Friday, January 27, 2012

ምሥጢረ-ሥጋዌ (ክፍል ፩)


ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ከሚያስፈልጉን ጉዳዮች ቀዳሚዎቹ በእግዚአብሔርና በክርስቶስ ማመን (ምሥጢረ-ሥላሴና ምሥጢረ-ሥጋዌ)፡ መሆኑን በመጥቀስ ምሥጢረ-ሥላሴን ባለፈው ጽሑፋችን በጭሩ አይተናል። በዚህ ክፍል በክርስቶስ ስለማመን የምንማርበትን ምሥጢረ-ሥጋዌን እንዲሁ አጠር አድርገን እናያለን።
ሥጋዌ የሚለው ቃል ተሠገወ- ሥጋን ለበሰ፡ ሰው ሆነ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ነው።  ምሥጢር ማለት  የማይነገር ሳይሆን የማይመረመር ለማለት ነው። ቀደም ሲል በምሥጢረ-ሥላሴ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ብለን ካየናቸው ከሦስቱ አካላት አንዱ የሆነው ወልድ አዳምንና የሰውን ልጅ ለማዳን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ለብሶ ሰው መሆኑን የምናይበት ትምህርት ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን እና እንዴት ሰው ሆነ?
ለምን የሚለውን ወደታች እናያለን። እንዴት ለሚለው ግን ከድንግል ፡ያለወንድ ዘር፡ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ብለን ከመግለጽ በቀር ሰማይና ምድር የማይችሉት የማይወሰነው አምላክ እንዴት እንደተወሰነ፡ ለመመርመር አንችልም። ምሥጢር ያሰኘውም ይህ ነው። ለምን ሰው ሆነ? የሚለው ምሥጢር አይደለም፣ ሊነገርና ሊመሰከርለት የሚገባ ግልጽ የምሥራች ቃል ነው።  ይሄውም እርሱ ሞቶ እኛን ለማዳን ነው።
ወልድ ሰው ከመሆኑ በፊት አምላክ ብቻ ነው። ሥጋን ለብሶ ሰው ከሆነ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ በአንድነት(በተዋሕዶ) አምላክም ሰውም ይባላል። ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና ሰው አይደለም፡ አምላክም ሰውም ነው። ፍጹም የሆነ አምላክ ፍጹም የሆነ ሰው። አምላክነቱን ብቻ እያየን ሰውነቱን መዘንጋት የለብንም፡ ሰውነቱንም ብቻ እያየን አምላክነቱን መዘንጋት የለብንም። ሁለቱንም አጣምረን በአንድነት /በተዋሕዶ/ ማመን መቀበል አለብን።
 
የዚህን ነጥብ አስፈላጊነት ለመረዳት ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አንደምሳሌ እንይ
ከእኔ አብ ይበልጣልና። ዮሐ ፲፬፡፳፰
እኔና አብ አንድ ነን። ዮሐ ፲፡፴
ክርስቶስ ይህን ቃል የተናገረው ሰው ሆኖ እያስተማረ በአንድ ተመሳሳይ ወቅት ነው። ቃሉን እንዲሁ ስናየው ተቃራኒ ነው።ምሥጢረ-ሥጋዌን ማለትም ክርስቶስ አምላክም ሰውም መሆኑን ስናውቅ ግን ከእኔ አብ ይበልጣል ያለው በሰውነቱ፡ እኔና አብ አንድ ነን ያለው በአምላክነቱ መሆኑን እንረዳለን። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነትና ሰውነት ማወቅ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው ማለት ነው። ሌላም ጥቅስ ምሳሌ ማየት እንችላለን፡-
«ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ። እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት።» ዮሐ ፳፡፲፯፡፡
   - አባቴ ሲል የባሕርይ አባቱ ስለሆነ አምላክነቱን
  - አምላኬ ሲል ፍጹም ሰው በመሆኑ - ሰውነቱን ያሳያል፡
  አባታችሁ ሲል እግዚአብሔር የሁላችን የጸጋ አባት ነው። አምላካችሁ ሲልም እግዚአብሔር አምላካችን ነው።
«በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።» ኤፌ ፩፡፫።
 - የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ሲል ሰውነቱን፡ አባት ሲል አምላክነቱን ያሳያል።
የዚህ ዓይነት ጥቅሶች ብዙ ናቸው፡ ሁሉንም በየቦታቸው ስንደርስ እናያቸዋለን። እያየን ያለነው ነጥብ የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና ሰውነት የማይለያይ መሆኑን ነው። እርሱ ሥጋን ከለበሰ በኋላ ሁልጊዜም ለዘላለም ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆኖ የሚኖር መሆኑን ምንጊዜም መዘንጋት የለብንም። መጽሐፍ ቅዱሳችን ስናጠናም ይህን ጉዳይ ዘወትር ማሰብ አለብን።         
ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ሰው ሆነ?
እንግዲህ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነበትን ምክንያት ከመሠረቱ እንይ።  
      - እግዚአብሔር ዓለምን በወልድ ቃልነት ፈጠረ፤
- በኃጢአት የወደቀውን ዓለም በወልድ ሰውነት (በክርስቶስ ሞት) አዳነ።
      - በመጨረሻም ይህንን ዓለም በወልድ ዳግም ምጽአት ያሳልፈዋል።
ስለዚህ ዓለምንና የሰውን ልጅ በተመለከተ ሁሉም የሆነውና የሚሆነው በወልድ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
«ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።» ዮሐ ፩፡፫።
መጽሐፍ ቅዱስ በዋናነት የሚናገርውን ጉዳይ በአጭሩ እንግለጽ ቢባል፡-
 - እግዚአብሔር ዓለምን ሁሉ እንደፈጠረ፡   - ከዚያም ዓለሙ በሰው ኃጢአት እንደተበላሸ፡
 - ኢየሱስ ክርስቶስን ዓለምን ሁሉ ለማዳን እንደሞተ፡ - ከዚያም ሰው ሁሉ በእርሱ በማመን እንደሚድን፣
  - ዓለሙ ሁሉ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት እንደሚያልፍ፡ - ከዚያም ያመኑ ወደዘላለም ሕይወት፡ ያላመኑ ወደ ዘላለም ቅጣት እንደሚሄዱ ይናገራል።  የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ፍሬ ነገር ኢየሱስ ክርስቶስ ስላደረገውና ስለሚያደርገው ነገር መናገር ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ለማወቅ ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ዋና ጉዳይ ነው ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ሲባል ደግሞ እንዲሁ ማወቅ ብቻ ሳይሆን በትክክለኛ ማንነቱ (በሰውነቱም በአምላክነቱም) በማመን እና በሕይወት ማወቅ (በእርሱ አዳኝነት ማመንና መኖር) ሆኖ በተግባር ማወቅ ነው። 
«እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።»       ዮሐ ፲፯፡፫
ይቀጥላል።…..

2 comments:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን ስለ ሚስጥረ ስጋዌ ትምህርትህ እጅግ በጣም ጥሩ ነው ሰምቶ ለመጠቀም ያብቃን!!!

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን! መልካም ጅምር ነው!!!

    ReplyDelete

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment