሥጋ ከአፈር ነው። ነፍስ ከእግዚአብሔር እስትንፋስ ናት። የእርሱን ነገሮች በተመጠነ ሁኔታ ወደ እኛ አሳርፏል።

o   ሰው ሥጋ ብቻ ሳይሆን ረቂቅ ማንነት አለው። መንፈሱ- በነፍሱ ያገኛት ናት።

o   የነፍስ ባሕርያት፡፫ - አሳቢነት፣ ተናጋሪነት፣ ዘላለማዊነት፡- ይህም አብ፣ ወልድ፣ መንፈስቅዱስ፣ አንጻር የሚታዩ ናቸው፤  እግዚአብሔር ሦስትነት አለው፤ ሥላሴ። ሥላሴ በአብ ልብነት ያስባሉ፤ በወልድ ቃልነት ይናገራሉ፤ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት ይኖራሉ፤

o    ስለዚህ ነፍስ፡- ከእንስሳት የምንለይበት፣ እግዚአብሔርን የምንመስልበት ነው።

፪. በኑሮ/በአኗኗሩ፡  ሰው ዘላለማዊ ሆኖ ሲኖር - ፫ መገለጫዎች አሉት።

ü ፩. ዕውቀት፡- ከራሱ ጋር ያለውን ግንኙነት ያሳያል፣ በዚህ ውስጥ፡- የመምረጥ የመወሰን፣ የማድረግ/መሥራት/ ነጻነት አለን፤…ባወቅነው/በገባን ጉዳይ ላይ ምላሽ እንሰጣለን ይህም ስሜት ይባላል፤ በመጨረሻ ባወቅነው ነገር ተንተርሰን በጉዳዩ ላይ ፈቃዳችን እንገልጻለን። ይህም ውሳኔ ይባላል።

ü ፪. ቅድስና፡- ከሌላው ጋር ያለውን ግንኙነት ያሳያል።- በዚህ ውስጥ፣ ያለኃጢአት / ያለበደል/ በሰላም መኖር፣ ኅብረት፣ሌላውን የመፈለግ /የመርዳት/ ነገሮች ይገለጻሉ።

ü ፫. ጽድቅ፡- ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት ያሳያል፡- በዚህ ውስጥ ያለኃጢአት ከአምላክ ጋር የመኖር፣ አምክን የመፈለግ፣ የመታመን /ተስፋ የማድረግ ሁኔታዎች አሉ።

Wednesday, August 16, 2017

እግዚአብሔርን ማወቅ - ክፍል ፱

/የእግዚአብሔር ስም - ቀጣይ/

Ø የእግዚአብሔር ወዳጆች እግዚአብሔር ካደረገላቸው ነገር ጋር በማያያዝ ለልጆቻቸው ስም ያወጡ ነበር።

ምናሴ - ማስረሻ፡- አባቱ ዮሴፍ መከራየን የአባቴን ቤት አስረሳኝ ሲል። ዘፍ ፵፩፣፶፩

ሳሙኤል - እግዚአብሔር ሰማ - መካኒቱ ሐና ጸሎቷን ስለሰማ ልጅ ስለሰጣት፡      ፩ ሳሙ ፩፣ ፳

o   ዛሬ የእኛ ስም አወጣጥ ምን ይመስላል? - የእግዚአብሔር ወገን መሆናችንን የሚያሳይ ነው?.. ስሞቻችንን ብንፈትሻቸው፡

-      ቦግ አለ፣ ዱብ አለ።  - ኩራባቸው፣ ሰጥአርጋቸው፣

Ø ቦታዎችንም ከእግዚአብሔር ጋር በማያያዝ ይሰይሙ ነበር።

o   አጋር ከሣራ ተሰዳ ስትወጣ እግዚአብሔር አገኛት - በመልአኩ፡
እርስዋም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ኤልሮኢ ብላ ጠራች የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን? ብላለችና። ስለዚህም የዚያ ጕድጓድ ስም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ ተጠራ፡  ዘፍ ፲፮፣ ፲፫ - ፲፬

Ø እግዚአብሔር የወዳጆቹን ስም ይለውጣል።

- አብራም /ታላቅ አባት/ - አብርሃም /የብዙዎች አባት/…

- ያዕቆብ /አሰናካይ -ተረከዝ የሚይዝ (ሲወለዱ የኤሳውን እግር ይዞ ስለነበር ወላጆቹ ያወጡለት

እግዚአብሔር ግን - እስራኤል - አለው፡- እግዚአብሔር ያሸንፋል ማለት ነው።
ወዳጆቹ ወደፊት የሚሆኑትን በማየት ሕይወታቸውን ለመለወጥ ስማቸውን ከመለወጥ ይጀምራል።
እኛም ዛሬ በወል ስም -በክርስቶስ - ክርስቲያን የተባልነው- ከስማችን ጀምሮ ሕይወታችን እንዲለወጥ የክርስቶስን ፈለግ በመከተል እርሱን ወደ መምሰል እንድናድግ ነው።

የእግዚአብሔር ስም ለእኛ ምን ያስተምረናል?
Ø ይመልስልናል፡-  በስማችን ስንጠራ - አቤት- ብለን መልስ እንሰጣለን። በስም መጥራት የግንኙነቶች መጀመሪያ /ትውውቅ/ ፣ የሥራ መጀመሪያ ነው። ከጠራን በኋላ ወደ ጉዳያችን እንገባለን።

o   እግዚአብሔር ስም ያለው መሆኑ እንድንጠራው ያስችለናል። እርሱም  እንደሚመልስልን ማረጋገጫ ነው።

o   ጆሮ እያለው በስሙ ተጠርቶ የማይመልስ የለም። - ጆሮን የፈጠረ አምላክ ይሰማል

Ø ግንኙነትን ያመለክታል አጠራራችን ግንኙነታችንን ያመለክታል። ስሞቹ የትኛውን እንደምንጠቀም የሚያሳየው ቅርበታችንን ነው፤

o   ለምሳሌ እኔ ስጠራ፡-

§  አቶ አብርሃም / ጋሼ አብርሃም ብሎ የሚጠራኝ - የሥራ ግንኙነትን ያሳያል፤ በክብር በሩቁ የምጠራበት ነው ፡፡

§  አብርሽ - የወዳጅ መጥሪያ ነው- ቅርበትን ያሳያል፤

§  ባባ - የአባትና የልጅ..የበለጠ ቅርበትን ያሳያል።

o   እግዚአብሔርን ስንጠራው የትኛውን እንጠቀማለን። እግዚአብሔር  የሚለው በተፈጥሮ ሁሉም እርሱን የሚጠራበት - የአክብሮት -የጌትነቱ-የፈጣሪነቱ ነው። ለእኛ ግን ከዚያም በላይ ነው። በሩቁ የምናከብረው ብቻ አይደለም። ቅርብ ነው- አባታችን ስለሆነ፤

ጌታ ስትጸልዩ፡- አባታችን ሆይ - በሉ  አለ

አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና።   ሮሜ ፰፣ ፲፭።

አባ፣ አባት፡- የልጅነት - የቅርበት ስለሆነ- በዚህ እንድንጠራው ይፈልጋል።

Ø በከንቱ አይጠራም፡ -  ስም መጠሪያ ቢሆንም በትንሹ በትልቁ መጥራት የለብንም። ከ፲ቱ ትዕዛዛት አንዱ ሆኖ መሰጠቱ ይገርማል። ለስሙ ምን ያህል እንደሚጠነቀቅ/ እኛም እንድንጠነቀቅ በቋሚነት በ፲ቱ ትእዛዛት ተካተተ።

የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና።   ዘጸ ፳፣ ፯ፀ ስሙን በከንቱ መጥራት -ማለት

o   ያለቦታው መጥራት - እግዚአብሔርን ለጥፋት ተባባሪ ማድረግ

o   ስሙን ማሰደብ፡- የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን በማይሆን ቦታ/ በኃጢአት/ ብንገኝ የሚሰደበው እግዚአብሔር ነው። 

Monday, July 31, 2017

እግዚአብሔርን ማወቅ ክፍል - ፰


 የእግዚአብሔር ስም


ሙሴም እግዚአብሔርን፦ እነሆ፥ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ። የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ ባልሁም ጊዜ። ስሙስ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ፥ ምን እላቸዋለሁ? አለው።

እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «ያለና የሚኖር» እኔ ነኝ አለው እንዲህ ለእስራኤል ልጆች። «ያለና የሚኖር» ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ አለው። … ዘጸ ፫፣ ፲፫ - ፲፬

እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ወረደ፥ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፥ የእግዚአብሔርንም ስም አወጀ።

እግዚአብሔርም በፊቱ አልፎ። እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥

እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው ሲል አወጀ። .. ዘጸ ፴፬፣ ፭-፯

ስም፡- ምንድን ነው?

 - መጠሪያ ነው።በምክንያት የሚወጣ።  ለልጃችን ስም ለማውጣት ብዙ እናስባለን። የተለየ ቆንጆ ስም እንዲሆን እንፈልጋለን።

- ራስን መግለጫ /ማስተዋወቂያ/ ነው። ሰዎች ሲተዋወቁ መጀመሪያ የሚለዋወጡት ስም ነው። እገሌ እባላለሁ።…

·        አዳም በመጀመሪያ ለእንስሳት - በኋላም ለሚስቱ ስም አወጣ። - ባለቤትነትን ያሳያል።

በመጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ስም በራሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲተዋወቅ ፡- ለሙሴ- ማን ነው? ሲሉኝ…ማን ልበላቸው ባለው ጊዜ እንዲህ ብሎታል፡-

Ø ያለና የሚኖር  በእንግሊዝኛው - I AM that I AM’- ይላል። በቀጥታ እንዳለ ብንተረጉመው፡- « እኔ እኔው ነኝ፡- ማለት ነው።

o   ለእግዚአብሔር ማንም ስም አላወጣለትም፤ ራሱን ራሱ ገለጸ፣ ስሙን ተናገረ።

o   የሚገልጸው ነገር ስለሌለ - እኔ እኔው ነኝ -  አለ።

o   በራሱ ሕልው መሆኑን - በራሴ ያለሁና በራሴ የምኖር - አለ።

Ø በአማርኛ እግዚአብሔር  ብለን የሰጠነው ስም የግዕዝ ቃል ነው። አባቶች በሁለት መልክ ይተረጉሙታል፡

፩ኛ.  እግዚአ - ጌታ፣ ብሔር - ሃገር/ ዓለም/ - እግዚአ ብሔር፡- የዓለም ጌታ የሚል ነው። የዓለማት ሁሉ አስገኝ ባለቤት መሆኑን ያሳያል።

ይህ ማንነቱን በሙሉ አይገልጸውም። ያንሳል። እርሱ ከጌታም በላይ ነውና።

  ፪ኛ. እግዚእ- ወልድ፣ አብ - አብ፣ ሔር - መንፈስ ቅዱስ - ሥላሴነቱን ያሳያል።

ይህ ስሙም ሦስትነቱን መግለጹ እንጂ መላ ማንነቱን ሊገልጽ አይችልም።

Friday, July 14, 2017

እግዚአብሔርን ማወቅ - ክፍል ፯


. እግዚአብሔርን ፍለጋ - ቀጣይ፡-  
ምኑን ነው የምንፈልገው?፡-  

ባለፈው ክፍል  - እግዚአብሔርን ፍለጋ በሚል - ስለእግዚአብሔር መኖር በተፈጥሮ፣ በሕሊና፣ በመሳሰሉት ማረጋገጥ እንደሚቻል አይተናል።

 በአሁኑ ጊዜ የፈጣሪን /የእግዚአብሔርን መኖር የሚጠራጠር ብዙም ላይኖር ይችላል፤ ወይም በአሁኑ ጊዜ ለኛ ይህ ብዙም አሳሳቢ ጥያቄ አይደለም።

ከላይ ከተጠቀሱት በአንዱ ወይም በሌላ በሆነ መንገድ - የእግዚአብሐየርን መኖር አረጋገጥን - እግዚአብሔርን አገኘነው።  ካገኘነው በኋላ ምኑን ነው ማየት የምንፈልገው? ስንል ዳዊት እንዲህ ይለናል፡-

ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ።  መዝ ፻፬/፻፭፣ ፬

-      የእግዚአብሔር ሕልውና /መኖሩ/ የሚረጋገጠው አንድ ጊዜ ነው። ከተገኘ - አለ። አይጠፋም።

ከዚያ በኋላ ግን ሁልጊዜ መፈለግ ያለብን - ፊቱን - ነው።

-      በምናያቸው ፍጥረታት የእግዚአብሔርን አስደቂ ኃያል እጅ  እናያለን። ቀጥሎ ግን ሁልጊዜ ፊቱን ማየት አለብን።

ፊት ምንድን ነው? -የማንነት መለያ ነው። ሁላችንም የምንለየው በፊታችን ነው። መታወቂያ ላይ የሚደረገው ፎቶ - ጉርድ ፎቶ - የሚያሳየው ፊታችንን ነው።

-      አንድን ሰው አየሁት ለማለት - ፊቱን - ማየት ግድ ነው።

-      ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ሕዝቡን ነጻ አውጥቶ ሲመራ፣ በተአምራት ብዙ ዘመን ከኖረ በኋላ፡- እግዚአብሔርን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡-

o   እርሱም፦ እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ።….

-      እግዚአብሔርም -

o   …ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም......ፊቴ ግን አይታይም»   አለ      ዘጸ ፴፫፡ ፲፯ - ፳፫።

-      ፊቱን ማየት የማይቻል ከሆነ -ፊቱ የማይታይ ከሆነ -  ለምን ፊቱን ፈልጉ ተባለ? -             ማየት የማይቻለው በዚህ በሥጋ ዓይን ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ነውና።

-      በመንፈስ ግን ከእኛ ጋራ ሲሆን፣ ሲሠራ፣ ሕይወታችን ሲጠብቅ… እናየዋለን።

ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።  (የሐዋ ፲፯፣ ፳፮)

-      መምህራን እንደሚያስተምሩት በርግጥ የሙሴ ጥያቄ ተመልሷል፤ ነገር ግን የተመለሰው ከ1400 ዓመት በኋላ- በኢየሱስ ክርስቶስ - በደብረ ታቦር ነው።

o   ሙሴ በጥየቄው መሰረት በዓይነ-ሥጋ በአካል እግዚአብሔርን ያየው - በኢየሱስ ክርስቶስ - ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነው አግዚአብሔር ነውና።
በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ማቴ ፲፯፣ ፪ - ፫
ዛሬም እኛ እግዚአብሔርን በመንፈስ ዓይን የምናየው - በኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ስለዚህ፡-