Friday, July 14, 2017

እግዚአብሔርን ማወቅ - ክፍል ፯


. እግዚአብሔርን ፍለጋ - ቀጣይ፡-  
ምኑን ነው የምንፈልገው?፡-  

ባለፈው ክፍል  - እግዚአብሔርን ፍለጋ በሚል - ስለእግዚአብሔር መኖር በተፈጥሮ፣ በሕሊና፣ በመሳሰሉት ማረጋገጥ እንደሚቻል አይተናል።

 በአሁኑ ጊዜ የፈጣሪን /የእግዚአብሔርን መኖር የሚጠራጠር ብዙም ላይኖር ይችላል፤ ወይም በአሁኑ ጊዜ ለኛ ይህ ብዙም አሳሳቢ ጥያቄ አይደለም።

ከላይ ከተጠቀሱት በአንዱ ወይም በሌላ በሆነ መንገድ - የእግዚአብሐየርን መኖር አረጋገጥን - እግዚአብሔርን አገኘነው።  ካገኘነው በኋላ ምኑን ነው ማየት የምንፈልገው? ስንል ዳዊት እንዲህ ይለናል፡-

ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ።  መዝ ፻፬/፻፭፣ ፬

-      የእግዚአብሔር ሕልውና /መኖሩ/ የሚረጋገጠው አንድ ጊዜ ነው። ከተገኘ - አለ። አይጠፋም።

ከዚያ በኋላ ግን ሁልጊዜ መፈለግ ያለብን - ፊቱን - ነው።

-      በምናያቸው ፍጥረታት የእግዚአብሔርን አስደቂ ኃያል እጅ  እናያለን። ቀጥሎ ግን ሁልጊዜ ፊቱን ማየት አለብን።

ፊት ምንድን ነው? -የማንነት መለያ ነው። ሁላችንም የምንለየው በፊታችን ነው። መታወቂያ ላይ የሚደረገው ፎቶ - ጉርድ ፎቶ - የሚያሳየው ፊታችንን ነው።

-      አንድን ሰው አየሁት ለማለት - ፊቱን - ማየት ግድ ነው።

-      ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ሕዝቡን ነጻ አውጥቶ ሲመራ፣ በተአምራት ብዙ ዘመን ከኖረ በኋላ፡- እግዚአብሔርን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡-

o   እርሱም፦ እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ።….

-      እግዚአብሔርም -

o   …ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም......ፊቴ ግን አይታይም»   አለ      ዘጸ ፴፫፡ ፲፯ - ፳፫።

-      ፊቱን ማየት የማይቻል ከሆነ -ፊቱ የማይታይ ከሆነ -  ለምን ፊቱን ፈልጉ ተባለ? -             ማየት የማይቻለው በዚህ በሥጋ ዓይን ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ነውና።

-      በመንፈስ ግን ከእኛ ጋራ ሲሆን፣ ሲሠራ፣ ሕይወታችን ሲጠብቅ… እናየዋለን።

ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።  (የሐዋ ፲፯፣ ፳፮)

-      መምህራን እንደሚያስተምሩት በርግጥ የሙሴ ጥያቄ ተመልሷል፤ ነገር ግን የተመለሰው ከ1400 ዓመት በኋላ- በኢየሱስ ክርስቶስ - በደብረ ታቦር ነው።

o   ሙሴ በጥየቄው መሰረት በዓይነ-ሥጋ በአካል እግዚአብሔርን ያየው - በኢየሱስ ክርስቶስ - ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነው አግዚአብሔር ነውና።
በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ማቴ ፲፯፣ ፪ - ፫
ዛሬም እኛ እግዚአብሔርን በመንፈስ ዓይን የምናየው - በኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ስለዚህ፡-


፭.  የፍለጋው ማብቂያ - ኢየሱስ ክርስቶስ

o   በተሰጠን አእምሮ በምናደርገው ምርምር በተፈጥሮ፣ በኅሊና.. ፈጣሪ እንዳለ እናውቃለን። ፍጥረታትን ሁሉ እግዚአብሔር እንደፈጠራቸው እንዳስገኛቸው እንደሚቆጣጠራቸው እንረዳለን።

o   እግዚአብሔርን ፍለጋ የምናደርገው ጥረት እግዚአብሔር እንዳለ እንድናውቅ እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር እንድንገናኝ አያደርገንም።

o   ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኘው በእኛ ፍለጋ ሳይሆን በእርሱ ፍለጋ ነው። እርሱ እኛን ስለፈለገን።  ስለዚህ የእኛ እግዚአብሔርን ፍለጋ የሚጠናቀቀው በራሱ በእግዚአብሔር ፍለጋ ነው።

-      የእግዚአብሔር ፍለጋ - ፍለጋው አያልቅም - እንደምንለው አይደለም። መድረሻ አለው።   የእግዚአብሔር ፍለጋ ማብቂያው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።


እኛ እርሱን ልንደርስበት ስለማንችል እርሱ እኛን ፈለገን። በሚገባን በምናውቀው ባሕርይ።  በሰው - ሰው ሆኖ ሊፈልገን መጣ።
የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና አለው።  ሉቃ ፲፱፣ ፲

መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።  ዮሐ ፩፣ ፲፰።

ተረከው - ማለት የቃል ትረካ አይደለም፤ በተግባር በኑሮ፣ በሕይወት፣ በሞት፡በትንሣኤ… ገለጠው ማለት ነው።

ክርስቶስን ስናገኝ / ክርስቶስ ሲያገኘን/ ያን ጊዜ እግዚአብሔርን አገኘነው - አወቅነው፡ ማለት ነው።

ማጠቃለያ፡- እግዚአብሔር አንዲህ አለ / ብሎ ተናገረ፣ ከማለታችን በፊት እግዚአብሔር አለ /መኖሩን/ እንበል።

-      እግዚአብሔር አለ/የለም በሚል ክርክር አንዱ ፈላስፋ የቆሎ ተማሪን ሲጠይቀው፣ እነዲህ መለሰለት፡ «እግዚአብሔርን አለ ብለኽው ባይኖር ችግር የለውም፤ የለም ብለኽው ካለ ግን ወዮልህ።»

-      አንዳንድ ወገኖች - ከባድ ችግር ሲገጥማቸው ወይም ያልሆነ መጥፎ ነገር ሲያዩ «እግዚአብሔርማ የለም፤ በእውነት ቢኖር እንደዚህ አይሆንም ነበር፤ » ይላሉ።

-      እግዚአብሔር አንድን ነገር ለምን እንደሚያደርግ፣ እንዴት እንደሚሠራ ለእኛ ሁሉም ነገር ግልጽ ላይሆን ይችላል። ዝም ብለን በትዕግስት እንጠብቀው፤

እንደሚባለው አንዳንድ ነገሮች በጣም እንግዳ ይሆናሉ፤ ለምን እንዲህ ይሆናል አንበል፤ ቃሉ እንደሚል፡-

ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው።  ዘዳ ፳፱፣ ፳፱

-      ያለማቋረጥ ፀሐይን የሚያወጣት/የሚያገባት፣ ዝናቡን የሚያዘንብ፣ አዝመራውን የሚያበቅል፣ ለፍሬ የሚያደርስ፣ ሁሉን የሚመግበው ፣ የሚያስተዳድረው አምላክ - አለ።

-      እኛንም ወደዚች ምድር ያመጣን፣ የፈጠረን ነው እርሱ የሚያኖረን ። አንጨነቅ።

ሳለመድኃኔዓለም ምንም አንሆንም። አንፍራ።

-      በእውነት እግዚአብሔር አለ  ። ከሁሉም በላይ ትልቅ መጽናኛችን ነው።

o   መኖሩን ያመንነውን  - ፈልገን ያገኘነውን ወይም በትክክል ለመናገር ፈልጎን ያገኘንን / እንድናገኘው የተፈለገውን/ መተዋወቅ  ቀጣዩ ተገቢ ጉዳይ  ነው ። ስንተዋወቅ የምንለዋወጠው ስምን ነው? -- እገሌ እባላለሁ።- -

o   ስለዚህ ይህ ፈጣሪ ማን ይባላል?....

o   የእግዚአብሔር ስም.. ይቀጥላል

o   ይቆየን
ዲ/ን ኢንጅነር አብርሃም አብደላ
ሐምሌ ፯፣ ፳፻፱ ዓ/ም - ጎንደር

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment