Monday, July 31, 2017

እግዚአብሔርን ማወቅ ክፍል - ፰


 የእግዚአብሔር ስም


ሙሴም እግዚአብሔርን፦ እነሆ፥ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ። የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ ባልሁም ጊዜ። ስሙስ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ፥ ምን እላቸዋለሁ? አለው።

እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «ያለና የሚኖር» እኔ ነኝ አለው እንዲህ ለእስራኤል ልጆች። «ያለና የሚኖር» ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ አለው። … ዘጸ ፫፣ ፲፫ - ፲፬

እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ወረደ፥ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፥ የእግዚአብሔርንም ስም አወጀ።

እግዚአብሔርም በፊቱ አልፎ። እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥

እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው ሲል አወጀ። .. ዘጸ ፴፬፣ ፭-፯

ስም፡- ምንድን ነው?

 - መጠሪያ ነው።በምክንያት የሚወጣ።  ለልጃችን ስም ለማውጣት ብዙ እናስባለን። የተለየ ቆንጆ ስም እንዲሆን እንፈልጋለን።

- ራስን መግለጫ /ማስተዋወቂያ/ ነው። ሰዎች ሲተዋወቁ መጀመሪያ የሚለዋወጡት ስም ነው። እገሌ እባላለሁ።…

·        አዳም በመጀመሪያ ለእንስሳት - በኋላም ለሚስቱ ስም አወጣ። - ባለቤትነትን ያሳያል።

በመጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ስም በራሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲተዋወቅ ፡- ለሙሴ- ማን ነው? ሲሉኝ…ማን ልበላቸው ባለው ጊዜ እንዲህ ብሎታል፡-

Ø ያለና የሚኖር  በእንግሊዝኛው - I AM that I AM’- ይላል። በቀጥታ እንዳለ ብንተረጉመው፡- « እኔ እኔው ነኝ፡- ማለት ነው።

o   ለእግዚአብሔር ማንም ስም አላወጣለትም፤ ራሱን ራሱ ገለጸ፣ ስሙን ተናገረ።

o   የሚገልጸው ነገር ስለሌለ - እኔ እኔው ነኝ -  አለ።

o   በራሱ ሕልው መሆኑን - በራሴ ያለሁና በራሴ የምኖር - አለ።

Ø በአማርኛ እግዚአብሔር  ብለን የሰጠነው ስም የግዕዝ ቃል ነው። አባቶች በሁለት መልክ ይተረጉሙታል፡

፩ኛ.  እግዚአ - ጌታ፣ ብሔር - ሃገር/ ዓለም/ - እግዚአ ብሔር፡- የዓለም ጌታ የሚል ነው። የዓለማት ሁሉ አስገኝ ባለቤት መሆኑን ያሳያል።

ይህ ማንነቱን በሙሉ አይገልጸውም። ያንሳል። እርሱ ከጌታም በላይ ነውና።

  ፪ኛ. እግዚእ- ወልድ፣ አብ - አብ፣ ሔር - መንፈስ ቅዱስ - ሥላሴነቱን ያሳያል።

ይህ ስሙም ሦስትነቱን መግለጹ እንጂ መላ ማንነቱን ሊገልጽ አይችልም።


Ø ስለዚህ ለሙሴ ራሱ እግዚአብሔር የተናገረው ስሙ የተሻለ ገላጭ ነው። እኔ እኔው ነኝ። የሚገልጸኝ፣ የሚመስለኝ የለም ሲል ነው።

o   ለአብርሃም ዘፍ ፲፯፣ ፩ - እኔ ኤልሻዳይ ነኝ፡ ሲለው ከባሕርያቱ አንዱን ነው የሚገልጸው - ሁሉን ቻይነቱን። 

ስለእርሱ ሁሉንም እኔ እንዲህ ነኝ በማለት መዘርዘር ስለማንችል፡- እኔ እኔው ነኝ፤ አለ።

Ø በኋላ ለሙሴ በድጋሜ ራሱ ያወጀው ስም፡-- የእግዚአብሔርንም ስም አወጀ። - አስር መግለጫዎችን የያዘ ነው። በየቁጥሮቹ እንያቸው፡-

o   ፩. እግዚአብሔር እግዚአብሔር - ሁለት ጊዜ - ለአጽንኦት፡  በእንግሊዝኛው ጌታ፣ ጌታ እግዚአብሔር ይላል። - የዓለም ጌታ፤ ባለቤትነቱን ያሳያል። ቀዳማዊ ነገር ይህ ነው። የእግዚአብሔር ስም- የፍጥረት ሁሉ ባለቤት /ጌታ/ እርሱ መሆኑን - በቅድሚያ ያውጃል።  ጌታ ያለን መሆናችንን ማወቅ፡ -  የማን መሆናችንን ማወቅ ማለት ነው።

-የማን መሆናችንን ስናውቅ - ማንነታችንን እናውቃለን። ከዚያም ምን ማድረግ እንዳለብን እና እንደሌለብን እናውቃለን።

o   . መሐሪ፡- ቸር ነውና ምሕረቱ ለዘላለም ነውና  እንደተባለ።

በኃጢአት ለወደቀው ሰው ቅድሚያ የሚያስፈልገው የእግዚአብሔር ነገር - ምሕረቱ ነው።

ሰው ሲፈጠር የማን መሆኑን /ጌታ እንዳለው/ ካወቀ በኋላ በኃጢአት ስለወደቀ ምሕረቱን ይሻል። - ስለዚህ እግዚአብሔር መሐሪ ተባለ።

§  ስለእግዚአብሔር ያለን አመለካከት የሚጨክን እንዳይመስለን፡ -  መሐሪ ነው

§  እኛም ለሌሎች የሚጨክን ልብ እንዳይኖረን - ምሕረት እናድርግ።

o   ፫. ሞገስ ያለው፡-  ሞገስ ምን ማለት ነው? -- መልካም አመለካከት ያለው፤

§  ፩. እግዚአብሔር ለሰዎች ያለው፡-

-      ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ።  ዘፍ ፮፣፰

መልካም ተቀባይነትን አገኘ፡፡ ለኖኅ ሞገስን የሰጠው እግዚአብሔር ነው። - ሞገስ ያለው ስለሆነ፡፡

o   ፬. ታገሽ፡- ትዕግስቱን

o   ፭. ቸርነቱ ብዙ የሆነ፡- ባለጸጋ፡- የሰጠ - - ተፈጥሮን፣ ሕይወትን የሰጠ።

o   ፮. እውነቱ /ታማኝነቱ የበዛ፡- ማንም እውነትነቱን የማያረጋግጥለት፣ በራሱ እውነት የሆነ፡- ታማኝነቱን ለመግለጽ ነው።

o   ፯. እስከ ሺ ትውልድ ቸርነትን የሚጠብቅ፡-  ሺ ሲባል በትክክል እየተቆጠረ አንድ ሺ ለማለት አይደለም። ቁጥሮች በውሳኔ እና ያለውሳኔ ይነገራሉ።

ያለውሳኔ ሲነገሩ ቁጥርን ሳይሆን ታላቅነትን፣ ፍጹምነትን፣ ዘላቂነትን ያሳያሉ፡፡

ለምሳሌ፡- «አስር ጊዜ አትጨቅጭቀኝ፤ ሺ ጊዜ ብትለፋ አይሆንም።… » ሲባል ቁጥሮችን አይደለም። ፈጽሞ እንደማይሆን ለማሳየት ነው።

እዚህም ላይ ሺ ትውልድ ሲል ያለውሳኔ የተነገረ በመሆኑ እንደማያልቅ - ቸርነቱ ብዙ እንደሆነ ያሳያል።

o   ፰. ይቅር ባይ፡- አበሳን፣ መተላለፍን፡ ኃጢአትን… ይቅር የሚል።

o   ፱. በደለኛውን ከቶ የማያነጻ፡- በደለኛን ይቅር አይልም ማለት ነው? አይደለም። በእንግሊዝኛው that will by no means clear the guilty - ይላል። ጥፋተኛውን ነጻ ነህ / ንፁህ ነህ / ሊለው አይችልም። ያጠፋን ሳይቀጣ እንዳላጠፋ ዝም ብሎ አያልፍም። - ወይ በንስሐ ይቅር ይለዋል፤ ወይ ያጠፋዋል - ይበቀለዋል።

o   ፲. የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ፡- በመጨረሻ የታወጀው የስሙ መገለጫ።

የአባቶቹን ጥፋት / ኃጢአት/ እያየ ትውልዱ ንስሀ ካልገባ በዚያው ኃጢአት ይያዛል። ይጠየቃል። 

- በአባቶች ኃጢአት ልጆች፣ የልጅ ልጆች ይቀጣሉ። ለምን?

-እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ ያለው ጭካኔ ከባድ እንደሆነ - እስከትውልድ እንደሚቀጥል እንጂ ዘመን በረዘመ ቁጥር ሳይቀጣ የሚተው፡ የሚረሳ እንዳልሆነ ያሳያል።

-ልጆች ቅጣቱ ቢተርፋቸውምለ - ልጆች - እስከሆኑ ድረስ ንስሐ የመግባትና ምሕረት የማግኘት እድል አላቸው።

-እስራኤላውያን በበረሀ በእግዚአብሔር ላይ በማመጻቸው የተቀጡት /፵ ዓመት የተንከራተቱት/ ያጠፉት አዋቂዎቹ ብቻ አይደሉም። አብረው የተወለዱት ሕጻናትም ተንከራትተዋል።

-ልጆች፣ የልጅ ልጆች - እስከ ፫ና ፬ ትውልድ - ይህ በውሳኔ የተነገረ ስለሆነ ቁጥሩን የሚያሳይ ነው። አንድ ሰው በዕድሜ ባለጸጋ ሲሆን የልጅ ልጆቹን ማየት የሚችለው እስከ ፬ ትውልድ ነው። -- ሲበድል ንስሐ ካልገባ ዓይኑ እያየ ልጆቹ የልጅ ልጆቹ ይቀጣሉ፣ ማለት ነው። ንስሐ መግባት አለበት። እንጂ ጥፋትን /በደልን/ ከእግዚአብሔር ጋር በዘመን ርዝመት ማረሳሳት አይቻልም።

-ይህ ሲቀጥል - እኛ የምናጭደው የአባቶቻችንን በረከት/መርገም ሲሆን የእኛን በረከት/መርገም ልጆቻችን ያጫዳሉ የሚለውንም ያሳያል።

-- ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት - መልካም ከሆነ ውጤቱ፤ ክፉም ከሆነ ጦሱ እስከልጆቻችን እንደሚሆን አውቀን መጠንቀቅ አለብን።

Ø የእግዚአብሔር ስም በእግዚአብሔር ሲታወጅ ሙሴ የሰጠው ምላሽ - አምልኮ-ስግደት ነበር

ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተጐነበሰና ሰገደ፦  ዘጸ ፴፬፣ ፰

……………ይቀጥላል……………
ዲ/ን ኢንጅነር አብርሃም አብደላ
ሐምሌ ፳፬/ ፳፻፱ ዓ/ም - ጎንደር

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment